የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች || ሰኔ 26 /2011 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች || ሰኔ 26 /2011 ዓ.ም

“ፓልም ዘይት” ለሳሙና ፋብሪካ ግብዓት የሚውል ተረፈ ምርት መሆኑ ታወቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ አገር ቤት እንዳይገባ የታገደው ‹‹ፓልም›› ዘይት ለሳሙና ፋብሪካ የሚውል ተረፈ ምርት እንዲሆን ተገለፀ፡፡

ለበርካታ ዓመታት በመንግስት ቀጥተኛ ገንዘብ እየተገዛ ለሕዝብ እንዲሰራጭ ሲደረግ የኖረው ቀላጩ ‹‹ፓልም›. ዘይት ለጤና አስጊ መሆኑና በተለይም ለኮሌስትሮል የሚያጋላጥ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ጉዳዩ የሚመለከተው መንግስታዊ አካል (ኢህአዴግ) ሀቁን እያወቀ ዘይቱን በቅናሽ ዋጋ ለሕዝብ ያሰራጭ እንደነበር አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው ኦህዴድ የአሁኑ ኦዴፓ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አምባሳደር ሱሌይማን ከዓመታት በፊት ለኦሮሚያ ፕሬዝዳት ወንበር ሲጠበቁ ከአባዱላ ገመዳና ከሕወሓት ሹማምንት ጋር ባላቸው አለመግባባት የተነሳ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በአምባሳደርነት እንዲያገለግሉ መገደዳቸው ይታወሳል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ሱሌይማን አሁን በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርነት አገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
በለውጡ ማግስት የወያኔ/ኢህአዴግ ስርዓት ከውጭ አገር ከሚያስገባው የስንዴ አቅርቦት ጋር በተያያዘ 55 ሺኅ ቶን የበሰበሰ ስንዴ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባቱን ያጋለጡት አምባሳደር ዛሬ ደግሞ ሌላ ጉድ ይፋ አውጥተዋል፡፡

መንግስት ወደ ኢትዮጵያ ሲያስገባውና ሕዝብ ሲመገብ የኖረው “ፓልም ዘይት” ሶስተኛ ደረጃ የዘይት ተረፈ ምርት እንደሆነ ተሰምቷል፡፡ “ምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘይት እያለ ሲመገብ የኖረው ለሳሙና ፋብሪካ የሚውል ተረፈ ምርት ነው” ያሉት አምባደር ሱሌይማን ደደፎ ፤ላለፉት ስምንት ዓመታት በተከታታይ ይሄ ምርት በገፍ ወደ አገር ቤት ይገባ እንደነበር ከሸገር ታይምስ ጋር በነበራቸው ቆይታ አረጋግጠዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ግልጽ የሆነ ደብዳቤ ከስምንት ዓመት በፊት ለአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ፅፌ ነበር የሚሉት አምባሳደር ሱሌይማን፤ በወቅቱ በአገሪቱ ዘይት ጠፋ በሚል በጅቡቲና በዱባይ የዘይት ፍለጋው ባልተሳካበት ወቅት፣ ከማሌዥያ የፓልም ዘይት ጭኖ ወደ በግብፅ ለምግብነት ሳይሆን ለሳሙና ፋብሪካ ግብዓትነት እንዲውል የሚጓዝ መርከብ ባህር ላይ መሆኑን የሰሙ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት መላ ዘየዱ፡፡

የግዢ ኤጀንሲና የገንዘብ ሚኒስቴር ሰዎችን በፍጥነትወደ ጅቡቲ በመላክና በመደራደር በመርከቡ የተጫነው ዘይት፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባና ለምግብነት እንዲውል በማድረግ አሳፋሪ ስራ እንዳከናወኑ ያጋልጣሉ፡፡

“በወቅቱ ይህንን ጉዳይ ለጠ/ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ባሳውቃቸውም እሳቸው ግን ይጣራል ብለው ነው ዝም ያሉት” በማለት እውነታውን ገሀድ ያወጡት ሱሌይማን ደደፎ፤ ዘይቱ ለሳሙና ተረፈ ምርትነት እንደሚውል የማሌዥያ ፓልም ኦይል አምራቾች ያረጋገጡላቸው መሆኑን በመግለፅ፣ ቀጣይ ዕርምጃውን ለማቋረጥ ጥረት ቢያደርጉም፤ የኢህአዴግ ሰዎች ግን የመጀመሪያው መርከብ ምርት በገባ ማግስት፣ ከካምፓኒው ጋር የሁለት ዓመት ስምምነት በመፈረም በሕዝብ ላይ የከፋ ግፍ መፈፀማቸውን አስታውቀዋል፡፡

“ፓልም ዘይቱን” የወያኔ መንግስት በጅቡቲ ወደብ በሚያስገባበት ሰዓት፤ ጅቡቲዎች ምርቱ ለምግብነት የማይውል መሆኑን ስለሚያውቁ፣ አገራቸው ውስጥ እንዳይቀር በከፍተኛ ጦር መሳሪያና ፈንጂዎች ታጅቦ፣ ከጅቡቲ እንዲወጣ ልዩ ጥበቃና ሽኝት ያደርጉ ነበርም ብለዋል፡፡

ከ2 ዓመት በኋላ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊዎች ክስ ተቋረጠ

ከሁለት ዓመታት በላይ በዕስር ላይ ሆነው ክርክር ሲያደርጉ የቆዩት የቀድሞ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛ ኃላፊዎች ክስ በድንገት መቋረጡ ተሰማ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ክስ ያቋረጠላቸው የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ለዓመታት ያገለገሉት ኢንጅነር ፈቃደ ኃይሌ፣ ኢንጅነር አህመዲን ቡዴር፣ ኢንጅነር ሙልጌታ አብርሃ፣ ኢንጅነር ዋስይሁን ሽፈራው እና እስራኤላዊው ሚስተር ሜናሼ ሊቪ ናቸው፡፡

በግንቦት ወር 2009 ዓ.ም ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት እነዚህ ግለሰቦች ከ198.9 ሚሊዮን (ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ) ብር በላይ መንግስትን አክስረዋል በሚል ነበር፡፡ “ኪትድሃ ኤክስካቪሽን ኤንድ ኧርዝ ሙቪንግ ሊሚትድ” ጋር፤ ባለስልጣን መ/ቤቱ ከመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ኪሳራውን አድርሷል ተብሎም ተወንጅሏል፡፡

በጊዜው ከማዕድን ሚኒስቴር እስከ ውሃ ሀብት ሚኒስቴር የሚያደርሰው መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን ተንተርሶ ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የቅድመ ክፍያና የመልካም ስራ አፈፃፀም ዋስትና ከኮንትራክተሩ ጋር ተዋውለዋል፡፡ ውሉ ላይ ገንዘብ ወጪ እንዲሆን በመፍቀድ ኃላፊዎቹ ብር 198.872.730 ብር ጉዳት አድርሰዋል በሚልም ተከሰው ነበር፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲከራከሩ የቆዩት ተከሳሾችን ሰሞኑን ዐቃቤ ሕግ ድንገት “ክሴን አቋርጫለሁ” ሲል ገልጿል፡፡

ከዚህ በፊት በተከሳሾቹ ተቀባይነት ያላገኘውንና “የደረሰውን ጉዳት የሚከፍሉ ከሆነ ብቻ ክሱን አቋርጣለሁ” ብሎ የነበረው ዐቃቤ ሕግ፤ ድንገት ከሁለት ዓመት በኋላ “የባለስልጣናቱን ክስ አቋርጫለሁ” ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል፡፡

የቱርኩ “አይካ አዲስ ፋብሪካ” በሁለት ቢሊየን ብር በሐራጅ ሊሸጥ ነው

በዓለም ገና ከተማ በ205 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የተገነባው ግዙፉ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ፋብሪካ በልማት ባንክ አማካይነት ለጨረታ ሊቀርብ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የቱርክ ኩባንያው “አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ኢንቨስትመንት ግሩፕ” ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበደረውን ገንዘብ ለመመለስ ባለመቻሉ፣ ኩባንያውና ንብረቶቹ በልማት ባንኩ ከተወረሱ ሰነባብተዋል፡፡ ሆኖም ለፋብሪካው በጠቅላላ ከ2.8 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ሰጥቶ የነበረው ልማት ባንክ፣ ፋብሪካውን ወደ ሁለት ቢሊየን ብር በሚጠጋ ገንዘብ ለመሸጥ በሐምሌ ወር ለጨረታ እንደሚያቀርበው ታውቋል፡፡

ልማት ባንኩ ባወጣው ማስታወቂያ ፋብሪካው ለብቻው ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ ለጨረታ ይቀርባል፡፡ በተለያዩ ሶስት ዙሮች የሚሸጡ የተከማቹ ልዩ ልዩ አልባሳት ደግሞ፣ በድምሩ 130 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ገንዘብ በሌላ ጨረታ እንደሚቀርቡ መረዳት ተችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ፋብሪካውን የተረከበው ልማት ባንክ የሐራጅ ጨረታውን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ይፋ አድርጓል፡፡

ኦነግ እና ኦፌኮ አባሎቻችን በኦሮሚያ ክልል እየታፈኑ ነው አሉ

በነቀምት፣ በጊምቢ፣ በገሊሳ ወረዳ፣ በለመና በጉጂ ዞን በርካታ የኦ.ፌ.ኮ አመራሮች “ኦነግ ናችሁ” በሚል ሰበብ እየታሰሩ መሆኑን የድርጅቱ ም/ሊመንበር ሙላቱ ገመቹ ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ጉጂ የሚገኘው የኦ.ፌ.ኮ ጽ/ቤት በአካባቢው ባሉ ኮማንድ ፖስት አመራሮች መበርበሩንና በጽ/ቤቱ ሠራተኛ ላይም  ከባድ ደብደባ መፈፀሙንም ገልጸዋል፡፡

በርካታ የኦሮሚያ ዞኖች በኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ስር ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ኮማንድ ፖስቱ በነቀምትና በሌሎች አካባቢዎች፣ የኦ.ነ.ግ አባል በሚል ሰበብ በርካታ ሰዎችን እያፈሰና እያሰረ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የኦነግ አመራር የሆኑት አቦ ቶሌራ አደባም በምስራቅ ሐረርጌ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራና ወለጋ ጥቂት የማይባሉ አባሎቻቸው እየታሰሩ መሆናቸውን በተመሳሳይ ገልፀዋል፡፡

በዶ/ር መራራ ጉዲና እና በአቶ በቀለ ገርባ የሚመራው ኦ.ፌ.ኮ በቅርቡ  ከኦነግ ጋር ውህደት ለመፍጠር ከስምምነት ጋር መድረሱና አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ከወዲሁ በጋራ ማከናወን መጀመሩ ይታወሳል፡፡
በሶማሌና ኦሮሚያ ሴቶች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀምባቸዋል ተባለ

በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚገኙ ሴቶች ውስጥ 23 በመቶ የሚሆኑት የአካላዊ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ የኃይል ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቆም በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው 8ኛ አገር አቀፍ ጉባኤ ላይ ነው ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው፡፡

34 ከመቶ ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው ጥቃት ሲደርስባቸው፣ ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች መካልም 29 ከመቶው አካላዊ ጉዳት እንደሚፈፀምባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ መልክ ተጠቂ ከሆኑት መሀል 23 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ እርዳታ እንደሚጠይቁ ነው የተነገረው፡፡

በተጠቀሱት ክልሎች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቀረት፤ በአገራችን በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ የተለያዩ የኃይል ጥቃቶችንም ለመዋጋት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስወገድ ዋነኛ መፍትሄ መሆኑ በጉባኤው ተነግሯል፡፡

የአ.ብ.ን አባላት አሁንም እየተሰሩ ነው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ክርስቲያን ታደለ ታስሮ ተፈቷል

የአማራ ብሔራዊ  ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ከዕስር መፈታቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ የተፈፀመውን ስልጣንን ያለ አግባብ የመቆጣጠር ድርጊት ጋር ተያይዞ በርካታ የአ.ብ.ን አባላትና በተለያዩ ከተሞች የሚያገለግሉ የድርጅቱ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በፍጥነት ቢሆንም፤ ወጣቱ ፖለቲከኛ ግን ለስድስት ቀናት ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥመው ቆይቷል፡፡

ጥቂት የማይባሉ የአማራ ወጣቶች በአ.ብ.ን ደጋፊነት እየተለቀሙ ከገቡ ከስድስት ቀናት በኋላ፤ ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም “ሰከላ” ወረዳ ውስጥ ክርስቲያን ታደለ ተይዞ ለእስር ተደርጎ ነበር፡፡ ከክርስቲያን ባሻገር ሌሎች ሁለት የምክር ቤት አባላትም በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ቆይተዋል፡፡

ይሁንና የአ.ብ.ን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፈ አቶ ክርስቲያን ታደለ ከአንድ ቀን ዕስር በኋላ እንደተፈቱና ወደ መደበኛ የስራ ገበታቸው መመለስ እንደቻሉ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በአማራ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ፣ በርካታ የአ.ብ.ን አባላትና ደጋፊዎች በስፋት እየተያዙና የሽብርተኝነት ክስ እየተመሰረተባቸው መሆኑን ከአ.ብ.ን ሊ/መንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ መረዳት ችለናል፡፡

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ የመከላከያና የደህንነት ኃላፊዎች ሹመት እያነጋገረ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሶስት የመከላከያና የደህንነት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ሹመት መስጠታቸውን ተከትሎ በብሔር የበላይነት ሂደት አሁንም በኢትዮጰያ ስጋት መሆኑ ተገለጸ፡፡ በጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም የስልጣን ጊዜ “የአየር ኃይል አዛዥ”፣ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ስልጣን በያዙ ማግስት “የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር” የነበሩት ጀነራል አደም መሀመድ ሰሞኑን አዲስ ሹመት ተሰጥቷል፡፡

ሰኔ 15 ቀን በመኖሪያ ቤታቸው የተገደሉት የጀነራል ሰዓረ መኮንን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹመት ጀነራል አደም መሐመድ ተረክበዋል፡፡ በተጨማሪም ሌተና ጄነራል ሞላ ኃይለማርያም የምድር ኃይል ዋና አዛዥ፣ አቶ ደመላሽ ገብረሚካኤል የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመዋል፡፡ ሌተና ጄነራል ሞላ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ አሁን በአዲሱ ሹመታቸው የምድር ኃይልን በዋና አዛዥነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡

አቶ ደመላሽ ከአንድ ዓመት በፊት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ም/ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል፡፡ ከዛ በፊት የኦሮሚያ ከልል ምክትል ኮሚሽነር፣ የፌደራል ፖሊስ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ዳይሬክተር በመሆንም አገልግለዋል፡፡

ይህንን ሹመት ተከትሎ በተልይ የመከላከያና የደህንነት ተቋማትን ብቻ ሳይሆን የጸጥታ ሃይሉን እንቅስቃሴ ኦህዴድ/ኦዴፓ መያዙ ኢሓዴግ የሚመራበትን የኮታ ከፍፍል የስልጣን ተዋረድ ወደ ባለተረኝነተ የፖለቲካ ቅብብሎሽ መሸጋገሩን ያሳያል የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች   የሀገሪቱን ዋና ዋና የስልጣን ቦታዎች ከህወሃት ወደ ኦህዴድ/ኦዴፓ መሸጋገሩን ያመላክታል ይላሉ:: በህወሃት አሰራር ዋና እና የሰራስኪያጅ ቦታዎች ለሌሎች ክልሎች ቢሰጡም  ምክትል በሆኑ የሀወሃት አባላት አድራጊ ፈጣሪ የሚሆኑበት አሰራር እንደነበር ይታዎሳል:: በአሁኑ ሰአት የሚሰጡ ስልጣኖች ሙሉ በሙሉ በኦዴፓ አባላት መታደሉ የሀገሪቱን የፖለቲካ ድባብ አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አሰተያየት ሰጭዎቹ ለኢትዮጰያ ነገ ገልጸዋል::

LEAVE A REPLY