ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ...

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የሲዳማ ዞን መስተዳደር ምክር ቤት ውሳኔን መሰረት በማድረግ በህዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ለመወሰን ህዝበ ውሳኔ እንዲደራጅለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እንደ አዲስ የማደራጀት፣ የምርጫ ቦርድ ስልጣንና ተግባር የሚወስነውን ህግ የማርቀቅ እና በተወካዮች ምክር ቤት የማጸደቅ፣ የምርጫ ህጎችን የማሻሻል፣ ተቋማዊ ለውጦችን የማከናወን እንቅስቃቄ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ከነዚህ ተቋማዊ ለውጦች መካከል የቦርዱን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት አድርጎ የተከናወነው የምርጫ ቦርድ አባላት መረጣ ዋነኛው ነው፡፡

በዚህም መሰረት ከዚህ የቦርድ አባለት መረጣ ሰፊ ምክክርና ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጐበት ከተለየ በኋላ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 06 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ተጨማሪ አራት የቦርድ አባላት ሹመት ተከናውኖ ቦርዱ አባላት ተሟልተውለት ስራውን ጀምሯል፡፡

ቦርዱ ተሟልቶ ስራ በጀመረበት ባለፈው አንድ ወር በእንጥልጥል የሚገኙ እና አስቸኳይ ናቸው ያላቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

በቦርዱ አለመሟላት ምክንያት በእንጥልጥል ከቆዮት ጉዳዮች አንዱ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ለቦርዱ የቀረበው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ ማደራጀት ነው፡፡

ቦርዱ ስራ ከጀመረ አንስቶ የሲዳማ ዞን ክልልነትን የሚመለከቱ በተለያዩ ጊዚያት የቀረቡትን ጥያቄዎች ከመመልከቱም በላይ ከክልሉና የዞን መስተዳድር አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

እንደሚታወቀው የሲዳማ ዞን የክልልነት ህዝበ ውሳኔ የማደራጀት ጥያቄ ከክልሉ ምክር ቤት ለቦርዱ የደረሰው ህዳር 12/2011 ዓ.ም ሲሆን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 47/3/ለ/ ለክልሉ የተሰጠው “ጥያቄው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በአንድ አመት” የሚለው የማደራጀት ጊዜ ገደብ ለቦርዱም ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡

በመሆኑ በህግ መንግስቱ የተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ በቀሩት 5 ወራት ውስጥ ህዝበ ውሳኔውን ለማከናወን የመጀመሪያ ደረጃ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡

ህዝበ ውሳኔ የሚከናወነው የህዝብን ፍላጐትና ውሳኔ ህጋዊ እና ነፃ በሆነ አግባብ መሰጠቱን ለማረጋገጥ ነው፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ተገቢና በቂ ዝግጅት አድርጐ ህዝበ ውሳኔውን ማካሄድ ይችል ዘንድ የሚያደርጋቸው ዝግጅቶች
– የህዝበ ውሳኔ አካሄድ የሚመራበት የስነስርአት መመሪያ ማዘጋጀት
– የህዝበ ውሳኔ አጠቃላይ ጊዜ ሰሌዳና በጀት ማዘጋጀት
– በህዝበ ውሳኔ ዝግጅትና ድምፅ መስጠት ሂደት ስለሚኖረው የፀጥታ አጠባበቅ ሁኔታ ግብረ ሃይል ማደራጀትና ዕቅድ ማፅደቅ
– ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚዎች መመልመል፣ ማሰልጠንና ማሰማራት
– ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረክ ማዘጋጀት፣ የድርጊት መርሃ ግብር ማውጣት
– በህዝበ ውሳኔ አፈፃፄም ሂደቱ ላይ የጋራ ምክክር መርሃ ግብሮችን አውጥቶ መተግበር
– የሰነድና ቁሳቁስ ዝግጅትና ህትመት ስራዎች ማከናወን
– ድምፅ መስጫ ወረቀቶችና ፖስተሮች ማዘጋጀት፣ ማሳተም፣ ማሰራጨት
– ህዝበ ውሳኔ ድምጽ ማሰጠት
– ቆጠራና ውጤት ማሳወቅ
ሲሆኑ በሌላ በኩል ሂደቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

በዚህም መሰረት፦

1. የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ከክልሉ መንግስትና ከዞኑ መስተዳደር ጋር በመመካከር በአሁኑ ወቅት የክልሉም የዞኑም አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሀዋሳ ከተማ የህዝበ ውሳኔው ውጤት የሲዳማን ክልል መሆን የሚያረጋግጥ ቢሆን በከተማዋ ላይ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብትና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎችን የሚያስተናግዱበትን አሰራር አዘጋጅተው ለቦርዱ እንዲያሳውቁ

2. በአዋጅ 532/1999 አንቀጽ 107 በተጠቀሰው የትብብር ድንጋጌ መሰረት የህዝበ ውሳኔው ጸጥታና ደህንነትን ( electoral security) ማስጠበቅን አስመልክቶ የፌደራል ፓሊስ፣ የክልሉ ፓሊስና የዞኑ ፓሊስ በትብብር የሚሰሩበትን ዝርዝር እቅድ እንዲያወጡና ከቦርድ ጋር ተባብረው እንዲሰሩ

3. የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሄር ብሔረሰብ አባላት ከህዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ህጋዊ የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ግልጽ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማእቀፍ እንዲያዘጋጅና ለቦርዱ እንዲያሳውቅ ምርጫ ቦርድ የወሰነ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ምላሽ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በጽሁፍ እንዲያሳውቁ ወስኗል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህገ መንግስቱና በምርጫ አዋጁ የተሰጠውን ሃላፊነት አለም አቀፍ የምርጫ መሰረታዊ መርሆዎች ጋር በማጣመር ሃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ለመግለጽ ይወዳል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሐምሌ 10/2011 ዓ.ም

LEAVE A REPLY