ኢሕአዴግ ራሱን ችሎ ይወድቅ ይሆን? || በፍቃዱ ኃይሉ ለዶይቸ ቬለ

ኢሕአዴግ ራሱን ችሎ ይወድቅ ይሆን? || በፍቃዱ ኃይሉ ለዶይቸ ቬለ

ለዶይቸ ቬለ ከምልካቸው መጣጥፎች መካከል የበኩሬ በሆነው እና “የኢሕአዴግ ‘ዳግማይ ትንሳዔ’ ወይስ ‘ዜና እረፍት’?” የሚል ርዕስ ሰጥቼው የነበረው ጽሑፍ ላይ፥ ‘አሮጌው ኢሕአዴግ’ ሞቶ ‘አዲሱ’ መወለዱን ተናግሬ ነበር። ይሁንና ከዓመት በኋላ ያንን ድምዳሜዬን የሚያስገመግም ፖለቲካዊ ለውጥ ተከስቷል። አምና ኢሕአዴግ ከጥቂት አባላቱ በቀር በጅምላ ይቅርታ አግኝቶ ነበር፤ አሁን ‘ዓይንህን ላፈር’ የሚሉት እየበዙ ነው። አምና እምነት ሰጪዎቹ እና ተስፈኞቹ ብዙ ነበሩ፤ ዛሬ ተጠራጣሪዎቹ እና ድንጉጦች በዝተዋል። አምና የግንባሩ አባል ድርጅቶች እየተጎሻሸሙም ቢሆን ኅብረታቸውን እንደጠበቁ ነበር፤ ዘንድሮ ግን “አብረን ለመሥራት እንቸገራለን” እየተባባሉ ነው።

በተለይም የመጨረሻው በሕወሓት እና በአዴፓ መካከል ተራ የግለሰቦች ብሽሽቅ የሚመስለው እና የሁለቱ ክልሎች – ትግራይ እና አማራ – ገዢ ፓርቲዎች የተለዋወጧቸው የመግለጫ ኃይለ ቃሎች ፓርቲዎቹን ራሳቸው እንደሚሉት “እህትማማቾች” ሳይሆን፥ ለጦርነት የሚፈላለጉ ጠበኞች አስመስሏቸዋል።

ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ እና አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አሁን ዛቻ እና ማስፈራሪያውን ይፋ አወጡት እንጂ በሐሳብ ደረጃ እንደተጣሉ ግልጽ ነበር። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መምጣት እና “የለውጡ ኀይል” ለሚባለው ቡድን መወለድ መንሥኤ ነው ተብሎ የሚጠቀሰው የኦሮማራ (የኦሮሞ እና አማራ ጥምረት) በርግጥም የሕወሓትን የበላይነት ለማዳከም ኦዴፓ እና አዴፓ (በቀድሞ ሥማቸው ኦሕዴድ እና ብአዴን) የፈጠሩት ንቅናቄ ነበር። እነሆ ተሳክቶላቸው ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ መገለል ደርሶብኛል የሚለውን ሕወሓት አገሪቱ ውስጥ ለተከተለው አለመረጋጋት ተጠያቂ እያደረጉ ከርመዋል። ሆኖም ግንባሩ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች ተቋቁሞ እስከዛሬ ዘልቋል። ይህ ግን ለወደፊቱም ይዘልቃል ማለት አይደለም።

የኢሕአዴግ መፍረስ ምልክቶች

ኢሕአዴግ የተመሠረተው በሕወሓት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በትጥቅ ትግሉ ወቅት የበለጠ ድል እያስመዘገበ የነበረው ሕወሓት ኢሕዴን (የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ይባል የነበረውን ብአዴን እንዲሆን በማድረግ እና የኦሕዴድን መመሥረት በማገዝ የኋላ ኋላም የዛሬውን ደኢሕዴንን (ያኔ የተለያዩ ፓርቲዎች ግንባር የነበረ ፓርቲ) በማሰባሰብ ኢሕአዴግ በሚል መጠሪያ ኢትዮጵያን ከ1983 ጀምሮ ገዝቷል። ይሁንና ሕወሓት በመሠረተው ኢሕአዴግ ውስጥም ይሁን በብዙኀኑ ዘንድ ያልተመጣጠነ የሥልጣን የበላይነት በማከማቸት ሲታማ ኖሯል።

ኢሕአዴግ በ2010 ውስጣዊ ለውጥ በማምጣት ጊዜያዊም ቢሆን ሕዝባዊ ቅቡልነት ያስገኘለትን ለውጥ ሲያካሒድ የገዛ አባል ፓርቲውን ሕወሓትን በመውቀስ ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከመጡ በኋላ ሕወሓት ኢሕአዴግ ውስጥ ብቸኛ ሀጢያተኛ ተደርጎ መሣሉ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ተቃዋሚዎችም ይህንን ሁኔታ “የጠላቴ ጠላት” በሚል መርሕ ተቀብለው ከቀሪዎቹ የኢሕአዴግ እህት ፓርቲዎች ጋር ስልታዊ ወዳጅነት ጀምረዋል። የፖለቲካ አሰላለፎችም በብዙ መልኩ ተቀይረዋል። አዲሱ ኢሕአዴግ ይህንን ተቀባይነቱን እና አዲሱን የፖለቲካ አሰላለፍ ይዞ ለመቀጠል ሲል ሕወሓትን እያገለለ መቀጠሉ ስለማይቀር ከመሥራቹ (እናት ፓርቲው ሕወሓት) የተለየው ኢሕአዴግ በግንባርነት ይቀጥላል ብሎ ማለት ይቸግራል። በዚህ ላይ በሕወሓት እና አዴፓ መካከል ያለውን ግብግብ ስንጨምረው ቢያንስ ግንባሩ ቢቀጥል እንኳን ሕወሓት የሌለበት ግንባር ሆኖ ይቀጥላል የሚል መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን።

የኢሕአዴግን መፍረስ የሚያመላክተው ሌላኛው ምልክት የደቡብ ክልል ለመበታተን መዘጋጀቱ ነው። በቅርቡ ከታየው የፖለቲካ ለውጥ ወዲህ በደቡብ ክልል በርካታ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ማንሳታቸው ይታወቃል። እነዚህ ፓርቲዎች የራሳቸውን ክልል መመሥረት የሚችሉ ከሆነ፣ በጋራ ደኢሕዴን የሚለውን ፓርቲ ይዘው በመቀጠል ፈንታ የየራሳቸውን ክልላዊ ፓርቲ ይዘው የሚቀጥሉ መሆኑ አያጠራጥርም። እነዚህ አዳዲስ ፓርቲዎች የኢሕአዴግ አባል ሆነው የሚቀጥሉበት ዕድል ያለ ቢሆንም፥ ከኢሕአዴግ ያፈነገጡ ድርጅቶች ሊሆኑ የሚችሉበትም ዕድል አለ። ደኢሕዴን በተለይም የሲዳማ አባላቱ እያፈነገጡ ስላስቸገሩት ብቻ መደበኛ ስብሰባውን በክልሉ ዋና ከተማ – ሐዋሳ ላይ በማካሔድ ፈንታ አዲስ አበባ ላይ ለማካሔድ መገደዱ ይታወቃል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውሕድ ፓርቲ የመመሥረት ሕልም ሌላኛው የኢሕአዴግ ግንባር መፍረስ አይቀሬ መሆኑን አመላካች ነው። ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ ሥራው ባይጀመርም እና አባል ፓርቲዎቹ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስቡ ማወቅ ባይቻልም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጪው ምርጫ አስቀድመው ክልላዊ ፓርቲዎችን እና ግንባራቸውን በማፍረስ ኢሕአዴግን አገር ዐቀፍ ውሕድ ፓርቲ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው በይፋ ተናግረዋል። ይህ ንግግር፣ መቼም ተፈፀመ መቼ የኢሕአዴግ ፍፃሜ አይቀሬ መሆኑን ያመላክታል።

ኢሕአዴግ ቢፈርስ ምን ችግር አለው?

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ትንታኔ የሚጽፉት ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ሬኔ ሌፎርት በሚያዝያ ወር በጻፉት መጣጥፋቸው “ተወደደም ተጠላ፣ ኢሕአዴግን ሊተካ የሚችል ኃይል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ በአሁኑ ሰዓት የለም። በኢሕአዴግ ውስጥ ሥነ ስርዓት መልሶ ማስፈን ለየትኛውም ጠቃሚ ንቅናቄ መፈጠር እንደ ቅድመ ሁኔታ አስፈላጊ ነው። ከዚህ ቀውስ ውስጥ ፈጣን እንዲሁም ነጭ ወይም ጥቁር የሚባል መፍትሔ አይገኝም፤ በርካታ ግራጫማ እና የተለያየ ደረጃ ያላቸው ማስተካከያዎች እንጂ” ብለው ነበር። አሁንም እየታየ ያለው ይኸው ነው።

በኢሕአዴግ ውስጥ ኅብረት መጥፋቱ በየክልሉ ለፉክክር የጦር ጉሰማ መጦፍ፣ መንግሥታዊ ላልሆኑ ኀይሎች መፈርጠም፣ ግዙፍ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ለመሸሸግ አልፎ ተርፎም ለስርዓተ አልበኝነት እና የአገር እና የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ ለሚጥል ሁኔታ በር ከፍቷል። ኢሕአዴግ በመንግሥት እና በገዢው ፓርቲ መካከል ያልተፈለገ ውሕደት እንዲፈፀም በማድረጉ ሳቢያ ፓርቲው ሲከፋፈል፣ አገሪቷም እንድትከፋፈል፤ ከዚህም በላይ ፓርቲው ሲፈርስ አገሪቷን አብሮ ሊያፈርስ የሚችል ስጋት እንዲጋረጥባት አድርጓል።

ኢሕአዴግ እንደ ግምባር በጋራ የፈጠረውን ችግር በጋራ ለመፍታት ፈቃደኛ አልሆነም። ይልቁን በግለሰቦች ብሽሽቅ እና ኩራት ምክንያት የብዙኀኑን ጥቅምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ሌላ አዲስ ገጽታ ያለው ችግር ፈጥሯል። ይህንን ችግር ለመፍታት አባል ድርጅቶቹ በጥሞና የሚያስቡበት ጊዜ አሁን ነው። ግንባሩ የሚፈርስም ቢሆን እንኳን ራሱን ችሎ በመፍረስ የአገሪቷን ብሎም የምሥራቅ አፍሪካን ዕጣ ፈንታ ከፓርቲው ጋር እንዳያበላሽ አባላቱ ከዚህ በላይ ሳይረፍድ ሊያስቡበት ይገባል።

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የዶይቸ ቬለ (DW)ን አቋም አያንጸባርቅም።

LEAVE A REPLY