በበረዶ ሰልፍ ወጥቼ፣ ጠላትን በአደባባይ አውግዤ
አገር ነፃ ወጥታ፣ እኔም ነፃ ልወጣ፣ እፎይ ልል ተስፋ አርግዤ
ባንዲራዋን ተጠቅልዬ፣ ከፍ አድርጌ ተሸክሜ
ገጿ ባክኖ ቢርቀኝም፣ የሷን ምስል ልቤ አትሜ
በየመንገዱ ግርጌ፣ በየቢሮው ደጃፍ ድኼ
ቀን ለፈረንጅ ጆሮ፣ ማታ ለጭንቅ አማልጇ ጮኼ
ሰሚ አጥቼ እይዝ እጨብጠው ሳጣ
እመብርሃን ደርሳ ገዥው ተግበስብሶ ሲወጣ
እሰይ! ብዬ መሬት ስሜ ቀና ሳልል
የልብ ውሌን ደጇ ሄጄ ስለት ሳልጥል
“ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥ!”
ብዬ ያልኩት ቃሌ ሳይደርስ
ባቡር ወጥቶ ሳይመለስ
ካኅን ቅዳሴ ሳይጨርስ
ተሿሚው በመንበሩ ሳይደላደል
ተሻሪው በትረ ዘንጉን ከእጁ ሳይጥል
ገና የሟች ደም ሳይጠረግ
የግርፋት ቁስል ሳይጠግግ
ዓባይ እንደደፈረሰ
ጣና እንቦጭ እንደለበሰ
የተበተነው ተሰብስቦ ሳይገባ
ጉምና ጭጋግ እንደለበሰች አዲስ አበባ
የማንነቷ እጣ ሳይጣል
በአፍ ቅብብል ስትዋልል
የቀን ጅብ እንደተቀናጣ
መብራት እንኳን ዙሩ ሳይመጣ
ደግሞ ደፈረሰ ሰልፍ ልውጣ!
|| welelaye2@yahoo.com ||