ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በእስራኤል ፖሊስ የተገደለው የወጣቱ ሰለሞን ተካ ሞት ያስቆጣቸው ኢትዮጵያውያን፣ በእስራኤል የጀመሩትን ተቃውሞ ቀጥለውበታል፡፡ ሰኞ ዕለት የጀመሩት የአደባባይ ሰልፍና ከፍተኛ ተቃውሞ እስከ ረቡዕ ምሽት ድረስ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በትናንትናው ዕለት ባካሄዱት የአደባባይ ሰልፍ የመኪና መንገዶችን በመዝጋት፣ ጎማና መኪኖችን በማቃጠል ተቃውሞአቸውን በግልጽ ለዓለም አሳይተዋል፡፡ ፖሊስ አስለቃሽ ጢስና አስደንጋጭ ተኩሶችን በመክፈት ሰልፈኞቹን ለመበተን ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም፡፡
ሀሳባቸውንና ተቃውሞአቸውን እንዳያሰሙ የተከለከሉት ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር ባደረጉት የድንጋይ ግጭት 111 (አንድ መቶ አስራ አንድ) ፖሲሶች ቆስለዋል፡፡ ጠ/ሚ/ር ቤኒያሚን ኔታንያሁ “በሰለሞን ተካ ሞት ሁላችንም አዝነናል፡፡
ሟቹ ለሁላችንም ተወዳጅ ነው፡፡ መወገድ የሚገባው ችግር እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ግን መንገድ በመዝጋት ችግሮችን አታባብሱ፡፡ ጥያቄያችሁ በሕጋዊ መንገድ ይመለሳል” ቢሉም ሰሚ አላገኙም፡፡ የ18 ዓመቱን ወጣት ሕይወት ሕልፈት ተከትሎ በተደረገው ተቃውሞ በትናንትናው ዕለት ብቻ 136 ሰልፈኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡