ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም

ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም

ዜና ኢትዮጵያ ነገ ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም

የባልደራሱ ባለአደራ ምክር ቤት ነገ መግለጫ ይሰጣል፤ ጸሃፊው ኤልያስ ገብሩ በሽብር ተከሷል

በጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ በሚመራው የባለአደራው ም/ቤት (ባልደራስ) አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚደርሰው ቀጥተኛ ጥቃት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ዛሬ ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም የም/ቤቱ ዋና ጸሐፊ የሆነው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩን ጨምሮ አስራ አራት ግለሰቦች “የሽብርተኝነት ድርጊት ፈፅመዋል፤ ህገወጥ ሰነድ አዘጋጅተዋል፣ የጦር መሳሪያ በድብቅ ይዘዋል” በሚል ክስ ፖሊስ ፍርድ ቤት አቅርቧቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የ28 ቀን ቀጠሮ ሰጥቶ ተጠርጣሪዎቹን ወደ ዕስር ቤት እንዲመለሱ አድርጓል፡፡

ከአስር ዓመታት በላይ በነፃ ሚዲያ ውስጥ በጋዜጠኝነት በመስራትና በማህበራዊ ድረ ገፅ የላቀ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ “የአዲስ አበባ ባላደራ ምከር ቤት በፀሐፊነት ሲያገለግል እንደነበር ይታወቃል:: ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የባልደራስ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ከስብሰባ ብኋላ ወደ ቤቱ በመሄድ ላይ ሳለ ምሽት 2፡30 ላይ አራት ኪሎ አካባቢ በደህንነት ሰዎች መያዙ ታውቋል፡፡

በሽብር የተከሰሱት የህሊና እስረኞች ስለታሰሩበት ሁኔታና አያያዝ ምክር ቤቱ ዘርዘር ያለ መግለጫ ይሰጣል ተብልኣል:: ባለአደራው ም/ቤት በባህርዳር ሰኔ 15 እና 16 ስለነበረው ሕዝባዊ ስብሰባ እና ሂደቱ በመግለጫው ማብራሪያ እንደሚሰጥ ታውቋል::

በተጨማሪም በአዲስ አበባና ኦሮሚያ በንፁሃን ላይ በቅንጅት እየተፈፀሙ ስለሚገኙት ህገ – ወጥ የእስር ዘመቻዎችና ሌሎችም ጉዳዮች ነገ ሐምሌ 3 ቀን ከጠዋቱ 4፡30 ላይ ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ከፍ ብሎ በሚገኘው የባለአደራው ም/ቤት ጽ/ቤት መግለጫ ይሰጣል፡፡

ሙያዊ ተሳትፎና አገራዊ ግዴታዎችን ባመነበት መንገድ ከመወጣት ውጪ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ንክኪ ኖሮት የማያውቀው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩን በዚህን መሰሉ የሽብርተኝነት ክስ ጠርጥሮ ታስሯል:: እስክንድር ነጋ ዛሬ ለአስራት ቴሌቭዥን በሰጠው ቃለ ምልልስ ባሕር ዳር ላይ የተከሰተዉ ክስተት ሙሉ ለሙሉ የኢህአዴግ የዉስጥ ጉዳይ መሆኑን አውስቷል:: በማያያዝም እስረኞቹ በየእስር ቤቱ የተያዙበት ሁኔታም እጅግ የሚያሳዝን መሆኑንና ከህወሃት ዘመን የሚብስ እንጂ የሚስተካከል አይደለም። ከማለቱም በላይ ወንድሞቻችን እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ላይ ነዉ የሚገኙት’ ሲል የእስረኞቹን አያያዝ አብራርቷል::

“እጅግ ጠባብ በሆነ፤ ምንም ብርሃን በሌለበት ጨለማ እና ቀዝቃዛ ክፍል፤ ከፈነዳ መፃዳጃ ቤት የሚወጣ ሽታን እየተነፈሱ፤ ኢ- ሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ላይ ነዉ የሚገኙት» ሲልም ታሳሪዎቹ ይገኙበታል ያለውን ሁኔታ ዘርዝሯል።

የኢህአዴግን ለበርካታ አምታት ሲጠቀምበት የነበረውን የምርጫ ሂደት አከርካሪ የሚሰብረው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

ከምን ግዜውም በላይ ነፃና ፍትሃዊ ይሆናል የተባለለት “ምርጫ 2012”ን በተመለከተ መንግስት ቃል በገባውና ምህዳሩን ለማስፋት ዕገዛ ያደርጋል የተባለው የምርጫ ሕግ ማሻሻያ ተጠናቆ ረቂቁ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቧል፡፡

በርካታ ማሻሻያዎችን የያዘው ረቂቅ አዋጅ ላለፉት በርካታ ዓመታት አወዛጋቢ ሆኖ የቆየው የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሥራቸው የሚያስተዳድሯቸው የንግድ ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎችን ጉዳይ መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል አማራጭ ይዞ መጥቷል፡፡

በዚህም መሰረት ረቂቅ አዋጁ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈቀዱ የገንዘብ ምንጮችን በግልፅ አስቀምጧል፡፡ እነዚህም ከአባላት የሚሰበሰብ የአባልነት መዋጮ፣ ምርጫ ቦርድ አጥንቶ በሚያስቀምጠው “ጣሪያ” መሰረት በኢትዮጵያውያን ወይም ኢትዮጵያውያን በሚቆጣጠሯቸው ኩባንያዎች የሚደረግ ስጦታና ዕርዳታ፣ በመንግስት ከሚሰጠው ድጋፍና ዕርዳታ፣ የገንዘብ አቅምን ለማጎልበት ከሚያግዙ የገቢ መሰባሰቢያ ዝግጅቶች ከሚገኝ ገቢ ብቻ መንቀሳቀስ እንደሚቻል ያስረዳል፡፡

ማንኛውም ሕጋዊ ሰውነት ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በንግድና ኢንዱስትሪ ስራዎች መሰማራት አይችልምም ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም ፓርቲ ካልታወቀ ምንጭ ወይም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የመንግስት ከሆኑ የልማት ድርጅቶች የሚቀርብ ስጦታና ዕርዳታን መቀበል አይቻልም ሲል ረቂቅ አዋጁ ይገድባል፡፡ ይህን በጣሰ መልኩ የተከለከለ ስጦታና ዕርዳታ የተቀበለ ፓርቲ ዕርዳታውን በተቀበለ 21 ቀናት ውስጥ ከተያያዥ መረጃዎች ጋር ለቦርዱ ገቢ የማድረግ ግዴታም አለበት፡፡

ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ በምርጫው መሳተፍ የሚችል ሲሆን በውጭ አገር በመኖራቸው ወይም በሌላ ምክንያት በአካባቢያቸው መምረጥ ለማይችሉ ዜጎች፣ በምርጫው የሚሳተፉበት ልዩ ሥርዓትን ምርጫ ቦርድ ሊዘረጋ እንደሚችልም ከወዲሁ ተነግሯል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ኮሚቴ ተመርቷል፡፡ አዲሱና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የምርጫ ሕግ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ የሚፀድቅ ከሆነ በበርካታ ቢዝነሶችና ኢንዱስትሪዎች ላይ የተሰማራው ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹ ወደ ትክክለኛና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ወደሚመጣጠን የኢኮኖሚ አቅም እንዲገቡ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ለኤክስፖርት ገበያ የተዘጋጀ 39.9 ሜትሪክ ቶን ቡና ከመነኪናው ተዘረፈ

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን የቡና ጥራት መስፈርት አሟልቶ፣ የጉምሩክ ፎርማሊቲውን አጠናቆ ወደ ጅቡቲ የተሸኘ 39.9 ሜትሪክ ቶን ቡና ከነመኪናው መዘረፉ ተገለጸ፡፡

“ኩሩ ኢትዮጵያዊ” ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ንብረት የሆነው 39.9 ሜትሪክ ቶን ቡና “የሲዳማ ደረጃ ሁለት የታጠበ ቡና” በሰሌዳ ቁጥር 3 – 25201 እና 3 – 06783 በሆነ ዋናና ተሳቢ ተሸከርካሪ ተጭኖ ለኤክስፖርት ገበያ ሊውል ወደ ጅቡቲ እየተጓዘ እንደነበር ታውቋል::

በሞጆና አዳማ መካከል ባለው የጉዞ መንገድ ላይ ከእነ ተሸከርካሪው እንደተወሰደ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትና ለጠ/ሚ/ር ቢሮ የተፃፈው፣ በድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አብዱራህማን ማህዲ የተፈረመው ሰነድ በግልፅ ያስረዳል፡፡

የቡናውን መዘረፍ ተከትሎ በተደረገ የፖሊስና የሕዝብ ትብብር ተሸከርካሪው በአዳማ ከተማ ሲገኝ፣ በመኪናው ላይ 5.514 ኪሎ ግራም ቡና ብቻ ሲያዝ ቀሪው ቡና ጠፍቷል፡፡ የቡናው አጠቃላይ ዋጋ 178.440 ዶላር እንደሆነ ከላኪው ድርጅት የወጣው ደብዳቤ ይፋ አድርጓል፡፡

የተዘረፈው ቡና የት እንደደረሰ ባይታወቅም አንድ ተጠርታሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሃገር ውስ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል::

በሐረር በተደራጁ ኃይሎች ሰፊ የመሬት ዝርፊያና ብዙ ሚሊየን ብሮች በካሳ እየተከፈሉ ነው

በሐረር ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 650 ሔክታር መሬት በተደራጁ ኃይሎች ሲዘረፍ፣ 56 ሚሊዮን ብር ደግሞ አግባብ ባልሆነ መንገድ በካሳ እንዲከፈል መደረጉ ታወቀ፡፡

በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሕገ – ወጥ ቤቶች ግንባታ እየተጥለቀለቀች ሲሆን በዛው መጠን የተደራጁ ኃይሎች የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን በጉልበት መንጠቅ፤ ቤተክርስቲያንና መስጊዶችን መድፈርም መደበኛ ስራቸው ሆኗል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ንቅናቄ ተከትሎ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ክልሉ የገቡ ታጣቂ ቡድኖችና የክልሉ ነዋሪዎች ሐረሪ ክልል መንግስት አልባ ከተማ እስክትመስል ድረስ ባለፉት ተከታታይ ወራት በርካታ ወንጀሎችን ፈፅመዋል፡፡ የሐረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አብዱላኪም ዩኒስ በስድስት ወር ውስጥ ከአንድ ሺኅ በላይ ቤቶች በሕገወጥ መንገድ መገንባታቸውንና ሀረማያ ዩንቨርስቲ ፍራፍሬ የሚያመርትበት ሴራት ፓርኪንግ መዘረፉን፣ በተጨማሪም የዕምነት ተቋማት በእነዚህ የተደራጁ ኃይሎች አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ እየተደፈሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

“የሚሰገድበትን መስጊድ ደፍሮ ቤት የሰራ እንዳለ እና በርካታ ግለሰቦችም ለፍተው የሰሩትን ቤት እንደተቀሙ ታውቋል፡፡ ገንዘብ ቆጥበው ኮንዶሚንየም ቤት የሰሩ መምህራንና ሠራተኞች ለአንድ ዓመት ተኩል ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገው፣ በቤቱ ውስጥ ሌሎች ሰዎች እንዲኖሩ ተደርጎ ነበር” ያሉት አብዱላኪም ዮኒስ በአሁኑ ሰዓት የክልሉ መንግስት ሕገወጦችን በማስወጣት የቤት ባለቤቶቹ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ከማድረጉ ባሻገር በተለያየ መንገድ ወንጀለኞችን የመቆጣጠር ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ
ገልፀዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ከከተማዋ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ጋር በተያያዘ በሁለት ዙር የሰላሳ ስድስት ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ተፈፅሟል፡፡ ከሐረር ከተማ 7 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው ጄኒሳ ወረዳ ልዩ ስሙ “ላንድ ፊል” በሚባል ስፍራ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሰኔ 2000 ዓ.ም ለአስር ዓመት የሚሆን ካሳ ተከፍሏቸው ነበር፡፡ ከአስር ዓመት በኋላ የአካባቢው ማህበረሰብ “የቆሻሻውን “ሽታ አልቻልንም፤ የሀረርን ቆሻሻ አንሸከምም” በማለታቸው በመጀመሪያ ዙር 16 ሚሊዮን ብር ካሳ ተከፍሏቸዋል፡፡ ራቅ ብለው የሚኖሩ ሌሎች ገበሬዎችም “እኛም ቆሻሻው ሸቶናል፤ ስለዚህ የጉዳት ካሳ እንፈልጋለን” በማለታቸው ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ ተፈፅሟል፡፡ ከውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘም እንዲሁ 23 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መከፈሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአምቦ እና የኮካ ውህደትን ፍርድ ቤት በድጋሚ አገደ

የኮካ ኮላ እናት ድርጅት በሆነው ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግና በአምቦ የማዕድን ውሃ ኩባንያ መሀል የተፈጠረውን ውህደት የሸማቾች ጥበቃና የንግድ ውድድር ባለስልጣን አስተዳዳራዊ ፍ/ቤት በይግባኝ አቤቱታ መሰረት በድጋሚ ቢመለከትም፤ የቀድሞውን ብይን በማፅናት ውህደቱ ሕገ ወጥ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ሁለቱ ድርጅቶች ጥር 2009 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ አዳራሽ ባካሄዱት አመታዊ ጉባኤ ሠራተኞቻቸውን ሰብስበው ውህደታቸውን ያለ ባለስልጣኑ ዕውቅና ይፋ አድርገው ነበር፡፡ በባለስልጣኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ከ30 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የንግድ ድርጅት ውህደት ከመፈፀሙ በፊት ለባለስልጣኑ እንዲያሳውቅ ይደነግጋል፡፡

ድርጅቶቹ አርማቸውን በማቀላቀል የኮካ ኮላ አከፋፋይ አምቦ ውሃን አብሮ እንዲያከፋፍል ማድረጉ፣ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ወደ አምቦ የማዕድን ውሃ አራት ሰራተኞቹን ማዛወሩ ይታወቃል:: ይህ አካሄድ ስህተት እንደሆነ ተጠቅሶ ለሁለተኛ ጊዜ በተላለፈውና አስር ወራት በፈጀው የዳኝነትና የምርመራ ሂደት መሰረት፤ የኩባንያዎቹ ውህደት ሕገ – ወጥ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም በማለት የከዚህ ቀደሙን የውሳኔ አፅንቷል፡፡

LEAVE A REPLY