ለማን ብየ ላልቅስ? || አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)

ለማን ብየ ላልቅስ? || አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)

“የገደለው ባልሽ፤ የሞተው ወንድምሽ!”
“ሃዘንሽ ቅጥ አጣ ምን ብየ ላላቅስሽ!”

“እኔ ለዐማራው ሕዝብ ህይወቴን ሰጥቻለሁ” ዶር አምባቸው መኮነን

የእኛ አገር ጉዳይ ቅጥ ያጣ ሆኗል። ወንድም ወንድሙን እንዲገድል ከጀርባ ሆኖ የሚቀሰቅሰው ማነው? የሚለውን ጥያቄ ለተመራማሪዎች ልተወው። የክልሉና የፌድራሉ ባለሥልጣናት ማን ገዳይ እና ማን ተገዳይ እንደሆነ ነግረውናል። ቁም ነገሩ፤ እነማን ናቸው ወይንም ከየትኛው ዘውግ ወይንም ጎጥ ናቸው አይደለም። ግድያውን በጎጥ መፈተሹ ራሱ አሳፋሪ ነው። ጎጣዊነትን ተጠቅሞ እርስ በርስ መወነጃጀሉ የሞቱትን ብቻ ሳይሆን የዐማራውንና የመላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝቅ አድርጎታል።

በአገር ወዳድነቱ ምንም እንከን የሌለው የዐማራው ሕዝብ ከሁሉም በላይ ለአገሩ ክብር፤ ነጻነትና ሉዐላዊነት መስዋእት ሲሆን ቆይቷል። ለጥቁር ሕዝቦች ያደረገውን አስተዋፆ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ጥቁርና ነጭ ጽሃፊዎች መዝግበውታል፤ አድንቀውታል። በዚሁ አስደናቂ ታሪክ ልክ ግን፤ ይህን ከሁሉም ዘውጎች ጋር ተዋልዶና ተከባብሮ የሚኖር ሕዝብ በጠላትነት የሚያወግዙትና የሚያሳድዱት የውጭና የውስጥ ጠላቶቹ ብዙ ናቸው።

የተቀነባበረና ያልተቋረጠ ሴራ

ይህ ትንተና ስለ ዐማራ ታሪክና ስለ ከፈለው ዋጋ አይደለም። ግን፤ አንባቢ እንዲያጤነው የምፈልግው አስኳል ጉዳይ፤ በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚካሄደው ግፍና በደል ዛሬ አለመጀመሩን ለመጠቆም ነው። የአውስትርያው ተወላጅና ዘረኛ ፕሮቻካ ሮማን (Prochaka Roman) the Abyssinia Powder Barrel, 1927 በጻፈው መጽሃፉ ላይ እንዳስቀመጠው የዐማራው ሕዝብ ራሱን ከፈረንጆች በታች አድርጎ የማይቀበል፤ በነጻነቱና በሉዐላዊነቱ የማይደራደር መሆኑን አስምሮበታል። ሆኖም፤ ፋሺስቶችና ናዚዝቶች፤ አስካሪዎችና ከሃዲዎች ይህን ሕዝብ እንደ ጠላት እንዲኮንኑትና እንዲጠፋ፤ ባይጠፋም እንዲሸማቀቅ አድርገው ያልተቆጠበ ፕሮፓጋንዳና ጦርነት አካሂደውበታል።

የኢትዮጵያ የውጭና የውስጥ ጠላቶች የዐማራውን ሕዝብ የሚጠሉበትና እንዲጠፋ የሚመኙት ለምንድን ነው? የዐማራው ሕዝብ የነጻነት፤ የአትንኩኝ ባይነት፤ የነጭ ሆነ የቢጫ ሕዝብ የጥቁር ሕዝብ የበላይ ዓይደለም፤ ሆኖም አያውቅም፤ እኔ ለቅኝ ገዢዎች አልንበረከክም ባይነት በነጮች በኩል ተቀባይነት አግኝቶ አያውቅም። ይህን አመለካከት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የናደው በአጼ ምኒልክ የተመራው የአድዋ ድል ነው። የአድዋ ድል ግን በተናጠል መታየት የለበትም። ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል፤ የራሷ የቀን መቁጠሪያ፤ የራሷ የመንግሥት ስርዓት ያላት አገር መሆኑና ጭንቀት እንደፈጠረ ማጤን ያስፈልጋል።

ይህ ታላቅነት ያልተዋጠለት ሙሶሊኒና ተባባሪ የነበሩት የአገር ውስጥ ከሃዲዎችና አስካሪዎች ኢትዮጵያ እንደ ገና እንድትወረር አድርገዋል። ይህ የመጨረሽ የውጭ ወረራ ግን አገሪቱ የጣሊያን አካል እንድትሆን አላደረጋትም። የሃበሻ ጀብዱ የተባለው አስደናቂ መጽሃፍ እንደሚያሳየው ለአምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ጀግኖች በዱር በገደሉ ጣሊያኖችን ተዋግተዋል፤ ጣሊያንን አሸንፈዋል።

ሆኖም፤ አሁንም ቢሆን ፋሽስቶችና ናዚዝቶች ተክለውት የሄዱት የዘውግ ጥላቻና የከፈፍለህ ግዛው ስልትና ስሌት መፍትሄ አላገኘም። ኢትዮጵያ ታላቅ አገር እንዳትሆን የሚፈልጉ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ዋና መሳሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት የዘውግና የኃይማኖት ልዩነት ፖለቲካን ነው። የዘውግ ፖለቲካን በዜግነት ፖለቲካ መቀየር የአገር ህልውና ጥያቄ ነው።

ግድያው አሳፍሮኛል። ያሳፈረኝና ያስፈራኝ ምን ጨካኝና አረመኔ ግለሰብ ወይንም ቡድን ነው ይህን ወንጀል የፈጸመው የሚለው ነው። ግለሰቡ ወይንም ቡድኑ ግደል እንኳን ቢባል፤ ወገኖቸን ብቻ ሳይሆን፤ አንድን ግለሰብ ያለ ምንምም ምክንያት፤ ሳይተኩስብኝ ሌላው ቀርቶ ድንጋይ ሳይወረውርብኝ አልገልም ሊል ይችል ነበር። ይህን የሚያደርግው ግን ለህሊናው የሚገዛ፤ ወንድሙን ኢትዮጵያዊውን የሚወድ፤ ለሕብረተሰቡና ለሃገሩ የሚቆረቆር፤ በገንዘብ ሆነ በሥልጣን ህሊናውን የማይሸጥ ሰው ነው። ወንድም ወንድሙን ሲገድል ተሸናፊ እንጅ አሸናፊ የለም። ተጠቂ እንጅ አጥቂ የለም። ፈሪ እንጅ ጀግና አይኖርም። ጥቂቶችም ብንሆን፤ ተማርን የምንለው በስደት የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ነጻነታችን እየተጠቀምን፤ ሃላፊነት የጎደለው የቃላት ጦርነት እያካሄድን ነው። ተጠቂውና ዋጋ ከፋዩ የዐማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና እናፈቅራታለን የምንላት ኢትዮጵያ ናት። ለአንድ ሰኮንድም ቢሆን፤ አእምሯችን ሰብሰብ አድርገን ለህሊናችን እንገዛ። ህወሓታዊ የጭካኔና ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያናክስ ስራ መስራትን እናቁም።

በቅንነቱ፤ በትሁትነቱና በአገር ውዳድነቱ የሚታወቀው ወንድማችን ዶር አምባቸው መኮነና ጓዶቹ ያለ ጊዜያቸው አልፈዋል። ኤታ ማጆር ሹሙ ጀኔራል ሰዓረ መኮነን መተኪያ  የሌለው የጦር መሪ፤ አስተማሪ፤ ከማንኛውም በላይ አገሩን አፍቃሪ፤ ጠባብ ብሄርተኝነትን ተቃዋሚ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አስቀዳሚ አጥተናል። እነዚህ ጀግኖች የሚታወቁት ዐማራ ወይንም ትግሬ ወይንም ድብልቅ በመሆናቸው አይደለም። በኢትዮጵያዊነታቸው ነው። ከእልፈታቸው በኋላ “የኔ ነው! የኔ ነው! የዚያ ነው! የዚህ ነው! እያልን ዝቅ የምናደርጋቸው እኛው ነን። ‘የኔና የአንተ’ የሚለውን የህወሓቶችን ፈለግ ተከትለን። እየተፈራረቁ መግዛትና መብላት ለኢትዮጵያ አሳፋሪ ነው። ህወሓት ለሃያ ስምንት አመታት በልቷል! ዛሬ ደግሞ የኔ ፋንታ ነው! የሚሉትን የኦነጎችንና መሰሎቻቸውን ብሂል እየተከተልን ሁኔታዎችን ማባባሱ መቆም አለበት።

ሴራና ድንገተኛ አደጋ የተለያዩ ናቸው

በእኔ ግንዛቤና ዘገባ፤ ግድያውና “መፈንቅለ መንግሥቱ” በደንብ ታስቦበት፤ ብዙ ወጭ ተደርጎበት የዐማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ተተኪ መሪዎች እንዳይኖሯት፤ ለውጡ እንዳይሳካ የተደረገ ሴራ ነው። ሴራው እንዳይታወቅ ከተፈለገ ወንድም ወንድሙን እንዲገድልና እርስ በእርሳችን እንድንወነጃጀል ማድረግ ስልት ነው። የስድሳ ስድስቱን “አብዮት” ጭካኔ ብቻ ዞር ብሎ መገምገም ይጠቅማል።

እኔን እጅግ የሚያሳስበኝ፤ የሞቱትን አገር ወዳዶችና ጀግኖች ቀብረን ገና ሃዘናችን ሳንጨርስና ከሞታቸው ምን እንማራለን ብለን ሳንመራመር፤ የመሳፍንት ዘመን መሰል ቲያትር እያካሄድን ነው። ጎንደሬውና ጎጃሜው የእርስ በርስ ጦርነት እያካሄደ ነው። ወሎየውና ጎንደሬው እርስ በርሱ እየተወነጃጀለ ነው። የሸዋውና የሌላው ዐማራ እነዚህ “እብዶች እርስ በርሳቸው መናከስ ልምዳቸው ነው” የሚል መሃል ሰፋሪ ይመስላል። የሲዳሞ ወገኖቻችን የራሳችን ክልል ያስፈልገናል እያሉ ያስፈራራሉ። የክልል ድንበሩ የት ላይ ነው? ይህ አመለካከት አፍራሽ ነው።

ጀኔራል ሰዐረ መኮነን ነፍሳቸውን ይማርና ልንመራበት የሚገባን ትምህርት ለግሰውን አልፈዋል፡ “ጠላቶቻችን የሚጠቀሙብን በክልል ማሰብ ስንጀምር ነው።” ጎጠኝነት ደግሞ የሞት ሞት ነው። ዛሬ እኛ ኢትዮጵያዊያን ቀን ከሌት መስራት ያለብን ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ማዳን ነው። ይህን ለማድረግ የምንችለው ደግሞ ከዘውግ በላይ “መንፈስና ሱስ ነው” ተብሎ በሚታወቀው በኢትዮጵያዊነት ስንሰበሰብና ስንተባበር ነው።

በግድያውን ማን ተጠቃሚ፤ ማን ተጠቂ ሆነ?

ግድያውንና “መፈንቅለ መንግሥት” ተብሎ የሚጠራውን ክስተት በተመለከተ አጥጋቢ የሆነ መረጃ የለም። ሁሉም እንደፈለገው ከባርኔጣ “ሃቅ ነው” ብሎ የሚያስበውን በመገናኛ ብዙሃን እያሰራጨ ሕዝቡ እርስ በእርሱ እንዲጠራረር በክሎታል። የዚህ ዋና ተጠቃሚ ኃይሎች በአገር ውስጥ ህወሓት፤ ኦንነግ፤ የብሄር ጽንፈኞችና የተወሰኑ ነጋዴዎች ናቸው የሚለውን እጋራለሁ። በውጭ ግብጾችና ሌሎች በኢትዮጵያ ላይ እቅድ ያላቸው መንግሥታትና ኢንቬስተሮች ናቸው። የተቀነባበረውን የሳይበር ጦርነት የሚያካሂደው ቡድን ህወሓት ነው። ህወሓት የዘረጋ እረጂም ክንድ፤ የካድሬዎች ሰንሰለትና መዋቅር ገና አልፈረሰም።

ስለዚህ፤ የትግላችንና የጉዟችን ኢላማው የዐብይ መንግሥት ሊሆን አይችልም። የአፈጻጸም ድክመቶች ያሉት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የዐብይ ቡድን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጠበቃና ተከላካይ ነው። ኢላማው የህወሓት ሰንሰለትና መዋቅር እንዲፈርስ ማድረግ ነው። በተመሳሳይ፤ ኦነግና መሰል ድርጅቶች የህወሓትን መስመር ተከትለው ሊያደርጉ የሚሞክሩት ግፍ፤ በደልና ዘረፋ እንዲቆም መተባበር ነው። በተጨማሪ፤ ጃዋር ሞሃመድ መለስን ተክቶ ሕዝብ ከሕዝብ፤ ኃይማኖት ከኃይማኖት ጋር እንዲጋጭ እየታገለና እየሰበከ ነው።

ጃዋር አደገኛና አገር አፍራሽ መሆኑን የሚያመለክቱ ብዙ መረጃዎች አሉ።

  • በማያገባው ጣልቃ ገብቶ የዐማራው ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲናከስ ካደረጉት ሰዎች መካከል አንዱ እሱ ነው። ለምሳሌ፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አድርጎ ራሱን በመሾም የዐማራውና የቅማንቱ ወንድማማች ሕዝብ እንዲናከስ ቅስቀሳ አድርጓል። የወሎን ክፍለ ሃገር የኦሮምያ አካል ነው ብሎ ተናግሯል። ይህ ሴራ፤ የዐማራው ህዝብ ጎንደሬ፤ ወሎየ፤ ጎጃሜ፤ ሸየ ወዘተ በሚል መለያ ተለያይቶ መንደር የሚያክሉ፤ አቅም የማይኖራቸው ለተስፋፊነት የሚበጁ “ንኡስ ክልሎችን” ለመፍጠር ነው። በዐማራው መቃብር ላይ ታላቅ ሌላ አገር ለመመስረት የሚደረግ ሴራ ነው።
  • ይህ ግለሰብ የራሱን መንግሥት እንደመሰረተ ሆኖ ይሰብካል፤ ይንቀሳቀሳል። እድል በሚሰጠው በማንኛውም ሜድያ እየገባና በፖለቲካ ምህዳሩ ቤንዚን እየረጨ፤ጎራዴ ምዘዙ እያለ፤ ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ የደም ምድር እንድትሆን ይናገራል፤ ይቀሰቅሳል። ከተቻለ “በሕገ-መንግሥቱ፤ አለያ በኃይል” የሚል የብሄር ጽንፈኛ፤ የኃይማኖት አክራሪ ከብሄርተኛውና ከዘረኛው ከህወሓት በምን ይለያል?
  • ጃዋርን የቅማንት ሆነ የወሎ ሕዝብ፤ የሲዳማ ሆነ የአዲስ አበባ ሕዝብ ጠበቃ አድርጎ የሾመው ማነው? ይህ ግለሰብ በሃላፊነት መጠየቅ አለበት።
  • ጃዋር ከኸርማን ኮህን ጋር ይመሳሰላል። ሁለቱም የዐማራውን ሕዝብ አውግዘው፤ ዐማራው ለ500 ዓመታት ገዝቷል የሚል ከእውነቱ የራቀ ዘገባ እያቀረቡ ዐማራው ለባሰ አደጋ እንዲጋለጥ እያደረጉት ነው።
  • በቅርቡ ስለ ሲዳሞ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ሲናገር፤ ጃዋር በቀጥታ ኢላማ ያደረገው የዐብይን ፌደራል መንግሥትና አስተዳደር ነው። ይህ አቋም ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶችና ከህወሓት ሴራ በምኑ ይለያል?

ግድያውና “መፈንቅለ መንግሥቱ” ምን ፋይዳ አለው? ህወሓቶች፤ የተወሰኑ የዘውግ ልሂቃኖች፤ ጃዋር መሰሎችና የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች የሚከተሉትን ስኬታማ አድርገዋል። ይህ የአጭር ጊዜ ድል ግን የከስራል።

  1. የማህበረሰባዊ ሜድያና የሳይበር ስፔስ ጦርነቱ በዐማራው ሕዝብ ላይ ያተኮረ ሆኖ፤ የእርስ በእርሱ ጦርነት በጎጠኝነት ዙሪያ እንዲካሄድ መደረጉና ዋናው ችግር እንዳይፈታ መሰናክል መሆኑ፤
  2. ይህ በዐማራው ክልል መንግሥት ዙሪያ ያለው የእርስ በእርስ ሹክቻና የሥልጣን ግብግብ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለመላዋ ኢትዮጵያ የጸጥታና የአገር ህልውና ተግዳሮቶች ግብዓት መስጠቱ፤
  3. በአማራው ወጣት ትውልድ ድርጅቶች ለምሳሌ በአብን፤ በፋኖና በሌሎች እንቅስቃሴዎችና በዐማራው ዲሞክራቲክ ፓርቲ መካከክል ያለው ግንኙነት አሁንም ጤናማነትና ተደጋጋፊነት አለማሳየቱ፤
  4. ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ ስልጣን ከያዙበት ወቅት በኋላ በተከታታይ በሁሉም የዐማራ ክልል ከተማዎችና የትምህርት ተቋማት ለዐብይ ለውጥ ይደረግ የነበረው የማያሻማ ድጋፍ ወደ ጥርጣሬና ትችት መሸጋገሩና የዚህ ሂደት ዋና ተጠቃሚ ህወሓት መሆኑ፤
  5. የዐማራው ክልል አመራር የዐማራውን ሕዝብ “ዘላቂ ጥቅምና የህልውናውን ጥያቄ ዋና መርህ አድርጎ በማስተጋባት ፋንታ የዐብይ ደጋፊ ሆኗል” የሚለው በመረጃ ያልተደገፈ ብሂል መዛመቱ፤
  6. ለዚህ ክስ ግብዓት የሆኑት የቡራዩ ግድያ፤ የሰሜን ሸው ወረራ፤ የለገጣፎ ዜጎች መፈናቀል፤ የቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ የዐማራ ሕዝብ ግድያ፤ በራያን አዜቦ ቢያንስ የ 2,000 ዐማራ ወጣቶች በህወሓት ታፍነው ትግራይ ተወስደው መታሰራቸው ጉዳይ አለመፈታት፤ የወልቃይት ጠገዴ፤ የራያና አዜቦ፤ የመተከል ጉዳዮች ምንም አይነት መፍትሄ ያለማግኘታቸው ጉዳይ፤ በአዲስ አበባ የተቋቋመው “የባለአደራ ም/ቤት” አቋም በአግባብ ያለመታየቱና “ወገንተኛነትና አድልዎ ያሳያል” የሚለው ጥርጣሬ፤ በመቀሌ መሽጎ የሚገኘው “ለወንጀለኞች” ምሽግ ሆኗል የሚለው አመለካክት ምንም አይነት መፍትሄ አለማግኘቱ፤ የኦሮሞ ልሂቃንና ጃዋር “ወሎ የኦሮምያ አካል ነው” ማለታቸው፤ ልዩ ልዩ ክሎሎች የተለያዩ የፌደራል መንግሥት አስተዳደርና ውሳኔ ያሳያሉ የሚለው ዘገባ መኖሩ፤
  7. ጎንደሬው “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ብሎ በአማራው ክልል ያካሄደው ትግል ተዛምቶ ለለውጡ ፋና ወጊ መሆኑ እየታወቀ ይህን ቀስቃሽ አስተዋፆ የማኮላሸት ፕሮፓጋንዳ መካሄዱ፤ ለውጡ ሕዝባዊ መሆኑ በተቋማትና በአመራር ገና ስር አለመስደዱ፤ ኢትዮጵያዊ መዋቅር አለመያዙ፤
  8. በግድያውና “በመፈንቅለ መንግሥቱ” ሰበብ የአብንና የባለአደራው ም/ቤት አባላት “በሽብርተኛነት” መከሰሳቸውና ይህ ሂደት ህወሓት መራሹ አገዛዝ በኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ የበላይነት ተተክቷል የሚል ክስና ወቀሳ ማስከተሉ፤
  9. ጠ/ሚንስትሩ ሚዛናዊ አቋም አይወስዱም የሚለው አመለካከት መዛመቱ፤ ለምስሌ፤ ጃዋር የሚናገረውና የሚሰራው ጽንፈኝነትና አክራሪነት ትኩረት ሳይሰጠው በጋዜጠኛ እስክንድር ላይ ግን ትችት መሰንዘሩ፤
  10. ጠ/ሚንስትሩ የሚታወቁበትና የሚለዩበት የሰብአዊ መብቶችና የመገናኛ ብዙሃን መብትና ነጻነት መከበር ጉዳይ “እየተናደ ነው” የሚለው ብሂል የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡና በመታገቡ ጥርጣሬ መከሰቱ፤
  11. ጸረ-ኢህአዴግነትና አማራጮችን ማቅረብ ለፌደራሉ መንግሥት ተግዳሮት መሆናቸው፤
  12. በዘውጋዊ አድልዎ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ህወሓት መራሹ ቡድን ከስልጣን ከወረደ በኋላ በልዩ ልዩ ተቋማት በሞያ ብቃትነት (Competency and merit) ሳይሆን በዘውግና በታማኝነት ብቻ የፌደራል ስልጣን እየተሰጠ ነው የሚለው ብሂል መዛመቱ፤
  13. አሁንም ቢሆን እንደ ቀድሞው ህወሓት መራሹ ስርዓት፤ የዐማራው ሕዝብ “ጨቋኝ፤ ቀመኛ፤ ነፍጠኛ፤ ቅኝ ገዢ” ወዘተ በሚል ፕሮፓጋንዳና ለፈፋ እንዲጋለጥ እየተደረገ ነው የሚለው ሰፊ አመለካከት መኖሩ፤ ህወሓትና ኦነግ ይህን አመለካከት አለም አቀፍ በሆነ ትብብር ማስተጋባታቸውን መቀጠላቸው፤
  14. በኦሮምያና በሌሎች አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሃያ የሚደርሱ የባንክ ቅርንጫቾችን ዘርፈው ዘራፊዎቹ በሃላፊነት ለሕግ አለመቅረባቸው የሕግ የበላይነት የሚለው አስፈላጊ መርህ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አይስተናገድም የሚለው ብሂል በሶሻል ሜዱያ መሰራጨቱና መፍትሄ አለማግኘቱ፤
  15. ህወሓትና ሌሎች ኃይሎች ስልኮችን እየጠለፉ በኢንተርኔትና በሌሎች መገናኛ ዘዴዎች በዐማራው ክልል አመራርና በተራው ሕዝብ ላይ፤ በዐብይ የለውጥ አመራር ብቃት ላይ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በየአካባቢው ሲያዛምቱ ይህን የሳይበር ጦርነት የፌደራሉ መንግሥትና “ተፎካካሪ” ነን የሚሉት ልሂቃንና ምሁራን ለመቋቋም አለመቻላቸው ሁኔታውን ማባባሱ፤
  16. የዐማራው ሕዝብ “ታሪካዊ ጠላታችን” ነው የሚሉ ኃይሎች መገናኛ ብዙሃን እየተጠቀሙ፤ እንደ ኸርማን ኮህን ካሉ ለኢትዮጵያ መፈራረስ ከፍተኛ አስተዋጾ ካደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር ቁርኝት በመፍጠር ይህ አገር ወዳድ ሕዝብ ራሱን ቀና አድርጎ ለራሱ ህልውና፤ ለአገሩ ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት ወሳኝ ሚና እንዳያይጫወት የፕሮፓጋንዳ ጦርነት መጀመሩ፤
  17. በዐማራውና በኦሮሞው ሕዝብ መካከል የተፈጠረው ጠንካራ ግንኙነት በፈጠራ ወሬ እንዲኮላሽ ለማድረግ የኃይማኖትና የመሬት ይገባኛልነት (ወሎ ምሳሌ ነው) መስመሩን እንዲስት መደረጉ፤
  18. አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ምሁራንና ሌሎች በኢትዮጵያ አማራጭ የለም፤ ያለውን አመራር ብቻ መደገፍ አስፈላጊ ነው እያሉ የሚናገሩት ሕብረተሰቡን የሚከፋፍል እመለካከት መዛመቱ። ይህ አመለካከት የኢትዮጵያን 110 ሚሊየን ሕዝብ መናቅ ከመሆኑም ባሻገር፤ ኢትዮጵያ ያላትን የተማረ ሰው እንዳትጠቀም ማድረጉ፤ አማራጭ መስጠት አሁንም እንደ ጠላትነት መቆጠሩ፤
  19. በተለይ በዘውግ ሳይሆን በዜጎች መብት ላይ የተመሰረተ የህገ መንግሥትና ሌላ የፖሊሲ አማራጭ ለመስጠት አለመድፈራችን ሁኔታውን ማባባሱ፤ እና፤
  20. ውይይቱ፤ ክርክሩና ድርድሩ የኦሮሞን፤ የዐማራንና የትግራይን ሕዝብ ብቻ እንደሚመለከት ሆኖ መቅረቡ ይገኙበታል። ይህ አመለካከት ሁሉን አቀፍ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያዊነት እንዲጠነክር ከተፈለገ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳታፊና ባለቤት መሆን አለባቸው።

ይህን አመልካች ስእል ለማጠቃለል፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን አስፈላጊ ሰላማዊና ዲሞክራሳዊ ለውጥ ለማብረድ ሳይሆን ፈጽሞ ለማጥፋት የሚታገሉ፤ የውጭ ድጋፍ የሚሰጣቸው የተባበሩ ኃይሎች እንዳሉ ይታያል። ምንም እንኳን አስተማማኝ መረጃዎች ለማግኘት ባልችልም፤ ስህተቶችም አሉ የሚለውን ብቀበልም፤ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ የሚመራው ለውጥ ስኬታማ እንዲሆን ከመተባበር ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። ግድፈቶችን ጨዋነት ባለው መልኩና አማራጮችን በመጠቆም እያስተጋባን ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንዳይጋጭ ማድረግ ታሪካዊ ግዴታችን ነው። በለይ ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለማዳን ያልተቆጠበ ጥረት ካላደረግን ይህችን ታሪካዊ አገር ልናጣት እንችላለን።

በዐማራው ክልል፤ በባህር ዳር የተካሄደው ጭካኔን የሚያሳይ ግድያ የጠላቶች ሴራ እንጅ የወንድማማቾች ሴራ ሊሆን የሚችልበት ምንም መስፈርት ላገኝ አልቻልኩም። ግን፤ ግድያው ወደ አሳፋሪ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። ይህ የጎጠኞችና የቀን ጅቦች የሚመስል የጥቅም ጦርነት ወደ ጎጥ ዝቅ ያለ መወነጃጀል ቀስ በቀስ ወደ ሩዋንዳ መሰል፤ ወደ ሶሪያ መሰል፤ ወደ የመን መሰል፤ ወደ ሶማሊያ መሰልና ወደ ሱዳን መሰል አደገኛ እልቂት (Genocide) እና ኢትዮጵያን ወደማትመለስበት መፈራረስ (Balkanization) እንድታመራ እያደረገ ነው።

እኔ አገሬን ካየኋት፤ በተለይ የጎንደርን አካባቢ ሕብረተሰብ በቀጥታና በአካል ባየሁት ሁኔታ መስፈርት ከገመገምኩት ከአርባ ሁለት ዓመት በላይ ሆኗል። የማውቀውና የማስታውሰው የዐማራው ሕዝብ እንኳንና የራሱን ወገን የማረከውንም ፈረንጅ ሰብእናና ህይዎት የሚያከብር፤ ኃይማኖቱና ባህሉ አእምሮውንና ስራውን እንዲያመዛዝን የሚያስገድድ ህብረተሰብ መሆኑ ነው ትዝ የሚለኝ። የዐማራ ወንድ አባቱን ወይንም ወንድሙን ወይንም ልጁን ወይንም ሚስቱን ገዳይ አይምርም። ንጹህ ደም ማፍሰስ ግን ነው ሲባል ነው የማስታውሰው።

የፈለገውን ያህል ብንጮሕና ብናለቅስ ኢትዮጵያ ያፈራቻቸውን፤ መተኪያ የማይገኝላቸውን ወንድሞቻችን የገደሉትን ግለሰቦች ከጀርባ ሆኖ ማን እንዳዘጋጃቸው አናውቅም። የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ክትትል፤ ጥናትና ምርምር ይደረጋል ቢልም የምናምንበት መስፈርት የለንም። ከዚህ በፊት በጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ምን ላይ ደረሰ፤ ማነው ከጀርባ ሆኖ ያቀነባበረው፤ ማን በሃላፊነት ፍርድ ቤት ቀርቧል?

ታላቁ የተሃድሶ ግድብ ኢትዮጵያ ከጀመረቻቸው መሰረተልማቶች መካከል አንደኛውን ደረጃ የያዘ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ግዙፍና መለያችን የሆነ ሃብት ነው። ይህን ወደ አምስት ቢሊየን ዶላር የሚፈጅ ግንባታ አቀናብሮ ይሰራ የነበረው ኢትዮጵያዊው መሃንዲስ ስመኘው በቀለ “ራሱን ገደለ” ተብሎ ሲነገር ለአገራችን መንግሥትና ሕዝብ አፈርኩ። ይህ መሃንዲስ ራሱን የሚገልበት ምክንያት የለም። ብዙ ቢሊየን ዶላር በሚሰረቅባት ኢትዮጵያ ሌቦችና ተባባሪዎች ቢገድሉት ሊታመን ይችላል። ቁም ነገሩ፤ ኢንጅኔር ስመኘው “ራሱን ገደለ” ከሚለው ውጭ የኢትዮጵያ መንግሥት ፋይዳ ያለው መግለጫ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አላቀረበም።

ህወሓቶች በድብቅ ተቃዋሚዎቻቸውንና ተፎካካሪዎች ናቸው ብለው የሚጠረጥሯቸውን ሁሉ፤ በተለይ ዐማራዎችን በስውር እንደሚገድሉ የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህ ስልት የሚጠቀሙ ሌሎችም ኃይሎች አሉ። ልዩ ልዩ የሚገድል መርዝና መድሃኒት በምግብና በመጠጥ እየጨመሩ የድብቅ ግፍ የሚሰሩ አሁንም አሉ። ጋዜጠኛውና አገር ወዳዱ አቶ ደምሴ በለጠ አገሩን ለማየት ሄዶ አዲስ አበባ “ባልታወቀ ምክንያት” ከዚህ ዐለም ተለይቷል። ይህን አገር ወዳድና ጀግና እኔም አውቀዋለሁ። ጤናማ ነበር። እንዴት እንደሞተና ማን እንደገደለው እስካሁን አይታወቅም። ስለዚህ፤ ምርመራ ቢካሄድም ሃቁን ለማወቅ አይቻልም ያልኩበት ምሳሌዎች ስላሉ ነው።

እኛ ልምዳችን ጀግኖቻችን የምናስታውሳቸው ካለፉ በኋላ መሆኑ ማቆም አለበት። ጀግኖቻችን በህይወት በነበሩበት ጊዜ ምን አይነት ድጋፍ ሰጠናቸው? የሚል ጥያቄ ብንጠይቅ ይጠቅማል።

ካለፉት መተኪያ ከሌላችው ኢትዮጵያዊያን መካከል የማውቀውና ለጥቂት ደቂቃዎች ያነጋገርኩት ዶር አምባቸው መኮነንን ብቻ ነው። ይህ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ “ህይወቴን ለአማራው ሕዝብ ሰጥቻለሁ” ብሎ ለቤተሰቡ ፍቅር ቅድሚያ ሳይሰጥ በለጋ እድሜው አልፏል። አቶ ገዱ እንዳስቀመጠው፤ “ከዚህ በላይ ሞት የለም። እውነትና ንጋት እያደር ይጣራል” እንዲሉ፤ ምን አልባት የዚህ አገር ወዳድና ጨዋ ኢትዮጵያዊ ገዳዮችም የሚታወቁበት ጊዜ ሊመጣ ይችል ይሆናል። ቁም ነገሩ ግን እሱና ጓዶቹ፤ እሱና ጀኔራል ሰዓረ መኮነን ለምን አላማ ቆመው ነበር የሚለው ነው።

  • ለፍትህ፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤
  • ለሕግ የበላይነት፤
  • ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት ወዘተ የቆሙትን ነው ኢትዮጵያ ያጣችው።

እኔ ለዶር አምባቸው ባለውለታው ነኝ። ባላውቀው ይሻለኝ ነበር። ምክንያቱም፤ ትህትናው፤ ፈገግታው፤ አገር ወዳድነቱ፤ ጨዋነቱ፤ ለዐላማ ያለው ቆራጠኛነቱ ስለሳቡኝ ሌላ ጊዜ አገሬ ስመለስ በሰፊው አነጋግራለሁ ካልኳቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘው እሱ ነበር። የሚያውቁት ሁሉ የሚሉት ተመሳሳይ ነው። ይህ ወንድማችን ለሰላምና ለአብሮነት የቆመ ግለሰብ ነበር። ይህን ባለውለታችን የሌለ ስም እየሰጠን ስንከሰው ያመኛል። መስዋእት ከሆነው ወንድማችን፤ ከጓዶቹና ከጀኔራል ሰዐረ መኮነን በመማር ፋንታ ራሳችን ዝቅ አድርገን መንደርተኛ ስንሆን ያማል፤ አጸያፊ ባህርይ ነው። ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጋር አብሮ የማይሄድ ነው። ዛሬም እንደ ወትሮው ልዩነትን በመሳሪያና በግድያ እንፈታለን የሚል ግለስብና ቡድን እብድ ነው። እብድ ህክምና ያስፈልገዋል። ሆነ ብሎ ያበደን ደግም በማባበል፤ በመምከርና በህክምና ለማዳን አይቻልም። ለዚህ ነው በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች ቀይ መስመር መወሰን አለባቸው እያልኩ የምከራከረው።

ለማጠናከር፤ የሕግ የበላይነት ወሳኝ ከሆነ፤ በክልል ደረጃ ሆነ በፌደራል ኢትዮጵያ ቀይ መስመር እንዲኖራት ያስፈልጋል። በቃ! ከዚህ ባሻገር አንታገስም የሚል መስመር ማለቴ ነው። ዶር አምባቸውንና ጓዶቹን፤ ጀኔራል ሰዐረ መኮንን የገደሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። ሁኔታውን የሚያባብሱና የፈጠራ ወሬ የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች በየትኛውም ዓለም ይኑሩ የተሳሳተ ወሬ ማሰራጨት እንዲያቆሙ ለሚኖሩበት መንግሥት በመረጃ የተደገፈ ክትትል እንዲደረግባቸው ጫና ማድረግ ያስፈልጋል።

የዐማራው ሕዝብ በመንደር ደረጃ ዝቅ ብሎ ህወሓት መራሽ የሆነውን ጎንደሬ፤ ወሎየ፤ ጎጃሜ፤ ሃረሬና ሌላ መለያ እየያዘ የመከፋፈል ዘመቻውን በአስቸኳይ ማቆም አለበት። ይህ እርግማን ነው። አባቶቻችን ትተውልን ከሄዱት እሴት ጋር አይመጣጠንም።

መለያየቱና መወቃቀሱ፤ መካሰሱና መወነጃጀሉ፤ በአጭሩ መንደርተኛነቱ ምን ፋይዳ አለው? በእኔ እምነት፤ ብሄራዊ ሃዘናችንን ወደ ብሄራዊ ውርደት አሸጋግረነዋል። ይህ ውርደት የሚያስከትለው አደጋ ምንድን ነው? ብለን ራሳችን እንጠይቅ። ኢትዮጵያ ሩዋንዳን ብትሆን፤ ኢትዮጵያ ዩጎስላቭያን ብትሆን ማንም ተጠቃሚ እንደማይኖር አሳስባለሁ። የሞቱት ወንድሞቻችን ኢትዮጵያዊያን ናቸው። የተጎዳችውና የምትደማው ኢትዮጵያ ናት። ከጀርባ ሆኖ ግድያውን ያካሄደው ኃይል ዐማራውንና ኢትዮጵያን የሚወድ አይደለም፤ ጠላት ነው። ለለውጡ ዋና መሰናክል ነው።

ዲያስፖራውን ስመለከት የምመክረው ሕዝቡን ከእልቂት፤ አገሩን ከመፈራረስ ለመታደግ የተቀነባበረ ዘመቻ ማካሄድ ታሪካዊ ግዴታችን የሚል ነው። ከእያንዳንዱ ዘውግ፤ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድሙ እንዳሉ አምናለሁ፤ ተስፋ የሚሰጡኝ እነሱ ናቸው። ኢትዮጵያ በተከታታይ የውጭ ጠላት ወሯት አሸንፋለች። የጉዲትን፤ የግራኝ ሞሃመድን እልቂት አልፋለች። ወደፊትም አትፈርስም።

አንዱ ብሄር ወይንም ዘውግ ከሌላው ጋር እንዲጋጭ የሚያደርጉ ኃይሎችን ለማሸነፍ እንችላለን፤ ከተባበርን። መጀመሪያ ግን ብሄር ተኮር ጥላቻና ዘመቻ የሚያካሂዱ ኃይሎችን ባለን አቅም መታገልና ማጋለጥ አለብን። የዐማራውና የኦሮሞው ሕዝብ እንደ ብረት የጠነክረ ግንኙነት እንዲጠነክር መታገል አለብን። ህወሓት የትግራይን ሕዝብ አይወክልም ለማለትና ደፍረን ሕዝቡ ሌላውን ወንድሙን እንዲቀላቀል፤ ለውጡን እንዲደግፍ ተደጋጋሚ ጥሪ ማድረግ አለብን። ህወሓትን ሆነ ጃዋርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽብርተኛ ቡድን ነው ብለን የምናጋልጥበት ወቅት አሁን ነው።

በዐማራው ክልል የተካሄደው ግድያ መወነጃጀልን አስከትሏል። መጠንቀቅ ያለብን ግን መረጃ ሳይኖረን ወገንተኛ መሆናችን እናቁም። አናውቅም፤ መረጃ የለንም ለማለት እንዴት አንችልም? እኛ ኢትዮጵያዊያን በማናውቀው ጉዳይ ላይ መፍረድ ይቀድመናል። እባካችሁ ይህን መጥፎ ባህል እናቁመው። ጠ/ሚንስትሩ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵይዊነትን እንደሚያስቀድም አምናለሁ። ግዙፍ ተግዳሮት ደግሞ እንደገጠመው አያለሁ፤ እሰማለሁ።

ግን ዐብይ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት አልቆመም የሚል የተሳሳተና ሃላፊነት የጎደለው ነገር ሲነገር ልክ የዶር አምባቸው ሞት እንደሚያመኝ ሁሉ ይህም ሃሜት ያመኛል።

ለማጠቃለል፤ እኔ ለዶር አምባችው ከዶር ንጉሴ ነጋ ቤት ተገናኝተን ሹክ ያልኩት “ከማንኛውም ስራ በፊት ቅድሚያ መስጠት ያለብህ፤ የዐማራው ሕዝብ ራሱን ቀና እንዲያደርግና በወንድማማቹ በአማራውና በትግራዩ ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ወሳኝ ስለሆነ ስራየ ብለህ አጠናክረው” የሚል ነበር። ለዚህ ምሳሌ የጠቀስኩለትና አቶ ገዱንም አደራ ያልኩት በአማራውና በኦሮሞው ሕዝብ መካከል የተደረገው ታሪካዊ  የወንድማማችነት ጅማሮ እንዲጠናከር ነበር። በዚህ ቅንና “ለዐማራው ሕዝብ ህይወቴን ሰጥቻለሁ” ብሎ ቃል ለገባው ወንድማችን የሚገባውን እውቅና እንስጠው። ኃውልት ይሰራለት፤ መንገድ ይሰየምለት። ለጀኔራል ሰዐረ መኮነንም እንደዚሁ። እኛ ጀግኖቻችን ህያው እናድርጋቸው።

“ቅጥ ያጣው ሃዘናችን” ፋይዳ የሚኖረው በሰከነ አእምሮ የሞቱትን ወንድሞቻችን ዓላማ ስናጤነውና እነሱን የሚተኩ መሪዎች ቦታቸውን እንዲይዙ ተመክሮ በመስጠት ነው። ሰብሳቢው መርህ መሆን ያለበት የሞቱት ጀግኖቻችን ምን እሴትና መርህ፤ ምን አደራ ትተውልን አለፉ? የሚለውን ጥያቄ በጋራ ለማስተጋባት ቆርጠን ስንነሳ ነው።

በአካል ባላውቃቸውም፤ የዐማራው ክልል ፖለቲካ ፓርቲ የበላይ አመራር አባላት፤ ወጣቶቹ አቶ ምግባሩ ከበደና አቶ አዘዘው ዋሴ ከአጋር ወንድማቸው ከዶር አምባቸው ጋር አብረው አልፈዋል። እነዚህ ወጣት መሪዎች የተገደሉበት ዋና ምክንያት፤ የዐማራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ መሪዎች እንዳይኖሯት የሚያደርግ ድርጊት ነው። ወይንም፤ ሆነ ተብሎ የዐማራው ሕዝብ መሪ አልባ እንዲሆን ታስቦበት የተፈጸመ ሴራ ነው።

ዛሬ እኛ ኢትዮጵያዊያን ቀን ከሌት መስራት ያለብን ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ማዳን ነው። ዶር አምባቸውና ጀኔራል ሰዐረ መኮን አልፈዋል።

የማያልፍ ታሪክ መስራት ያለብን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መአከልአድርገን ለውጡ በማንም የውስጥና የውጭ ሴራ እንዳይቀለበስ ማድረግ ነው።

ኢትዮጵያ ሃገራችን ለዘላለም ትኑር!!

የኢትዮጵያ ሕዝብ እኩልነት ይለምልም!!

LEAVE A REPLY