“ያገሬ እህት ናት” || ቴዲ ድንቅ አትላንታ

“ያገሬ እህት ናት” || ቴዲ ድንቅ አትላንታ

አላ ሳላህ የሱዳን የአንድ ሰሞኑ ተቃውሞ ዋና ምልክት ናት። አንዳንድ አገራት ድንገት ብቅ የሚሉ ጀግኖች አሏቸው። ለሱዳኖች ዘንድሮ አላ ሳላህ ነች።

ይህች ወጣት ፣ የሱዳን ህዝብ ፕሬዚዳንቱን ተቃውሞ ከሥልጣን እንዲወርዱ ባስገደደበት ዘመቻ ዋና ፊት መሪ ነበረች። ም ዕራባውያን ሚዲያዎች የተቃውሞው መልክ አድርገው ነበር የሚስሏት። ድፍረቷ ፣ ቆራጥነቷ፣ እየደከመ ወደኋላ የሚለውን ሰልፈኛ እንደገና ወደፊት እንዲመጣ በቆራጥነት ተጋድላለች። የነሱ “እቴጌ” ሆናለች ማለት ይቻላል።

ይህች ሴት፣ አልበሽር ከወረዱ በኋላም ፣ ሥልጣን ለህዝብ እንዲሆን ወታደሮቹም ሥልጣኑን ይዘው ሙጭጭ እንዳይሉ የምትችለውን ሁሉ አድርጋለች። አልበሽር ወረዱ በቃኝ ብላ አልተቀመጠችም። ወታደሮቹ ተመልሰው “ሌላ አልበሽር” እንዳይሆኑ ህዝቡን ወክላና አስተባብራ ታግላለች። ባጭሩ ለሱዳኖች የዘንድሮ ለውጥ ፊታውራሪ ሆናለች።

ይህች ሴት ታዲያ በጉልበትና በሃይል ሥልጣኑን አምጡ ብላ አልነበረም። በድርድርና በሰላም ለሱዳን የወደፊት ህልውና ስንል፣ “እናንተም ይህን ስጡን፣ ከኛም ይህን እንኩ” በሚል መንፈስ ነበር ወታደሮቹን የቀረበችው።

ወታደሮቹ ሲያንገራግሩና ሱዳን ሌላ ቀውስ ውስጥ ልትገባ ስትል፣ ኢትዮጵያ ጣልቃ እንድትገባ ተጠየቀች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሄደው አነጋገሯቸው፣ “በዚህ መልክ ብትስማሙ ጥሩ ነው” ብለው ሃሳብ አቀበሏቸው። ሱዳኖቹም አክብረው ተቀበሉ።

እነሆ ሰሞኑን የስቪሉ ህዝብ ወኪሎች እና የወታደሮቹ ወኪሎች ተፈራረሙ። ሱዳንም ከመፈራረስ ዳነች። ሱዳን ብትፈራርስ ጦሱ ለኢትዮጵያ ይተርፍ፣ አይ ሲስም እዚሁ አፍንጫችን ሥር ይበቅል ነበር።

አሁን ታዲያ ይህች የሱዳኖች መልክ የሆነች ሴት በደስታና በሃሴት ተነፈሰች። ኢትዮጵያንም እንዲህ ስትል አወደሰቻት። “ኢትዮጵያ የአገሬ የሱዳን እህት ነች” !

ዓረብኛ የሚያውቁ ሰዎች እንደሚሉት “በዓረብኛ አነጋገር እህቴ ማለት ትልቅ የፍቅር ቃል ነው”

በሃይልና በጉልበት ሳይሆን፣ ሰጥቶ በመቀበል፣ በመስማማትና በመነጋገር፣ አንዱ ከሱ ትቶ፣ ለአገሩ የወደፊት ህልውናና አንድነት ቅድሚያ ከሰጠ፣ የማይቻል ነገር የለም። ይህ የሱዳኖች መስማማት ፣ ደስታቸው ለኛም ነው።

ካፍንጫው አርቆ የማያስብ ሰው፣ “የኛ ችግር እያለ ለሱዳን ምን አገባን?” ይላል። መብትህ ነው። “ቤቴ ውስጥ ጭቅጭቅ እያለ እየተቃጠለ ያለውን የጎረቤቴን ቤት እሳት ለምን አጠፋለሁ?” በልና የሚመጣውን ታየዋለህ።

LEAVE A REPLY