በይርጋለምና አለታ ወንዶ በተነሳው አመጽ የሰው ሕይወት ጠፋ
ከ53 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብረው በፍቅር የኖሩባትና የጋራ ተምሳሌትነት መገለጫ የሆነችው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላሳ ቦታ በሚበጣጥሷት የክልልነት ጥያቄዎችና እሱን ተከትለው በሚመጡ ሁከትና ብጥብጦች እየታመሰች ትገኛለች፡፡
በሃይል ክልል የመሆን እንቅስቃሴን በሃዋሳ ለመተግበር የተውተረተሩትን ኢጄቶዎችን ተከትለው ለራሳቸው የነጻ አውጪነት ስያሜ ያጎናጸፉ ቡድኖች በየዞኑ ብቅ በማለት የ”ከማን አንሼ” ተግባር መፈጸሙንና የሀገሪቱን ሰላም ማወኩን ስራዬ ብለው ተያዘውታል፡፡
አድማሱን ባሰፋው ብጥብጥ ትናንትና ይርጋለም እና አለታ ወንዶን ከተሞች ሲንጣቸው ውሏል፡፡ “ንሳ” እና “ለኩ” ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጦች ተነስተዋል፡፡
በአለታ ወንዶ “አረብ ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባሉ የጣቃ ጨርቅ መሸጫ ሱቆች ላይ፣ በታይዋን ሰፈርና መናኸሪያ አካባቢ በርካታ ሱቆች በተነሰው ረብሻ ወድመዋል፡፡ ከመናኸሪያ ጀርባ ያሉ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ወድመዋል፡፡
ከአለታ ወንዶ አጎራባች የመጡ ወጣቶች ከተወሰኑ የከተማዋ ወጣቶች ጋር በመቀኛጀት በያዙት የነጋዴዎች ስም ዝርዝር እየተመሩ፣ ንግድ ቤቶችና መኖሪያ ቤቶችን ሲያወድሙ ታይተዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ሆን ብለው ንብረት ከማውደም በስተቀር የዘረፋ ተግባር አልፈጸሙም፡፡
በዚህ እንቅስቃሴ አስናቀ ገብረ ኪዳን ሆቴል መኝታ ክፍሎቹና ተሽከርካሪው ሙሉ ለሙሉ ወድሟል፡፡ የከተማዋ ወጣቶች ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ ጥፋት ሲያደርሱ ለከተማዋ ፖሊስ “የድረሱልን” ጥሪ ቢቀርብም ምንም ምላሽ ሳይሰጣቸው በመቅረቱ አደጋው መጠነ ሰፊ ሊሆን ችሏል፡፡ ማምሻውን ወደ ከተማዋ የገባው መከላከያና ፌደራል ፖሊስ ተኩስ በመክፈት በጥፋት ተግባሩ ላይ ከነበሩት ወጣቶች መኃል የተወሰኑትን በቁጥጥር ስር ከማዋሉ ባሻገር ፤ዛሬ (ቅዳሜ) የከተማዋን ጸጥታ ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ችሏል፡፡
በተመሳሳይ በይርጋለም ከተማም በትናንትናው ዕለት ከፍተኛ ችግር ተከስቶ ነበር፡፡ የወጣቶቹን ረብሻ ተከትሎ በ”አራዳ” አካባቢ ሰባት የግለሰብ ሱቆች ተቃጥለዋል፡፡ በሌላ ቦታ ዱቄት ፋብሪካና ሶስት ሱቆች በእሳት ጋይተዋል፡፡ በይርጋለም የከንቲባው ጽ/ቤት የተለያዩ መኪኖች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅት መኪና እንዲሁም የ”አረጋሽ ሎጅ” ሶስት መኪኖችም ለአመጽ አደባባይ በወጡት ወጣቶች አማካይነት ተቃጥለዋል፡፡
በትናንትናው አመጽ አንድ ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ፣ ሁለት ሰዎች ለከባድ ጉዳት ተጋልጠዋል፡፡ በይርጋለም ከተማም በተመሳሳይ ሁኔታ ከትናንት ምሽት ጀምሮ መከላከያ ሠራዊት ገብቶ የማረጋጋት ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡
አቶሙስጣፌ መሐመድ የክብር ሜዳሊያ ተሸለሙ
የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ለሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሙስጣፌ መሐመድ ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ መሸለሙ ተሰማ፡፡
አቶ ሙስጣፌ መሀመድ በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ታሪካዊውን የክብር ሜዳሊያ የተሸለሙት ዩኒቨርስቲው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን በርካታ ተማሪዎች ዛሬ ሐምሌ 13 ቀን 2011 ዓ.ም ባስመረቀበት ስነ ስርዓት ነው፡፡
አቶ ሙስጠፌ በባህርዳር ባስተላለፉት መልእክት
…”በእኔ እምነት ሁሉም ዜጋ አገራዊ ዜግነቱን ተቀብሎ፣ ኢትዮጵያዊነቱን ተቀዳሚ ማንነት አድርጎ ተቀብሎ፣ እንደሃገር የተገነባ Nation (አንድህዝብ) ሁኖ የምንነጋገርው በዘር ሳይሆን ከፍ ባለ በኢትዮጵያዊነት ደረጃ ቢሆን እና ሰዎች Association “ስብስብ” የሚፈጥሩት በዘር ሳይሆን በአመለካከት እንዲሆን መሪዎች በዘር ሳይሆን በችሎታ፣ ቢሮክራሲያችን Merit Based የአስተዳደር ዘይቤ ብንከተል የፌደራል አከላለላችንንም ከዘር ይልቅ ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚልተተክ
ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ላይ ከንቲባ በዘር ሳይሆን በችሎታው አወዳድረን ከንቲባ መሆን እንዲችሉ ተደርጎ መስተካከል አለበት” ማለታቸውን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ አድናቆትን እየተቸራቸው ይገኛል።
ለሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ይህንን የክብር ሜዳሊያ ያበረከተው፤ በክልሉ የነበረውን አለመረጋጋት በአጭር ጊዜ እንዲቀረፍ በማድረጋቸውና ከአጎራባች ክልሎች ጋር ሰላም ለመፍጠር ላደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የክብር ሜዳሊያውን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌውና የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬሕይዎት ተገኝ እንዳበረከቱላቸው ከደረሰን ዜና ለማወቅ ችለናል፡፡
ኢጄቶዎች በድብቅ እየተደራጁ ነው፤ የሃዋሳ ፖሊስ “ህጋዊ ሽፋን” ሰጥቷቸዋል
ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በሃዋሳ ከተማና በሌሎች የደቡብ ኢትዮጵያ አንዳንድ ዞኖች ተፈጥሮ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ በተወሰነ ደረጃ ረገብ ያለ ቢመስልም፤ የችግሩ ምንጭ እንደሆነ የሚነገርለት “ኢጄቶ” ዳግም ሃይሉን አጠናክሮ ለመመለስ በሚስጥር መወያየትና መደራጀት መጀመሩን ውስጥ አዋቂዎች ከሃዋሳ ካደረሱን ጥቆማ መረዳት ተችሏል፡፡
ሐሙስ 11/11/11 ን መሰረት በማድረግ የሲዳማ ክልልነትን በህገ ወጥ መንገድ ለማወጅ ያለ የሌለ ሃይሉን በመጠቀም ወደ አመጽ የገባው ኤጀቶ በከተማዋ እንደ ልዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሃይል በመቆጠሩ፣ በሃዋሳ አስተዳደር በርካታ አመራሮችም በተዘዋዋሪ ድጋፍ የሚደረግለት ከመሆኑ ጋር ተያያዞ፤ ይህ በሲዳማ ወጣቶች የተዋቀረው ቡድን አላስፈላጊ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን በይፋ ሲያደርግ አስቀድሞ “እረፍ” የሚለው ህጋዊ አካል ባለመኖሩ ያየናቸው አሳዛኝ ጥፋቶች እንዲከሰት ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡
ዛሬ ላይ ከጃዋር መሐመድ እስከ አዲሱ ረጋሳ፣ ከታከለ ኡማ እስከ ዳውድ ኢብሳ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተገኘው ለውጥ አንበሳውን ድርሻ እንደያዘ በሃሰት የሚመሰከርለትና ከሌላው ኢትዮጵያዊ አንዳችም የተለየ ትግል ያላደረገው “ቄሮ” በሚወደሰብት ልክ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ውስጥ ስልጣን የያዙት የሲዳማ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሉን ህዝብ እንወክላለን የሚሉ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ልሂቃኖች “ኢጄቶ”ን በዚህን መሰሉ የተሳሳተ ግምት መቅረጻቸው፤ወጣቶቹ ሲዳማን አስመልክቶ የሚያደርጉት የትኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ በክልሉ የተፈቀደ ይመስል ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ከሀሙስ ማለዳ አንስቶ በሃዋሳ መንደሮች ውስጥ እንደልባቸው የሌላውን ህብረተሰብ ተወላጅ ሲዘርፉ፣ሲደበድቡና በቂም በቀል የተለያዩ የግል ፍላጎቶችን ቢፈጽሙም ወጣቶቹ እንዳጠፉት ጥፋት ልክ በህግ እየተጠየቁ አይደሉም፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የከተማው ፖሊስ ወንጀለኞችን አድኖ ከመያዝ ይልቅ፤ በተጠናወተን ክፉ የብሔርተኝነት ስሜት በመለከፉ ተጠርጣሪዎቹን እያስመለጠ፣ለይስሙላ ተራ የሲዳማ ወላጆችን በተጠርጣሪነት እንዲያዙ እያደረገ ነው የሚሉ መረጃዎች በደሉ ከተፈጸመባቸው የሃዋሳ ነዋሪዎች ዘንድ እየተሰማ ነው፡፡
አስቀድሞም ቢሆን የከተማው ፖሊስ የተዋቀረው በሲዳማ ተወላጆች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በደህንነታቸው ጉዳይ ትልቅ ስጋት ውስጥ ገብተው የሰነበቱት የሃዋሳ ነዋሪዎች “የክልልነት ጥያቄውና እሱን ተከተለው የሚመጡ ማናቸውም ነገሮች ትክክል ናቸው” የሚል አስተያየት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ የጸጥታ ሃይሎችም ሆነ በከተማዋ የመንግስታዊና ሕዝባዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በግልጽ እየተንጸባረቀ፤መንግስት መከላከያና ፌደራል ፖሊስን በከተማዋ ዋነኛ ቦታዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ብቻ እንዲቆጣጠሩ አድርጎ፣ሙሉ የከተማዋን ዙሪያና ውስጥ ለውስጥ የነበረውን እንቅስቃሴ “በእኔነት” ስሜት ለተለከፈው ፖሊስ መተው አልነበረበትም ሲሉም ይተቻሉ፡፡
በዚህም መሰረት በጉዱማሌ አካባቢ ከተነሳው የኢጄቶና የመከላከያ ግጭት ውጪ፤ በከተማዋ ከሲዳማ ተወላጆች ውጪ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚገኙባቸው አብዛኛው መንደሮች ውስጥ ኢጄቶ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከባድ ዘረፋ ከማካሄድ ባሻገር በንጹሃን ዜጎች ላይ ድብደባ ሲያካሂድ ታይቷል፡፡
በሃዋሳ ለተፈጠረው ብጥብጥ ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ወጣቶች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ቢነገርም የሃዋሳ ምንጮቻችን እንደነገሩን ከሆነ የኢጄቶ ዋነኛ አባላት አሁንም በብዛት እንዳልተያዙና ዋና ዋና አስተባባሪዎቹም እዛው ሃዋሳ ውስጥ ሆነው ስለ ቀጣይ እንቅስቃሴያቸው በድብቅ እየመከሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይም በተለምዶ አራዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለ አንድ የሲዳማ ተወላጅ መኖሪያ ቤት ውስጥ ትናንት ከቀትር በኋላ ቁጥራቸው 20 የሚደርስ ዋነኛ የኢጄቶ አስተባባሪዎች እንዴት ወጣቱን አስተባብረውና ሃይላቸውን አደራጅተው እንደሚመለሱ ሲመክሩ አምሽተዋል፡፡
በእንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ የሚታወቁት የወጣቶቹ መሰባበብ በእጅጉ ያስጨነቃቸው የሃዋሳ ነዋሪዎች ጉዳዩን ለከተማው ፖሊስ ከቀኑ 9 ሰኣት ጀምሮ ደጋግመው ሪፖርት ቢያደርጉም ፤ የጸጥታ ሃይሉ “ጥቆማውን ተቀብለናል፤ ዕርምጃ የሚወስድ ሃይል እንልካለን” ከማለት ውጪ ምንም ነገር ሳይፈይዱ እንደቀሩ እነዚሁ የሃዋሳ ምንጮጫችን ይናገራሉ፡፡ ወጣቶቹ ምክክራቸውን ያለስጋት በነጻነት አድርገው ከምሽቱ 12 ሰኣት ጀምሮ በተናጠል ወደየመጡበት መመለሳቸው፤ ነዋሪዎቹን የከተማው ፖሊስ ለህገ መንግስቱ ተገዢ በመሆን የዜጎችን ሕይወት መጠበቅ ሲገባው፣ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለአጥፊዎች በስውር ድጋፍ እየሰጠ ነው የሚል እምነትን በብዙኃኑ የሃዋሳ ነዋሪ ዘንድ እያሳደረ መሆኑን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ሚዲያ ኔት ዎርክ ሓላፊዎች፤ ትንናት ምሽት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተያዙ
በሃዋሳ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ እንዲቀጣጠል፣ እንዲሁም የሚሰማው የክልል እንሁን ጩኸት እንዲሰተጋባ ዓይነተኛ ሚና ተጫውተዋል የተባሉት “የሲዳማ ኔትዎርክ ሓላፊዎች ትናንት ምሽት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል፡፡
“ሰሞነኛውን ችግር ከማባበስ ይልቅ መፍትሄ ሊያበጁለት አልቻሉም” በሚል ጠንክር ያለ ወቀሳ እየቀረበባቸው ከሚገኙት ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ቁጭ ባሉበት ነው የሲዳማ ሚዲያ ኔት ዎርክ ሓላፊዎች የተያዙት፡፡
በደሕንንት አባላት፣ በፌደራል ፖሊስና የመከላከያ አባላት የተዋቀረው ቡድን የሃዋሳን እንቅስቃሴ ከመራው ኢጄቶ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው በማለት የሚዲያ ኔት ዎርኩን አመራሮች ለመያዝ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ወደ ቢሮአቸው ቢሄድም፤ ከዘበኞች ውጪ ማንንም ሊያገኝ ባለመቻሉ ሳይሳካለት ተመልሷል፡፡
በዚህ መሰረት አሰሳውን አጠናክሮ የቀጠለው የጸጥታ ቡድን ትናንት ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ በታቦር መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሲዳማ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢጀቶ አባሎች፣ የአገር ሽማግሌዎች ጉዳያቸውን አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ሃሳብ “እንቀበል ወይስ አንቀበል” በሚለው ላይ ከሲዳማ ሚዲያ ኔት ዎርክ አባላት ጋር እየተነጋገሩ ባለበት ሰዓት ደርሶ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡ የሲዳማ ሚዲያ ኔት ዎርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ደጉዬ እና ምክትላቸው አቶ ታሪኩ ለማ ከኢጄቶ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው በሚል በፖሊስ ተወንጅለዋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ ሥራ የጀመረውና አሁን በሙከራ ስርጭት ላይ የሚገኘው ሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ ፕሮግራሙን የሚያስተላልፈው ሃዋሳ ከሚገኘው ቢሮው፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከሚገኘው ማሰራጫ ጣቢያው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሲዳማ ሚዲያ ኔት ዎርክ በሲዳማ ተወላጅ ዲያስፖራዎችና ባለሀብቶች የተቋቋመ ቴሌቪዥን ሲሆን፤ በስሩ አርባ አንድ ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡