የጄነራሉ የነፃ እርምጃ አዋጅ || ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

የጄነራሉ የነፃ እርምጃ አዋጅ || ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

በመከላከያ ሚኒስቴር የኢንዶክትሬኔሽን ዳይሪከቶሬት ዳይሪክተር ሜ/ጄ መሀመድ ተሰማ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ይታወቃል፡፡ በርካታ ጉዳዮችንም አንስተው ለማብራራት ሞክረዋል፡፡

በርግጥ የጄነራል መሀመድ መልዕክት ማጠንጠኛ የ‹መከላከያን ስም የሚያጠፉ›፣ ‹አመራሩን እና ሰራዊቱን ለማራራቅ የሚያሴሩ› ጋዜጠኞች እና ሚዲያዎችን ሰራዊቱ አሳድዶ በነፃ እርምጃ እንዲደመሰስ መፈቀዱን ‹ማብሰር› እንደ ነበረ ፕሮግራሙን የተከታተሉ በሙሉ የሚረዱት እውነታ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩ የተቋሙ መሪዎች በአደባባይ (በሚዲያ) ሲነገሩ ያልተደመጡ ክብረ-ነክና ኃይለ ቃሎችንም ተጠቅመዋል፡፡

‹ዋልታ ቲቪ› እንደ ሌሎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሳይቆራረጥ ሙሉውን ባስተላለፈው የጄነራሉ መግለጫ ላይ የ‹ፍትሕ መጽሔት› ማኔጂንግ ኤዲተር ተመስገን ደሳለኝን አራት ጊዜ በስም ጠቀሰው በተራ ቃላቶች ከመሳደብ እና ከመዝለፍም በዘለለ፤ ‹የተናደደ ወታደር ለሚወስደው እርምጃ ኃላፊነት የለብንም› በሚል ሽፋን ሰራዊቱ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስድበት የግላጭ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ መከላከያ ሠራዊት የዜጎችን አንገት መቀንጠስ እንደሚችል በይፋ አስረግጠዋል፡፡ ጉዳዩን አስገራሚ ያደረገው ደግሞ በሕግ ለመጠየቅ ዝግጅታቸውን እየጨረሱ እንደሆነ በመናገር በፍትሕ ስርዓቱ ላይ መሳለቃቸው ነው፡፡

ጄነራሉ ጋዜጠኞችን እና ሚዲያዎችን በጅምላ በስሁት ፖሮፓጋንዳ ለማሸማቀቅ መሞከራቸው ሳይዘነጋ፤ እንደ ቀይ እና ነጭ ሽብር ዘመን ነፃ እርምጃን ለሚመሩት ሠራዊት መፍቀዳቸው ከአንድ ግለሰብ ነፍስ በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ወታደሩ የፈለገውን እርምጃ ወስዶ፣ ‹መናደዱን› እንደ ምክንያት መጥቀስ ብቻ በቂ ነው በሚል ጄነራል መዳፍ ላይ የአገሪቱ ዕጣ-ፋንታ ወድቋል፡፡ ሁነቱ የፍትሕ ሥርዓቱን የናቀ፣ ለራሱ ለመንግሥትም ስጋት የሚፈጥር፣ ሀገራዊ ቀውስ የሚያነብር፣ ለፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ መግፍኤ የሚሆን አደገኛ አደጋ የተሸከመ ነው፡፡ የጄነራል መሀመድ አካሄድ፣ የጄነራል ሰዓረ ገዳይ ምናልባት ከደረሰበት ጉዳት መዳን ከቻለ እና ፍርድ ቤት ከቀረበ ‹ሰዓረን የገደልኩት ስላናደደኝ ነው› የሚል ቃል ሰጥቶ በነፃ መሰናበት የማለት ያህል ነው፡፡ ‹የጋዜጠኛ ደም ከወታደር ይቀጥናል› ካልተባለ፡፡ ይህንን ጉዳይ ከግድያው አኳያ ተቋሞ ሰፋ ያለ ምርመራ እንዲያደርግበት ይመከራል፡፡ (ጄነራሉ የአክራሪ ሽብርተኞችን አሰራር በመዋስ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ሰራዊቱ ባገኘው ቦታ እርምጃ እንዲወስድበት ያስተላለፉት መልእክት የተቋሙን አመራሮች በተመለከተ ከዚህ ቀደም ያዘጋጀናቸውን ዘገባዎች እውነታነት የሚጠናክር እንደሆነም ልብ ይሏል)

በጥቅሉ የጄነራል መሀመድ ተሰማ መልዕክት ‹የአገሪቱን ሕግ በግላጭ የናደ› ብቻ ተብሎ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በርከታ የታፈኑ እውነታዎች መኖራቸውንም ይጠቁማል፡፡ በተለይ የተወሰኑ የጦር መኮንኖችን ተንተርሶ በሕዝባችን ዘንድ በስፋት ሲወሩ የነበሩ አደገኛና ሕገ-ወጥ ተግባሮች ለመፈፀማቸው ምልክት የሰጠ ነው፡፡ የሃላፊው ንግግር እግረ መንገዱን ተቋሙ ‹አስተዳድረዋለሁ› የሚለውን ሰራዊት ‹ንዴት› መቆጣጠር እንደተሳነው፣ ዲስፒሊን እንደጠፋ፣ ሕግ የሚያከብር ወታደር እንደሌለ ከመመስከሩም በላይ፤ አገሪቷ ያለችብትን የፍርሰት ጠርዝም ጠቁሞ አልፏል፡፡

ጄነራል መሀመድ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በ‹ተናደዱ› እና በ‹ተበሳጩ› ቁጥር በፈለጉት ዜጋ እና ግብር ከፋይ ተቋማት ላይ እርምጃ የመውሰድ መብት ማን እንደሰጣቸው ግልጽ ባያደርጉም፣ የሕግ የባላይነትን የገረሰሰ፣ የመንግሥትን ህልውና የካደ፣ ሥርዓት አልበኝነትን የፈቀደ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው አከራካሪ አይደለም፡፡ በአገሪቱ ሕግ ተመዝግቦ እና ፍቃድ ተሰጥቶት በሚሰራ ሚዲያ ላይ በታተመ ሂስም ሆነ፣ በተጋለጠ መረጃ ‹ጉዳት ደረሰብኝ› ባይ አሳማኝ ማስረጃ እስካቀረበ ድረስ በፕሬስ አዋጁ›ም ሆነ በ‹ወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ› ፍትሕ ማግኘት እንደሚችል በዝርዝር መቀመጡ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ጄነራል መሀመድ እንደ ቀይና ነጭ ሽብር ዘመን ሰራዊቱ በ‹ተበሳጨ› ቁጥር ነፃ እርምጃ እንዲወስድ መንግሥታዊ ሚዲያዎችን ተጠቅመው ፍቃድ እስከ መስጠት መድፈራቸው ከኢትዮጵያውያንም ባሻገር አለም አቀፍ ማኀበረሰቡን ጭምር አስደንግጧል፡፡ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሲ.ፒ.ጄ እና የሰብአዊ መብት ተከራካሪው አምንስቲ መግለጫውን በቅድሚያ ያወገዙ ኢንተርናሽናል ተቋማት ናቸው፡፡

ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ደሞዝ የህይወት መስዋእትነትን በሚጠይቅ ሙያ የተሰማራውን፣ ችግር ያቆራመደውን፣ በአድሎኛ አዛዦች የተገፋውን ሰራዊት፣ ‹ገመናዬ ተጋለጠ› በሚል ግላዊ-ሰበብ በመሀል ከተማ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የፈቀደውን እርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ (ማነሳሳት) በነፍሰ-ገዳይነት የሚያስጠይቅ ከባድ ወንጀል በመሆኑ፣ የመከላከያ ኃላፊዎች የጄነራል መሀመድ አቋም ተቋሙን የማይወክል እና ያልመከሩበት ከሆነ የፋሽስት ኢጣሊያ ወኪል ጄነራል ግራዚያኒ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ያወጀውን አይነት ነፃ እርምጃ በፈቀዱት ጄነራል ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታቸውን በመወጣት ሊያረጋግጡልን ይገባል፡፡

በተጠላው እና መከራን ባዘነበው ዘመነ-ሕወሓት የነበሩ የጦር መኮንኖች እንኳ ቢያንስ በሚዲያ ይህንን የመሰለ ድፍረት እና ማን-አህሎኝነት ሲያሳዩ አልተመለከትንም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱን ለአልቦ-መረጋጋት፣ ሕዝብን ለሰቆቃ የዳረገውን አይነት የመንጋ ፍርድ ከደርግ እስከ ኢሕአዴግ ካገለገለ ወታደር የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ (ጄነራል መሀመድ ተሰማ በኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመን ኢትዮጵያን ከሻዕቢያ የመገንጠል ተልእኮ እና ከወያኔ የዘረኝነት ፖለቲካ እንዲከላከሉ በወታደርነት ሰልጥነው፣ በባንዲራው ስም ቃለ-መሀላ ፈፅመው ወደ ጦር ግንባር ከተላኩ በኋላ፣ በምርኮ ይሁን በወዶ-ገብነት ባይረጋገጥም የጠላትን ጎራ ተቀላቅለው በአሁኑ ወቅት ለደረሱበት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንንነት መብቃታቸው ይታወሳል፡፡) ዛሬ በእድሜም ሆነ በልምድ በስለው የተዛነፈውን ለማስተካከል፣ የተጣመመውን ለማቃናት፣ የተቀደደውን ለመድፈን… ባይችሉ እንኳ፣ ጋዜጠኛ በአደባባይ እንዲገደል እስከማዘዝ የደረሰ ‹ጥፋት ሊፈጽሙ ይችላሉ› ተብሎ አይጠበቅም ነበር፡፡ የሆነው ግን ይህ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትርም ሆነ የጦር አዛዥ፣ ወታደርም ሆነ ወዝ-አደር፣ ጋዜጠኛም ሆነ ቲያትረኛ፣ አርሶ አደርም ሆነ አርብቶ አደር፣ መንፈሳዊም ሆነ መናፍቅ፣ ነጋዴም ሆነ መደዴ… በሕግ ፊት ዕኩል ነው የሚለው የፍትህ ሥርዓቱ አዓማድ የማክበር ግዴታ ጄነራሉንም እንደሚጨምር ማስታወሰ ያስፈልጋል፡፡ በተመስገን ደሳለኝም ሆነ በሌሎች ጋዜጠኞች ላይ ለሚደርሱ ማንኛውም አይነት አደጋዎች እና ጥቃቶች መከለከያ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ አሰፈላጊ ነው።

ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሰራዊቱ ላይ የተሳካ ‹ሪፎርም› እንዳካሄዱ ቢናገሩም፣ መሬት የረገጠው እውነታ የተለየ እንደሆነ በማስረጃዎች የተደገፉ ክፍተቶችን በ‹ፍትሕ መጽሔት› በማቅረብ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ለመጠቆም እንደ ተሞከረ አንባቢን ያስታውሳሉ፡፡

LEAVE A REPLY