እስኪብርቶ በዱላ፣ ዲግሪ በአስከሬን የተቀየረበት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ግጭትና ምርቃት || ሮቤል ምትኩ...

እስኪብርቶ በዱላ፣ ዲግሪ በአስከሬን የተቀየረበት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ግጭትና ምርቃት || ሮቤል ምትኩ – አዲስ አበባ

በበርካታ የብሔር ግጭቶች፣ የማንነት ጥያቄዎችና እነዚህን ተከትለው በሚደርሱ ሰቅጣጭና አሳዛኝ ክስተቶች የታጀበው የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች ዓመታዊ የምረቃ ስነ – ስርዓት እንደቀጠለ ነው፡፡ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ስርዓት አልበኝነት የሰፈነበት፣ የሀገሪቱ ዩንቨርስቲዎች ዓመታዊ የትምህርት ሂደት አንዴ እየተቋረጠ፣

ሌላ ጊዜ እየቀጠለ፣ ዳግም በሚያገረሽ ሁከትና ብጥብጥ ለቀናት እየተዘጋ ዓመቱን ጨርሰውታል፡፡ በአንፃሩ የአዲስ አበባ የተሻለና የተረጋጋ የትምህርት ስርዓት የተካሄደበት ተቋም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በ1985፣ 1987፣ 1993 ዓ.ም ላይ ከፍተኛ የሆነ የተማሪዎች ዓመፅና እንቅስቃሴን በማቀጣጠል ከአዲስ አበባ ባህርዳር የደረሰው የዩንቨርስቲ ተማሪዎች አመፅ በርግጥም ምክንያታዊ ነበር፡፡

ከመሃል አገር የተነሱት እነዚህ ግዙፍ የተማሪ ንቅናቄዎች የኤርትራን መገንጠል በመቃወም፣ ስልጣን ላይ የነበረው ስርዓት የሚያከናውናቸው አፈናዎች በማውገዝ፣ ዛሬ በተግባር ላይ የዋለው ትውልድ ገዳይ የትምህርት ፖሊሲ እንዳይተገበር በመከላከልና የአካዳሚክ ነፃነታቸው እንዲከበር በመጠየቅ ላይ መሰረታቸውን የጣሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ሕወሓት መራሹ መንግስት የ‹‹ከፋፍለህ ግዛ›› ፖሊሲውን በመጠቀም የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎችን፣ የትግሬና የኦሮሞ ተማሪዎችን ዕርስ በርስ በማጋጨት የወጣቶቹን ጥያቄ ለማዳፈን ሞክሮ ነበር፡፡ ይሁንና እነዚህ ግጭቶች ብዙ ጊዜያት በተማሪው የነቃ ተሳትፎ ያለ ጸጥታ ኃይሎች ዕርምጃ በፍጥነት ሲከስሙ ታይተዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የዩንቨርስቲ ተማሪዎች አገራዊና ሕብረተሰባዊ ፋይዳ ያላቸውን ጥያቄዎች አቅርበው፣ ትክክለኛ አገር ተረካቢ ትውልድ፣ ሕዝብን ቀስቃሽና አደራጅ መሆናቸወን ከማሳየት ይልቅ እርስ በርስ በብሔርና በጎጥ እየተከፋፈሉ መናቆርና መተላለቅን በመምረጥ ‹‹ የመከነ ትውልድ ›› እንድናይ አስገድደውናል፡፡

ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተማሪዎቹን ካስመረቀው አዲስ አበባ ዩንቨርስቲን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ዩንቨርስቲዎችም የምረቃ ስነ ስርዓታቸውን እያካሄዱ ነው፡፡ በተቃርኖ በሽታ የተለከፉት አንዳንድ ዩንቨርስቲዎች የምርቃት ቀናቸውን በተመሳሳይ ሁኔታ ሲያከብሩ፣ ለዚህ ቀን ያልበቁት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ደግሞ የምረቃ ጊዜያቸውን በሰቀቀን እያሰቡ ይገኛሉ፡፤ ዩንቨርስቲዎቻን የዕውቀትና የጥበብ መቅሰሚያ መሆናቸው ቀርቶ፣ የመፈላለጫና የመገዳደያ ቦታ ሆነው ከርመዋል፡፡ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲህ ዓይነቱ ተግባር እንዳይደገም ከትምህርት ዓመቱ መጀመር አንስቶ የየአካባቢው የአገር .ሽማግሌዎች፣ ነዋሪዎች፣ የህግ አካላትና መምህራንን በማስተባበር የምክክር መድረኮችን አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም በበርካታ ቦታዎች ላይ ልፋቱን ገደል የሚከቱ ግጭቶችን ተመልክተናል፡፡

የአገሪቱ መሪ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የትምህርት ዓመቱ ከመጀመሩ በፊት “ ይድረስ ለነገዎቹ” በሚል ሰፋ ያለ መልዕክትና ምክር አስተላልፈው እንደነበርም ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ቁመና ላይ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲች እንቅስቃሴ ታክሎበት፤ ጫና ለመፍጠር ዩንቨርስቲዎችን ዋነኛ ዓላማ የማድረግ መረጃ ስለነበረ በዚህ ረገድ መንግስት ከፍተኛ ጥረትና እንቅስቃሴ ቢያደርግም አልተሳካላትም ማለት ይቻላል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መንገድ የትምህርት ተቋማቱን በማደራጀት የተጀመረው የ2011 ዓ.ም የዩንቨርስቲዎች ትምህርት፤ ወላጅ እስኪብርቶ አስይዞ የላካቸው ተማሪዎች፣ ትምህርታቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ ወደ ጠብ ለመግባት አልዘገዩም፡፡ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች መለያና መታወቂያ የነበረው እስኪብርቶ በዱላ ተተክቷል እስኪባል ድረስ የትምህርት ተቋማት የግጭት አውድማ እየሆኑ መጥተዋል፡፡

በኹለት ተማሪዎች መሀከል የሚፈጠር አለመግባባት ወደ ቡድን እየተቀየረ፣ የብሔር ካባም እየደረበ፣ በተማሪዎች ላይ በርካታ የአካል ጉዳት አድርሷል፡፡ ባለ ዲግሪ ልጆቻቸውን ሲጠባበቁ ለነበሩ ወላጆችም አስከሬን እንዲቀበሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ መንግስት ብዙ ወጪ ያፈሰሰባቸው ህንፃዎችና ልማቶችም ወድመዋል፡፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ከተፈራው የፖለቲካ ትኩሳት መለብለብ አላመለጡም፡፡ በዚህ መልክ የወጣት ተማሪዎችን ሕይወት የቀጠፈው የዩንቨርሰቲ ተማሪዎች ጥያቄ ከአምቦ፣ ወለጋ፣ ከደብረብርሃን፣ አዲግራት፣ ከሐሮማያ መቀሌ እያለ እንደ ግጭቶቹ ስፋትና ደረጃ በርካታ አሳዛኝ ክስተቶችን ሲያስተናግድ ሰንብቷል፡፡

ወላጅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሰቀቀን ባለፈበት ዓመት በሁሉም ዩንቨርስቲዎች ዓመታዊ የምረቃ ስነ ስርዓት 152 000 (አንድ መቶ ሀምሳ ሁለት ሺኅ) ተማሪዎች እየተመረቁ ነው፡፡ የተስተጎጎለውና በብሔር ግጭቶች እና አላስፈላጊ ብጥብጦች የታጀበው የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት በሚካሄዱ የምረቃ ሥነ-ሥርዓቶች መቋጫ ያገኘ ቢመስልም፤ የዘረኝነት በሽታ የተጸናወታቸው፣ ከእውቀት ይልቅ የፖለቲከኞችን ዲስኩር የሚጠቡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች “ልክፍት” በቀጣይ ዓመት ዳግም ላለማገርሸቱ አንዳችም ማረጋገጫ የለም፡፡

LEAVE A REPLY