ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም

ዜና ኢትዮጵያ ነገ || ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም

የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ የለማቸውን ሃዋሳን መጥቅለል ታስቦ ነው ተባለ

 እስከ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ጥያቄያችን ምላሽ ካላገኘ በራሳችን መንገድ ክልል የመሆን መብታችንን እናስከብራለን ከሚለው  ከሲዳማ ክልል ጥያቄ ጀርባ በአሁኑ ሰአት በከፍተኛ ልማት ላይ የምትገኘውን ሃዋሳ ከተማን በብቸኝነት የመጠቅለል እሳቤ በመኖሩ ነው ሲል ስዩም ተሾመ ገለጸ፡፡

የሲዳማ ሕዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ማቅረብ ሕገ መንግስታዊ መብቱ ነው የሚለው አክቲቪስትና መምህር ስዩም ተሸመ ነገር ግን ሲዳማዎች ጥያቄ ሲያቀርቡ በመጀመሪያ ደረጃ በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆችን መብት በሚገድብና በሚገፍ፣ ሰላምና ደህንነታቸውን በሚነሳ መልኩ መሆን የለበትምብሏል፡፡

በሲዳማ ብቻ ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ፣ በፌደራል መንግስት በጀትና ድጎማ፣ በፌደራል መንግስት ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች የደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች በጀት፣ ድጋፍ፣ ሐብትና ጥሪት የለማችው ሃዋሳን የመቀራመት አዝማሚያ መኖር እንደሌለበት የሚናገረው ስዩም ተሾመ፤ አሁን ያለው ከክልሉ የሚሰማው ጥያቄና ስሜት እንዲህ አይነት ገጽታ እንደያዘና ይሄ ደግሞ ትልቅ ስሕተት እንደሆነ ከግዮን መጽሔት ጋር ባደረገው ቆይታ ላይ ገልል፡፡

በጅምላ የታፈሱት የኦሮሞ ተወላጆች በአምቦ “ሰንቀሌ” ወታደራዊ ካምፕ ታስረዋል

  ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በጅምላ እየታፈሱ ወደ አምቦ ከተማ ለእስር አየተጓዙ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግስት በአማራ ፣ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ የተጠናከረ የእስር ዘመቻ የጀመረ ሲሆን፤ በአዲስ መልክ እየተካሄደ በሚገኘው እስር የሚያዙ ሰዎች በጨቋኙና አላስፈላጊው የሽብርተኝነት ክስ እየተከሰሱ ፍ/ቤት መቅረባቸው ስርዓቱ ወደ ኋላ ከመመለስ ባሻገር አምባገነን እየሆነ መጥቷል የሚሉ ትችቶችን እንዲያስተናግድ ዕድል ፈጥሯል፡፡

“በጂማ፣ነቀምት፣ ሐረር፣ ጉጂ፣ ሆለታና በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የሚገኙ ከአንድ ሺኅ በላይ የሚሆኑ ደጋፊዎቻችንና አባሎቻችን ታስረውብናል፡፡ የሚገኙበትንም ሁኔታ ለማወቅ አልቻልንም፤ ቤተሰብም እንዳይጠይቃቸው ፍቃድ ተከልክሏል፡፡” ያሉት የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦ.ፌ.ኮ) ለቀ መንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና እነዚህ መንግስት “በኦነግ ሸኔ” አባልነት ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸውን ግለሰቦች በጅምላ እያፈሰ አምቦ አካባቢ የሚገኘው “ሰንቀሌ” ወታደራዊ ካምፕ ውስጥከቤተሰብና ከአካባቢ አርቆ እንዳሰራቸው ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ለመንግስት ቅሬታቸውን በገለጹበት ወቅት የጅምላ እስሩ እንደሚቆምና “መንግስት ከዚህ በኋላ እያጣራ ያስራል” የሚል ምላሽ ቢሰጣቸውም እስካሁን ድረስ በጅምላ የማፈስ ተግባሩ እንዳልቆመና ተጠናክሮ  እንደቀጠለ ይፋ አድርገዋል፡፡

መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በሕይወት አለ፤ ትከሻው ላይ በጥይት ተመትቶ አምልጧል

 የቀድሞው የአየር ኃይል ተዋጊ ጀት አብራሪ የነበረውና ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአማራ መብት ተሟጋች በመሆን የትግል ጎራውን የተቀላቀለው መቶ አለቃ ማስረሻ  እንዳልሞተና በሕይወት እንደሚገኝ ከደረሰን ዜና ለማወቅ ተችሏል፡፡

 ለዓመታት ዕስር የዳረገውና ከአየር ኃይል አብራሪነቱ እንዲነሳ መንስኤ የሆነው “በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አማራን አግላይና ተንበርካኪ የሚያደርግ እንቅስቃሴ በገዢው ስርዓት ውስጥ በግልጽ ይንጸባረቃል” የሚሉ ተደጋጋሚ አስተያየቶችን በመስጠቱ እንደሆነ የሚናገረው ማስረሻ ሰጤ ከሌሎች ሶስት አብራሪዎች (የአማራ ተወላጆች የሆኑ) ጋር ለዕስር ተዳርጎ ነበር፡፡

 ማስረሻ ሰጤ ላይ ከተመሰረተበት መደበኛ ክስ በተጨማሪ በጎንደር ተቀስቅሶ የነበረውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ “የቂሊንጦ ቃጠሎን” ሆን ብሎ አስነስቷል፣አስተባብሯል በሚል የፈጠራ ክስ በሕወሓት መራሹ መንግስት አማካይነት ሀሰተኛ ፋይል ተከፍቶበት ብዙ መከራና ግፍ ተፈጽሞበት ነበር፡፡

የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግስት የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን መፍታት ሲጀምር በይቅርታና ምህረቱ ተጠቃሚ የሆነው መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ዘግየት በሎም ቢሆን ከዕስር ሊለቀቅ ችሏል፡፡ ማስረሻ ሰጤ ከወህኒ ቤት ከወጣ በኋላ ባሉት የመጀመሪያ ወራት በአዲስ መልክ እንዲዋቀር የታሰበውን የቀድሞ መ/ቤቱ አየር ኃይልን እንዲቀላቀል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግስት ይፋዊ ጥሪ ቀርቦለት ነበር፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ለመንግስት ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ግን ብዛት ያላቸው ታዋቂ የአማራ ብሔረሰብ አክቲቪስቶችና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አ.ብ.ን) ከፍተኛ አመራሮች ጥሪውን እንዳይቀበል የሚገፋፉ ዘመቻዎችን በማሕበራዊ ሚዲያዎች ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡ ከአስር ወር በፊት መቶ አለቃ ማስረሻ ማስረሻ ሰጤ ዳግም ወደ አየር ኃይል ለመመለስ መዘጋጀቱን ተከትሎ በአማራ አክራሪ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ጌታቸው ሽፈራውና ክርስቲያን ታደለን የመሳሰሉ ወጣቶች “ ጠ/ሚ/ር  ዐቢይ አሕመድ ለአማራ ሕዝብ ብዙ መስራት የሚችለውን መቶ ማስረሻ ሰጤን ወደ አየር ኃይል በመውሰድ አማራን እያዳከሙ ነው” የሚሉ ግልጽ ጽሑፎችን በፌስ ቡክ ገጾቻቸው በተደጋጋሚ በመጻፍ የአማራ ሕዝብ በማስረሻ ሰጤ ላይ ግልጽ ግፊት እንዲያደርግ ዓይነተኛ ሚና መጫወታቸው አይዘነጋም፡፡

 በዚህን መሰሉ ጉትጎታ የጠ/ሚኒስትሩን የአየር ኃይል ግብዣ የሰረዘው ማስረሻ ሰጤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአክራሪ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴን ተቀላቅሎ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የ”ግንባር ስጋ” ሲሆን ታየቷል፡፡ በተለይም ከጀነራል አሳምነው ጽጌ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመስረቱ በአማራ ሕዝብ ትግል ውስጥ አዲስ አቅጣጫን እንዲከተል ያደረገው መሆኑን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡

ማስረሻ ሰጤ በክልሉ ከአማራ ብሔርተኝነትና ከኃይል እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ እንዲሁም በቤኒሻንጉል በተፈጠረው ግጭት ላይ  እጁ አለበት በሚል ፌደራል ፖሊስ ሊይዘው ወደ ክልሉ ቢጓዝም ጀነራል አሳምነው እሱንና ሌሎች ግለሰቦችን አሳልፌ አልሰጥም ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ሰኔ 15 ቀን በባህርዳር ከተማ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ ተባባሪ ነው በሚልም መቶአለቃ ማስረሻ ሰጤ በጸጥታ ኃይሎች ለቀናት ያለበት ሲታሰስ ቆይቷል፡፡

ረቡዕ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ከተደበቀበት ቦታ (ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር በመሆን) ወደ ጎንደር ለመሄድ ሲሞክር መረጃው ከደረሳቸው የጸጥታ አካላት ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በጥይት ተመትቶ ሊቆስል ችሏል፡፡ በነበረው ድንገተኛ የተኩስ ለውውጥ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ከደረቱ ከፍ ብሎ ቀኝ ትከሻው አካባቢ በጥይት ቢመታም በነበረው ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ ታግዞ ሊያመልጥ ችሏል፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ ማሕበራዊ ድረ ገጾች መሞቱ ሲነገር ቆይም ዛሬ ማለዳ (ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ) ከቅርብ ቤተሰቦቹ ባገኘነው ትክክለኛ መረጃ መሰረት የቀድሞው የአየር ኃይል በሕይወትና በመልካም ጤንነነት ላይ ይገኛል  ተብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስሩ ጥቂት የማይባሉ ታጣቂዎችን ይዞ  ሲንቀሳቀስ የነበረው መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ለጊዜው ከጸጥታ ኃይሎች ቢያመልጥም በቀጣይ ይሕ ስህተት እንዳይደገም ይመስላል መከላከያ ሠራዊቱ አካባቢውን ዙሪያውን አጥሮ ጠንካራ ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ማስረሻ ወደ ጎንደር የመግባት ዕቅድ ነበረው፡፡ በርግጥም እንዳሰበው ግለሰቡ አምልጦ ጎንደር ከገባ ለመያዝ አስቸጋሪ ስለሚሆንና ምናልባትም ከአገር ለመውጣት ስለሚችል ወታደሮ የጎንደር መግቢያና መውጫውን ከበው የሚሆነውን በጥንቃቄ እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡                        

ዘመነ ካሴና አስቻለው ደሴም ከነታጣቂዎቻቸው እየታሰሱ ነው

    የሰኔ አስራ አምስቱን የአማራ ክልል ባለስልጣናትና በአዲስ አበባ የተከናወነውን የጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙን ተከተሎ እጃቸው አለበት በሚል ከተጠረጠሩትና የብ/ጀነራል አሳምነው ጽጌ ቀኝ እጅ ናቸው የሚባሉት ዘመነ ካሴና አስቻለው ደሴ በመከለከያ ሠራዊት እየታሰሱ እንደሚገኙ የዜና ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡

  በተጠቀሰው ቀን የጀነራል አሳምነው ቡድን በከተማዋ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ለመቆጣጠር በተንቀሳቀሰበት ወቅት በተቃራነው የተኩስ ልውውጥ በማድረግ አመጹን ሲያከሽፉ ከነበሩት ጥቂት የክልሉ ፖሊስና ልዩ ኃይል አባላት የተደረገውን ፍልሚያ ሲመሩ የነበሩት አስቻለው ደሴና ዘመነ ካሴ መሆናቸውን ዘግየት ብለው ከደረሱን  መረጃዎች ለማወቅ ችለናል፡፡

  እነዚህ በአማራነታቸው ብዙ ግፍና በደል የተፈጸመባቸው፣ ዘግናኝ የሚባሉ ኢሰብኣዊ ጥቃቶች ቀደም ሲል ስልጣን ላይ በነበረው አካል የደረሰባቸው ግለሰቦች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአማራን መብት ያስጠብቃል ባሉት የኃይል እንቅሳቃሴ ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ በተለይም ዘመነ ካሴ በዚህ ሂደቱ ፌደራል መንግስቱ በቁጥጥር ስር ሊያውለው በዝግጅት ላይ እንደነበርም ይታወቃል፡፡

  በርካታ የአማራ ወጣቶችን በማስታጠቅና በስሩ በማደራጀት የሚታወቀው አስቻለው ደሴ ሰኔ 16 ቀንና ሰኔ17 ቀን በተደረጉ  የተኩስ ልውውጦች ተመትቶ ሕይወቱ እንዳለፈ ቢወራምበተለያዩ መንገዶች ባደረግነው ማጣራት እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰበትና ከነተከታዮቹ በሕይወት እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል፡፡

  በሰኔ አስራ አምስቱና ተከታይ ቀናት በተደረጉ ፍልሚያዎች ከባድ መሳሪያ (ላውንቸር) ይዞ በአይን እማኞች የታየውና በአሁን ሰአት ”ጫካ ገብቷል” የሚባለውን የጀነራል አሳምነው ጽጌን ቡድን እየመራ የሚገኘው አስቻለው ደሴና ሌላኛውን አስተባባሪ ዘመነ ካሴን ለመያዝ ፌደራል ፖሊስና  መከላከያ ሠራዊት በጋራ ከፍተኛ አሰሳ በተለያዩ ቦታዎች እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

 እንደ ዜና ምንጮቻችን ጥቆማ በተለይም በሁለቱ ግለሰቦች ትውልድ ስፍራ፣ በቅርብ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው መኖሪያ አካባቢ፣ እንዲሁም ሊደበቁና ሊሸፍቱ ይችሉባቸዋል በሚባሉ ቦታዎች ያልተቋረጠ አሰሳ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከቀናት በፊት ከሁለቱም ቤተሰቦች አራት ያህል ግለሰቦች በፖሊስ ተይዘው የነበረ ቢሆንም ከሶስት ቀናት ዕስር በኋላ ሊፈቱ ችለዋል፡፡              

LEAVE A REPLY