የዴሞክራሲን ሰብል በጅብ እርሻ እንዲል ዳኛቸው || አቤል ዋበላ

የዴሞክራሲን ሰብል በጅብ እርሻ እንዲል ዳኛቸው || አቤል ዋበላ

ብዙዎች ሀገራቸውን ከመውደዳቸው እና ሰላምን ከመፈለጋቸው የተነሳ ፅንፈኛ ከሆኑ አማራጮች ይልቅ መሀከለኛውን መንገድ ይመርጣሉ። መግፍኤ ምክንያቱ ለሰው ልጅ መልካሙን መመኘት ስለሆነ ሊበረታታ የሚገባው አስተሳሰብ ነው። ነገር ግን ሁሉም ጉዳይ መሀል የለውም። ወይም መካከለኛው መንገድ ወደ አንደኛው መጥፎ ፅንፍ የሚወስድ ይሆናል። አንድም መካከለኛ የተባለው መንገድ የአጥፊው ስትራተጂያዊ ስልት ሊሆን ይችላል:: ለምሳሌ በሞት እና በህይወት መካከል ያለ ህላዌ የለም። አለ ከተባለም ያለው ታሞ መማቀቅ ነው፡፡ ህመሙም ወደሞት የሚያደርስ ነው፡፡ ምሳሌ ነው፡፡

የሀገራችን ፖለቲካም መካከል በሌላቸው ጉዳዮች ተወጥሯል፡፡ መካከለኛ መንገዶች አሉ ከተባሉም የጅብ እርሻ ናቸው፡፡ ዶር ዳኛቸው ቆየት ባለ አንድ ጽሑፉ ከአንድ አዛውንት ተውሶ በሜታፎር እንዳሰፈረው ጅብ አያርስም፣ ካረሰ ግን እስኪያድግ አይጠብቅም፡፡ ገና በቡቃያው ይበላዋል፡፡

ይህንን ገሐዳዊ እውነታ ወደ ጎን አድርገን ከጅብ ጋር ደቦ ገብተን ወደ እርሻ ልንገባ ያሰብንባቸው ሦስት ዋና ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም ምርጫ፣ የዜግነት ፖለቲካ እና ሀገር ግንባታ ናቸው፡፡

የጅብ እርሻ አንድ – የምርጫ እና መድብለ ፓርቲ ስርዓት

ምርጫ ቦርድን በመቀባባት ብርቱካን፣ ብርቱካን እንዲሸት በማድረግ ያለ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ወደ ምርጫ መግባት በራሱ የዜሮ ድምር ጨዋታ ነው፡፡ መንግስት እስካሁን ሕገ መንግስቱን ላለማሻሻል የሚሰጠው ምክንያት ቅቡልነት(legitimacy) የለኝም በሚል ነው፡፡ ነገር ግን ምርጫ ለማካሄድ ግን አይኑን አያሽም፡፡ ምርጫው እራሱ ሕጋዊ መሠረት ያገኘው በዚህ አንካሳ ሕገ መንግስት መሆኑን ለማዘናጋት ይሞክራል፡፡ ምርጫው የሚደረገው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 እና 38 መሠረት ነው፡፡ ሕገ መንግስት ለማሻሻል ማንዴት የሌለው መንግስት ምርጫ ለማካሄድም ማንዴት አይኖረውም፡፡ ይህንን ሂደት በአጋፋሪነት የሚሳተፍ በሙሉ፤ በመራጭነት፣ በተመራጭነት እና አስመራጭነት የተሰማራ ኹሉ ጅቡ አጎቱ ነው አሊያም ራሱ ሰብሉ ሳይደርስ ቡቃያውን ሊበላ የቋመጠ ጅብ ነው፡፡ ከዚህ የምርጫ ሂደት የሚወለድ ዴሞክራሲ ወደ ፍትሓዊ ማኀበረሰብ የሚያደርስ መንገድ የለም፡፡

የጅብ እርሻ ሁለት – የዜግነት ፖለቲካ

ሌላ ደግሞ ሰፊ የጅብ እርሻ አለ፡፡ ዜጎችን አደራጅቼ እና የፖለቲካ ስራ ሰርቼ የሀገር ባለቤት አደርጋለኹ ብሎ የሚከራከር፡፡ ነገር ግን በተግባር እንዴት ባለቤት የሚያደርግ ግራ የገባው አጃቢ አለ፡፡ በመላው ሀገሪቱ አንድ ስንዝር እንኳን በብሔር ያልተያዘ መሬት የለም፡፡ የመጫወቻ ሕጉ ራሱ ሙሉ እውቅና የሚሰጠው ለብሔር ብሔረሰቦች ነው፡፡ ህጉም ሜዳውም በብሔረሰብ ብቻ የተያዘ ነው፡፡ ነገር ግን የዜጎችን መብት አስከብራለኹ ብሎ የዜጎች የፖለቲካ ማኀበር ከመሰረቱ በኋላ ለዜጎች እውቅና ለማይሰጥ ሕገ መንግስት እውቅና ሰጥቶ ሕገ መንግስቱን አክብሬ እንቀሳቀሳለኹ ብሎ በጅብ እርሻ የዜግነት ሰብልን የሚዘራ ነሆለል አለ፡፡ ምርጫም ገብቼ እወዳደራለኹ ይላል፡፡ ፍትሓዊ ባልሆነ፣ ባጋደለ ሜዳ የሚወዳደረው ለመሸነፍ ነው? ከወዲሁ መሸነፉ የተረጋገጥን ቡድን ለምን ብዬ ነው የምደግፈው? ቢያሸንፍ እንኳን ሰብሉ እና ቡቃያው በጅቡ ላለመበላቱ ምን ዋስትና አለው? የአጃቢውን ትራፊ ከሚሰጡኝ የሙሽራው ምን አለኝ አንደተባለው ነው የሚሆነው፡፡ ህዝቡ ከኢህአዴግ አጃቢ ከሚቀላውጥ ከራሱ ከኢህአዴግ ቢለምን ይሻለዋል፡፡ የማይታወቅ ዜጋ በማይታወቅበት ሀገር ምርጫ ሊወዳደር ቀርቶ ሁነኛ የፖለቲካ ስራ ሊሰራ አይችልም፡፡

የጅብ እርሻ ሦስት – ሀገር ግንባታ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን መውደዳቸውን በብዙ ቀልብ በሚስቡ ንግግሮቻቸው ገልጸዋል፡፡ በርካታ ያከናወኗቸው ተግባራትም ይህንን ይመሰክራሉ፡፡ ከተራ ግለሰብ ጀምሮ በርካታ ሰዎችን የሚጠቅም ስራ ሰርተዋል፡፡ እነዚህ በጎ ምግባሮች በራሳቸው ግን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት የሚያረጋግጡ አይደሉም፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 8.1 የሀገር ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነትን ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ይሰጣል፡፡ ይህም የተለያዩ ብሔረሰብ ነን የሚሉ አካላት ራሳቸውን እንደሀገር እንዲቆጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህንን ሕገ መንግስት ለማሻሻል የሚያሳዩት ዳተኝነት ንግግራቸውን ሽንገላ ሲያደርገው፤ የነገሰውን የተረኝነት መንፈስ ደግሞ አደባባይ ያስጣዋል፡፡ እነዚህ ሀገሮች/ብሔሮች የራሳቸው የሆነ የተወሰነ ድንበር፣ ልዩ ኃይል አደራጅተው ሀገር የሚሉትን ነገር እየገነቡ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በስብጥር በሚኖሩባቸው ቦታዎችም የዘር ማጽዳት እና ሶሻል ሪኢንጂነሪንግ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ሀገሪቱ ከፌዴሬሽን ይልቅ የኮንፌዴሬሽን ቅርጽ ይዛለች፡፡ እንዲያም ሆኖ የበለጠ አውቶኖሚ የሚጠይቁ ባለጊዜዎች ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ ሂደት ሀገር እንዴት እንደሚገነባ ግልጽ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ስልጣን በብሔር ተዋጽኦ እየተሰላ ስለሚሰጥ ሁሉም ለኩርማን ሀገሩ ዳንቴል የሚሰራ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ከሀገር ይልቅ የክፍለ አሕጉር ትብብር መድረክ እየመሰለች ነው፡፡

ኢትዮጵያን መውደድ እና መጥላታችንን ወደ ጎን እናድርገውና ስለምንገነባው ሀገር ግልጽነት ይኑረን፡፡ አንድ ኢትዮጵያ ከተባለ መዋቅራዊ ማስተካከያዎች አድርገን ስለ አንድ ሉዓላዊነት ሀገር ግንባታ በየዘርፋችን እንድከም፡፡ አለበለዚያ ዘጠኝ እና ከዚያ በላይ(ሕገ መንግስቱ ሉዓላዊነትን የሚሰጠው ለክልሎች ሳይሆን ለብሔሮች ስለሆነ ሉዓላዊ ብሔሮች ክልል እና ሀገር ከመሆን የሚከለክላቸው ነገር የለም፡፡) ሀገሮች ከሆነም ግልጽ ይሁንና ወደየጥጋችን እንሂድ፡፡ የኔ ቢጤ ኢትዮጵያን ብቻ ያለ ደግሞ ከተባበሩት መንግስታት ሀገር ለሌላቸው ሰዎች የሚሰጥ ፓስፖርት መሰደድ ይችላል፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስተሩ እያስተዳደሩት ያለው ሀገር በዘጠኝ ሀገር እና በአንድ ሀገር መካከል የሚዋልል ነው፡፡ እርሳቸውን በኢቲቪ ሳያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ይልቅ የኢጋድ ሊቀመንበር መሆናቸው ይጎላብኛል፡፡ ይህንን አንድ ሲሉት ዘጠኝ የሚሆን ሀገር መገንባት ማለት የጅብ እርሻ ነው፡፡ ጅብ አያርስም፣ ካረሰ ግን እስኪያድግ አይጠብቅም፡፡ ገና በቡቃያው ይበላዋል፡፡

                         🎤🎤🎤🎤🎤🎤🎤🎤

LEAVE A REPLY