ኤፍ.ቢ.ሲ || የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አስመራ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ልኡካቸው አስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ነው በዛሬው እለት አስመራ የገቡት።
በአስመራ ቆይታቸውም ከኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብር ዙሪ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
በተጨማሪም በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋርም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ወደ አስመራ አቅንተዋል።
በተያያዘ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ከጀመረ ዛሬ ድፍን አንድ ዓመት እንደሞላው አስታውቋል።
በቀን ሁለት ጊዜ በአዲስ አበባ እና በአስመራ መካከል በሚያደርገው በረራም እስካሁን 130 ሺህ መንገደኞችን ማጓጓዙን ከአየር መንገዱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።