በአዲሱ ከቀረጥ ነፃ አዋጅ 31 የመንግስት ተቋማት ተቀናሽ ይሆናሉ
በተሻሻለ መንገድ እየተረቀቀ ባለው አዲስ የቀረጥ ነፃ አዋጅ ሲፀድቅና ተግባራዊ ሲሆን መንግስት በየዓመቱ ሲሰጥ ከቆየው የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ 20 ቢልዮን ብር ለማዳን ታስቧል፡፡ በረቂቅ አዋጁ መሠረት ለ35 የመንግስት አካላት (ተቋማት) ሲሰጥ የነበረው የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ወደ አራት ዝቅ እንዲል ከማድረግ ባሻገር በግልፅ ሲታዩ የቆዩ ክፍተቶችንም ይሞላል ተብሏል፡፡
ሰላሳ አንድ የመንግስት ተቋማትን እስከዛሬ ከቆዩበት የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ወጪ የሚያደርገው አዲስ አሰራር ጤናማ የንግድ ዕቅድ ይዘው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሁም የአገር ውስጥ አልሚዎች ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻዎች ይልቅ የገበያ ፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ይበልጥ ትኩረት እንዲያደርጉ ያስገድዳል፡፡ በአዲሱ አዋጅ የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚዎችን ከማሻሻል ባሻገር መብቶቹ ከተሰጡ በኋላ በትክክል ለተገባላቸው ዓላማ መዋላቸውን ወይም አለመዋላቸውን ለመከታተል የሚያግዝ ስርዓትም ይዘረጋል፡፡
“የአድዋ ማዕከል” ግንባታ በአዲስ አበባ ተጀመረ
በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ወጪ የሚገነባው የአድዋ ማዕከል ግንባታ መጀመሩ ታውቋል፡፡ የአድዋን ታሪካዊ ድሉን በሁለንተናዊ ይዘት ለትውልድ ለማሻጋገርና የአድዋ ጀግኖችን መዘከርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው የማዕከሉ ግንባታ የሚካሄደው፡፡
የዓድዋ ማዕከል ግንባታ ሲጠናቀቅ ከሚሰጠው ማህበራዊና ታሪካዊ ፋይዳ በተጨማሪ በውስጡ የአድዋ ሙዚየም ጨምሮ ከ2 ሺህ ሰው በላይ የሚይዝ ትልቅ አዳራሽ ይኖረዋል፡፡ ሁለት ዓመት የሚፈጀውን የማዕከሉን ግንባታን የቻይናው ጂያንግሱ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና ቴክኒካል ግሩፕ ያካሂደዋል፡፡
400 ሰው የመያዝ አቅም ያላቸው ተጨማሪ ሶስት አዳራሾች፣ የሲኒማ አዳራሽ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስሪያ ጂም የህፃናት መጫወቻ እና ስፍራዎች፤ እንዲሁም አረንጓዴ ስፍራ፣ ካፌና ምግብ ቤቶች፣ ዘመናዊ ፓርኪንግን የዓድዋ ማዕከሉ እንደሚያካትት ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ አስመራ ጉብኝት
በኤርትራ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማካሄድ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ወደ አስመራ ተጉዘዋል፡፡ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ እና ልዑካቸው አስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አቀባበል አድርገላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ በሚያደርጉት የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በሁለቱ ሃገራት አጠቃላይ ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት እንደሚመካከሩም የኤርትራ መንግስት የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገፃቸው ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይዘውት ወደ ኤርትራ በተጓዙት ልዑክ ውስጥ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሸዴና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ይገኙበታል፡፡ በቀን ሁለት ጊዜ በአዲስ አበባና በአስመራ መካከል የሚደረገው በረራ ከተጀመረ ዛሬ አንድ ዓመት ሞልቶታል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ተከትሎ አየር መንገዱ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት 130 ሺህ መንገደኞችን አጓጉዟል፡፡
በኦሮሚያ የነዋሪዎች ዜግነት አገልግሎት ዙሪያ ህዝባዊ ውይይት ተጀመረ
በኦሮሚያ ክልል የነዋሪዎች የዜግነት አገልግሎት ዙሪያ የሚመክሩና ለሁለት ቀናት የሚቆዩ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ዛሬ ሀምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ተጀምረዋል፡፡
በነዋሪዎች የዜግነት አገልግሎት ዙሪያ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች በሁሉም የኦሮሚያና ክልል፣ ዞኖችና ከተሞች ነው እየተካሄደ ያሉት፡፡ ዛሬ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች በለገጣፎ፣ ለገዳዲና በጅማ ዞን እንደተካሄደ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገልጿል፡፡
የዜግነት አገልግሎት ዋነኛ ዓላማ ትውልዱ በገዳ ስርዓት መሰረት ለክልሉ አስተዋፅኦ የሚያደርግ፣ ችሎታና ብቃትን ያጣመረ በተጨማሪም ለአገሩ ፍቅር ያለው ዜጋ እንዲፈጠር ማድረግ፣ ብሎም ዜጎች ለክልሉና ለአገራቸው ተቆርቋሪ ሆነው አብሮ የመስራት ባህልን እንዲያዳብሩ ማስቻል ነው ተብሏል፡፡
እንደመጨረሻው ከሆነ የዜግነት አገልግሎት አሰጣጥን በበላይነት የሚያስተባብር ምክር ቤት በክልል ደረጃ እንዲመሰረት የተደረገ ሲሆን፤ ከህዝባዊ ውይይቶች በኋላም የዜግነት አገልግሎቱ ማስተባበሪያ ም/ቤቶች፣ ዞን፣ ወረዳ ከተማ እና ቀበሌ ደረጃ እንደሚደራጅ ተነግሯል፡፡
በትግራይና ኦሮሚያ ሁለት ሺህ አራት መቶ ቤቶች ፈረሱ
ሕገ ወጥ ናቸው በሚል በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው ሁለት ሺህ አራት መቶ የሚሆን ቤቶች እንዲፈርሱ ተደርጓል፡፡
በክልሎች የተለያዩ ቦታዎች እየተወሰደ ያለውን ህገ-ወጥ ቤት የማፍረስ ሂደት ተከትሎ በትግራይ ክልል በእንደርታ ወረዳ አስተዳደር “ማህበረ ገነት” ቀበሌ ከ420 በላይ ቤቶች ሕገ ወጥ በሚል ፈርሰዋል፡፡ እነዚህ ህገ-ወጥ ግንባታዎች ተብለው የፈረሱት ቤቶች ከ1990 ጀምሮ ላለፉት 21 ዓመታት በቦታው የኖሩ ናቸው፡፡ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎችም በስራቸው ከአራት እስከ አስር የሚደርስ ሰው የሚያስተዳድሩ ናቸው፡፡
የእንደርታ ሕገ ወጥ ቤት ግንባታ የተከናወነው በልዩ ኃይልና በፖሊስ እጀባ ነበር ተብሏል፡፡ የከተማው አስተዳር የወሰደውን ዕርምጃ የተቃወመና ድርጊቱን ፎቶ ሲያነሱ የነበሩ ግለሰቦችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች የማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው ትናንት ምሽት ዶዘር ይዘው በመምጣት “ዕቃችሁን አውጡ” እንደተባሉ ተናግረዋል፡፡ ቤታቸው የፈረሰባቸው እነዚህ ነዋሪዎች ሜዳ ላይ ድንኳን በመስራት እንደተጠለሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ ዜና በምሥራቅ ሸዋ አዳማና ምቹ አካባቢ በህገ-ወጥ መንገድ በተካሄደ የመሬት ወረራ የተገነቡ ናቸው የተባሉ ከ2000 በላይ ቤቶች እንዲፈርሱ ተደርጓል፡፡ የምሥራቅ ሸዋ ዞን የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ክፍል ምክትል ሓላፊ አቶ ሙባረክ ዑስማን በዞኑ ሕገ – ወጥ የመሬት የተስፋፋ በመሆኑ ሕገ ወጥ ቤቶችን በተመለከተ የወጣውን ደንብ ቁጥር 182 ተከትሎ ከ2005 ዓ.ም ወዲህ የተሰሩ 5000 (አምስት ሺህ) ቤቶችን እንደሚያፈርሱና ዕርምጃውም እንደሚቀጥል ለቢቢሲ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ዩኒሴፍ እና ከመንግስታቱ ድርጅት የ1 ነጥብ 4 ቢልየን ብር ስምምት ተፈራረሙ
ኢትዮጵያ እና ከዓለም አቀፍ የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዲሁም ከመንግስታቱ ድርጅት የስነ ህዝብ ፈንድ (ዩ ኤን ኤፍፒ) ጋር የ49 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ1 ነጥብ 4 ቢልየን ብር ስምምት ተፈራረሙ፡፡
የኢፌድሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አድማሱ አበበ እና በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ኤይሰሌ ኮደር ስምምነቱን በመፈራረም ዕውን አድርገዋል፡፡
በሀገሪቱ የሚገኙ ህፃናትና ጤናማ አስተዳደግ ለማሻሻልና ባህሪያት ላይ የሚያደርሰውን ሰብዓዊ ጥቃት ለመከላከል ብሎም ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ፕሮግራሞች ነው ገንዘቡ የሚመራው፡፡ በዚህም መሰረት በህፃናት ጤና፣ ንፅህና፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት፣ ትምህርትና የሕፃናት መብትን ጨምሮ 16 የተለያዩ ፕሮግራሞች ይተገበራሉ፡፡
በኢትዮጵያ መንግስትና በዩኒሴፍ መካከል በተደረገው ስምምነት ላይ ከተገኘው ገንዘብ 10 ሚሊየን ዶላሩ በመንግስታቱ ድርጅት የሥነ ህዝብ ፈንድ (ዩ ኤን ኤፍ ፒ) የተሸፈነ ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም የሚተገበረው ይህ ፕሮግራም ዩኒሴፍ ከ2016 እስከ 2020 (እ.ኤ.አ) በኢትዮጵያና በመንግስታቱ ድርጅት የልማት አጋርነት ስር የሚተገበረው የመጨረሻው ፕሮግራም ይሆናል፡፡ ፕሮግራሙ በተከታታይ አምስት ዓመታትም እንደሚተገበር
ዩኒሴፍ አስታውቋል፡፡