በሐረር ለደረሰው የእሳት ቃጠሎ የመብራት ኃይል እጅ አለበት ተባለ

በሐረር ለደረሰው የእሳት ቃጠሎ የመብራት ኃይል እጅ አለበት ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሐረር ከተማ በተለምዶ “መብራት ኃይል” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተነሳ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ከ300 በላይ የንግድ ሱቆች መውደማቸው ታውቋል፡፡

ለሶስተኛ ጊዜ በሐረር የንግድ ሱቆች ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ፣ ምን ያህል ንብረት እንዳወደመ ለጊዜው በትክክል ባይታወቅም ኪሳራው ግን ከባድ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቷል፡፡

በገበያ ማዕከሉ አንድ ብሎክ ላይ የሚገኙ ሱቆች ሙሉ ለሙሉ በእሳት ቃጠሎው ወድመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም “ሸዋ በር” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰባቸው የእሳት ቃጠሎ ቦታውን ለቀው ወደ እዚህ ስፍራ እንዲመጡ የተደረጉት ነጋዴዎች፣ አሁን በሚገኙበት ስፍራም በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ለእሳት አደጋ ተጋልጠዋል፡፡

የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው፤ አደጋው በደረሰበት ቦታ በሰጡት መግለጫ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ፌደራል ፖሊስና ሕብረተሰቡ ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ እሳቱን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የተቃጠለው ቦታ የኤሌከትሮኒክስ ዕቃዎች፣ አዳዲስ ጨርቆች፣ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች የሚሸጡበት ግዙፍ የገበያ ማዕከል ነው:: በቃጠሎው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ነጋዴዎች፣ በቅርቡ መብራት ኃይል “ይዞታውን ልቀቁ” የሚል ማስታወቂያ ከለጠፈባቸው በኋላ ይህ አይነት አደጋ ሊከሰት እንደሞችል ስጋት አድሮባቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ “ቦታውን በአስቸኳይ ልቀቁ” ካላቸው መብራት ኃይል ግቢ ውስጥ እሳቱ መነሳቱ ደግሞ ጥርጣሬያቸውን የበለጠ እንዳሳደገው ገልጠዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ይህን ይበሉ እንጂ የሐረሪ ክልል የኤሌትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሊድ ጣሃ ነጋዴዎቹ ያሉበትን መሬት በ2003 ዓ.ም የከተማ ልማትና ማዘጋጃ ቤት ከዚሀ በፊት ነጋዴዎቹ በነበሩበት ቦታ የእሳት ቃጠሎ ሲያጋጥማቸው መሬቱን ከመብራት ኃይል በውሰት ወስዶ ለነጋዴዎቹ እንደሰጠ ገልፀዋል፡፡ በመብራት ኃይሉና በነጋዴዎቹ መሀከልም ቀጥተኛ ድርድር እንዳልተደረገም ተናግረዋል፡፡

LEAVE A REPLY