በአዲስ አበባ 20 ሺህ አባወራ ለጎርፍ አደጋ ተጋልጧል
በክረምቱ ወራትና በወቅታዊው ከፍተኛ ዝናብ የተነሳ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ 20 ሺህ 955 አባወራዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸው ተነገረ፡፡ 990 ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ ጎርፉ ያሰጋቸዋል ተብሏል፡፡
እንደ አዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መግለጫ ከሆነ ይህንን አደጋ በፍጥነት መከላከል ካልተቻለ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ይወድማል፡፡ በከተማዋ ካሉት አስር ክ/ከተሞች መሀል ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጎርፍ የሚያጠቃቸው አራዳ፣ ቂርቆስ፣ ልደትና አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተሞች አሁንም ከፍተኛ ስጋት ተጋርጦባቸዋል፡፡
አስቀድሞ በተደረገ ጥናት መሰረት የክረምት ወር መግባቱን ተከትሎ ለጎርፍ አደጋ ይጋለጣሉ የተባሉ 131 ቦታዎች ታውቀዋል፡፡ 67 በወንዝ ተፋሰስ፣ 20 በፍሳሽ ማስወገጃዎች ጥበት ማነስና አለመኖር ወይም በቆሻሻ መደፈን ምክንያት፣ 10 በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ “ሎሚ ሜዳ” በሚባለው አካባቢ የአስፋልት መንገድ ቱቦዎች በአግባቡ ባለመገንባታቸውና የውሃ ፍሳሽ ባለመኖሩ 500 አባወራዎች ለአደጋ ሥጋት ተጋላጭ ናቸው ተብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ሰው ሰራሽ በሆኑ ችግሮች ሳቢያ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በሰሞኑ ከፍተኛ ዝናብ ባለፈው ሳምንት በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ኹለት ሰዎች እንደሞቱ ከባለስልጣን መ/ቤቱ ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 19 ቢሊዮን ብር አተረፍኩ አለ
በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ ትርፍ በማስመዝገብ የሚታወቀው ንግድ ባንክ በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት 19 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡ ተሰምቷል፡፡
በ2011 ዓ.ም በጀት ግማሽ ዓመት 9.4 ቢሊዮን ብር ያተረፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ በዚሁ ግማሽ ዓመት ላይ 29 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ አሰባስቧል፡፡ በተመሳሳይም 40 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱ ታውቋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የትርፍ መዋዠቆች ገጥመውት የነበረው ንግድ ባንክ፤ የዘንድሮ የትርፍ እድገቱ ከአምናው ጋር ሲነፃፀርና በመቶኛ ሲሰላ የ90 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
በ2009 ዓ.ም 14ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ የነበረው ንግድ ባንክ፤ በቀጣይ 2010 በጀት ወደ 10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ቁልቁል መውረዱ አይዘነጋም፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1.200 በላይ ቅርንጫፎቹ ከ34 ሺኅ በላይ ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ ንግድ ባንክ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጠቅላላ ጥሪት ባለቤት በመሆን በአፍሪካም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ተቋም ነው፡፡
የጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች ወደ ግል ሊዛወሩ ነው
በቀድሞው ብአዴን በአሁኑ አዴፓ ባለቤትነት በአማራ ክልል በጥረት ኮርፖሬት ስር የሚተዳደሩ ከአስር በላይ የሚሆኑ ኩባኒያዎች በአክሲዮንና በሽያጭ ወደግል እንዲዛወሩ ተወስኗል፡፡ በዚሁም መሰረት አምባሰል ንግድ ስራዎች፣ ጥቁር አባይ ትራንስፖርት፣ የባህርዳርና ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ኩባኒያዎች፣ የተለያዩ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በቅርቡ ለሽያጭና ለአክሲዮን ገበያ ይቀርባሉ፡፡
ከቀጣዩ ምርጫ ጋር በተያያዘ አዲስ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረበው በብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው ምርጫ ቦርድ “ማንኛውም በምርጫ የሚሳተፍ የፖለቲካ ድርጅት በንግድ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ አይችልም” የሚል አዲስ አዋጅ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ አዴፓ ይህንን ተከትሎ ጥረትን ወደ ግል ባለሃብቶች በማዞር ለምርጫው እየተዘጋጀ ነው የሚሉ ግምቶች ከወዲሁ እየተሰነዘሩ ናቸው፡፡
“ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ካልተከናወነ ሞቼ እገኛለሁ” የሚለው ሕወሓት ለምርጫ ቦርድ አዲስ ህግ ተገዢ ሆኖ፣ ግዙፉንና የደምስሩ የሆነውን “ኤፈርትን” ለገበያ ያቀርብ ይሆን? ይሚል ጠያቄ በብዙዎች ዘንድ ቢነሳም ሱር ኮንስትራክሽንን የመሳሰሉ ድርጅቶቹን በውጭ ሀገር ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለምሸጥ ቅስቀሳ መጅምሩ አይዘነጋም::