1. ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ስለ ተቋማዊ ማሻሻያ፣ ኢኮኖሚ፣ ጸጥታ፣ መገናኛ ብዙኻን ነጻነትና ፖለቲካ ምህዳር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በባለፈው ሳምንት መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ቀደም ሲል ቤተ መንግሥት ድረስ ገብተው የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡ ሙከራውም መፈንቅለ መንግሥት እንደነበር አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡ በእስካሁኑ የመንግስት ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ 48 የሽብር ቡድን አባላት፣ 799 በብሔር ጥቃት የተጠረጠሩ መሪዎችና የጸጥታ አካላት፣ በኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 34፣ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር 64 ግለሰቦችና 51 ደሞ በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር አስረናል ብለዋል፡፡ በደቡብ ክልል ለመሆኑ የተነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ ምላሽ ለመስጠት ጊዜና ትዕግስት ያስፈልጋል፤ በተናጥል ክልልነትን ማወጅ እንደማያዋጣ ተናግረዋል፡፡ ስለ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ደሞ ሕገ መንግሥቱን የማይቀበል ሰው ለምርጫ መዘጋጀት የለበትም፤ የሃሳብ ነጻነት መብቱን መጠየቅ አይችልም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
2. በተያያዘ ዜና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በተያዘው ዐመት በ9.2 በመቶ እንደሚያድግ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ዐመታዊ የሥራ ሪፖርት ተናግረዋል፡፡ በ12 በመቶ ተገትቶ የነበረው ዋጋ ግሽበት ግን አሁን ወደ 16.2 ንሯል ብለዋል፡፡ ሃች አምና በዚህ ወቅት የግሽበቱ መጠን 16.1 በመቶ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
3. የጡረተኛው ጀኔራል አብርሃ ወልደ ማርያም ቀብር ስነ ሥርዓት ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተፈጽሟል፡፡ በቀብሩ የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጺዮን ገብረ ሚካዔልና የፌደራል መንግሥቱ ባለ ሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡ ጀኔራሉ ታይላንድ ሕክምና ላይ ሳሉ ነው ዐርብ ዕለት ሕይወታቸው ያለፈው፡፡
4. ለዛሬ የበረከት ስምዖንና ታደሠ ካሳን የክስ መዝገብ ላይ ምስክር ለመስማት ቀጠሮ ይዞ የነበረው ችሎት ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ችሎቱ ያልተካሄደው አንድ ቀሪ የዐቃቢ ሕግ ምስክር በአካል ባለመቅረባቸው እንደሆነ የአማራ ብዙኻን መገናኛ ዘግቧል፡፡ ችሎቱ ቀጣዩን ቀጠሮ ለሐምሌ 5 ነው የቀጠረው፡፡ በመዝገቡ 3ኛው ተከሳሽ አቶ ዳንዔል በጤና እክል ሳቢያ ዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ችሎቱ ግን ሳይቀበላቸው ቀርቷል፡፡
5. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በቀድሞው የአዲስ አበባ መንገዶች ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፍቃደ ኃይሌ ላይ የከፈትኩትን የሙስና ወንጀል ክስ አቋርጫለሁ ብሏል፡፡ ሪፖርተር እንዳስነበበው ከሥራ አስኪያጁ ጋር ተከሰው የነበሩት ሙሉጌታ አብርሃ (ኢንጅነር)፣ አህመዲን ቡሴር (ኢንጅነር)፣ ዋስይሁን ሽፈራው (ኢንጅነር) የተባሉ የሥራ ሃላፊዎችና እስራኤላዊው ሜናሼ ሌቪ ጭምር ክሳቸው ተቋርጦላቸዋል፡፡ ግለሰቦቹ በግንቦት 2009 ዓ.ም ከመንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘ ከ198.9 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ነበር በቁጥጥር ስር ውለው የተከሰሱት፡፡ ተከሳሾቹ ቀደም ሲል የጉዳቱን መጠን ከፍለው እንዲፈቱ ሲጠየቁ አልተስማሙም ነበር- ብሏል ዘገባው፡፡
6. 30ኛው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዐመታዊ የስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ትናንት በአትላንታ ጆርጅያ ተጀምሯል፡፡ በመክፈቻው ስነ ሥርዓት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ንግግር አድርገዋል፡፡ ዝግጅቱ የተለያዩ ውድድሮችን እያስተናገደ እስከ ሰኔ 29 ይቆያል፡፡