ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ከጧቱ 2 ሰዓት ብስራተ ገብርኤል አካባቢ፣ ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ምክንያት የተገደሉት የሁለቱ ወጣቶች የሞት ምክንያትና ለግድያቸውም ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል አለመገኘቱ በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካትሪን ሀምሊን ቅርንጫፍ የቢዝነስ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሟች ኢሳይያስ ታደሰና ሞተረኛ ጓደኛቸው ላይ ግድያው የተፈፀመው፣ ግለሰቡ ተከራይተው ከሚኖሩበት ቤት ወደ መሥራያ ቤታቸው በቅርብ ጓደኛቸው ሞተር እየተሸኙ ባሉበት ወቅት ነበር፡፡
የ33 ዓመቱ ወጣትና የባንክ ባለሙያ አቶ ኢሳይያስ ተወልደው ያደጉት በተለምዶ ሰባ ደረጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን በዕለቱ አብሯቸው አድሮ ሲሸኛቸው የነበረው ባልንጀራቸውም የእዛው አካባቢ ልጅ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ሟች አቶ ኢሳይያስ ሽንጣቸው አካባቢ በአንድ ጥይት ተመትተው መሞታቸውን ወላጅ አባታቸው በሆስፒታል ተገኝተው አረጋግጠዋል፡፡ ከኃዘኑ በኋላ ጉዳቱን ያደረሰው የፀጥታ አካል በቁጥጥር ስር ውሎ ይገኝበታል ወደ ተባለው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሟች ቤተሰቦች በሄዱበት ወቅት “ጉዳዩ ወደ ማዕከላዊ ተመርቷል” ቢባሉም በማዕከላዊ በኢሳይያስ ስም የተከፈተ ፋይል የለም ተብለው ተመልሰዋል፡፡
ከብዙ መንከራተት በኋላ በማዕከላዊ ሰኔ 25 ቀን አዲስ የክስ ፋይል ቢከፍቱም፣ ጉዳቱን በወጣቶቹ ላይ ያደረሰው የፀጥታ አካል ማንነትንእስካሁን ድረስ ግልፅ ሊሆን አልቻለም፡፡ በዕለቱ በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ከፀጥታ ኃይሎች መኪና ላይ በተተኮሰ ጥይት የሁለቱም ወጣቶች ሕይወት ሊያልፍ መቻሉን ተናግረዋል፡፡