የሀዋሳ ከተማ፣ የሲዳማና የሀድያ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ከስራ ታገዱ
የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) በሲዳማ ዞን ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ የሲዳማና የሀዲያ ዞን ከፍተኛ አመራሮችን ከሃላፊነት አገደ፡፡
ለተከታታይ ቀናት በዘለቀውና በሐምሌ 11/11/11 ለተፈጠረው የሲዳማ ክልልነት ጥያቄና ሕገ-ወጥ አመጽ፤ እጃቸው አለበት በመባሉ ነው የሥራ ሓላፊዎቹ እግዱ የተላለፈባቸው፡፡ እነዚህ የስራ ሓላፊዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር ሊውሉ እንደሚችሉም ከወዲሁ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ከፍተኛ አመራሮቹ የም/ቤት አባል በመሆናቸው ያለመከሰስ መብታቸው በሕገ ደንቡ አማካይነት እስኪነሳ ድረስ በፖሊስ እንዳልተያዙ በቦታው ካሉ ታማኝ ምንጮቻችን መረዳት ችለናል፡፡
ደ.ኢ.ህ.ዴ.ን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ “ሀዋሳ ከተማ እና በሲዳማ ዞን የገጠር አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ውስጥ የራሳቸው ሚና የነበራቸው በመሆኑ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደርና የሲዳማ ዞን አመራሮችን ከስራ አግጂያቸዋለሁ” ሲል ይፋ አድርጓል፡፡ የሀድያ ዞን አስተዳዳሪዎችም ተመሳሳይ ዕርምጃ በመውሰዳቸውና አካሄዱን በመከተላቸው፤ ዕግዱ በእነሱም ላይ ተፈፃሚ ሆኗል ብሏል፡፡
በተለይም ላለፉት አስራ ሁለት ወራት በሲዳማ ጉዳይ የነበረው እንቅስቃሴ በግልፅ እየታየ አስቀድሞ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ በዝምታ የተሸበበው ደ.ኢህ.ዴ.ን ፤ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውንና አካላቸውን ካጡ፣ ብዙ ንብረት ከወደመ በኋላ አመራሮቹን ከስራ ማገዱ በብዙዎች ዘንድ መነጋሪያ ርዕስ ሆኗል፡፡
የደ.ኢ.ህ.ዴ.ንን እንደ ፓርቲ በደቡብ ክልል የመቀጠል ሕልውና ሊፈታተን የሚችል ጥያቄ ያነሳው ሲዳማ፤ የደቡብ ክልል የስልጣን መዋቅር በተወላጆቹ አማካይነት አብዛኛው ቦታ ሆን ተብሎ እንዲያዝ፤ በእነ ሽፈራው ሽጉጤ አማካይነት አስቀድሞ መሰራቱ እየታወቀ ነገሩን በቸልታ መመልከቱ፣ ደ.ኢ.ህ.ዴ.ን በብዙ መልኩ “ግልብ” እና “ተጋላጭ” ድርጅት እንዲሆን አደርጎታል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
ባለቀ ሰዓት “አለሁ” ያለው የወ/ሮ ሞፈሪያት ካሚል ደ.ኢ.ህ.ዴ.ን በከፋ እና በወላይታ ዞኖችም ተመሳሳይ ድርጊቶች እየተስተዋሉ በመሆናቸው ይህ ሁኔታ በፍጥነት ሊገታ ካልቻለ የዞኑ ሓላፊዎች በሕግ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመግለጫው አሳስቧል፡፡
የአማራ ክልል ም/ቤት የ47 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በጀትን አፀደቀ
የአማራ ክልል ም/ቤት የክልሉን የ2012 በጀት የሆነውን 47 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተቀብሎ አፀደቀ፡፡ የቀጣይ ዓመት የክልሉ በጀት እንዲፀድቅ የቀረበው፤ በአማራ ክልል ምክር ቤት አራተኛ ቀን የጠዋት መርሃ ግብር ነው፡፡
እንደ ክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሓላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶክተር) ገለጻ ከሆነ ከበጀቱ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተመደበው የበጀት ድጋፍ ነው፡፡ ከመንግስት ግምጃ ቤት ከተመደበው ጠቅላላ በጀት 61 በመቶ ትኩረት ተሰጥቶት የበጀት ድልድሉ መሰራቱንም ከሓላፊው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡
በዚህ መሰረት ለመደበኛ ወይም ለካፒታል ሥራዎች ማስፈፀሚያ 8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ ይህ ከመንግስት ግምጃ ቤት ከተመደበው በጀት 20 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ ጥቅል በጀቱ ከባለፈው በጀት ዓመት አንጻር ሲለካ በ943 ሚሊዮን 420 ሺህ ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡ የአዳዲስ ተቋማት መመስረትና የሠራተኞች ደምወዝ ለውጥ መኖር ለልዩነቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከበጀቱ ውስጥ 7 ቢሊዮን 207 ሚሊዮን 738 ሺኅ ብር የሚሆነው ለደምወዝና ለስራ ማስኬጃ ይውላል፡፡
1 ቢሊዮን 604 ሚሊዮን 262 ሺህ ብር ደግሞ ለነባርና አዲስ ካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እንደሚውልም ተሰምቷል፡፡ የገጠር መንገድ መጠጥ ውሃን በሁሉም አካባቢዎች ለማዳረስ 250 ሚሊዮን ብር ተመድቧል፡፡
የመንግስት ልማት ድርጅቶችን አቅም ለመገንባት 100 ሚሊዮን ብር፣ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የመሬት ዝግጅትና የመሰረተ ልማት አቅርቦት ለማሟላት 700 ሚሊዮን ብር በበጀት ዓመቱ ተይዟል፡፡ ለጤና ጣቢያዎች ግዥ ማስፈፀሚያ፣ ለስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ማስፈተኛ፤ ለመጽሐፍት ህትመት፣ ለተገነቡ ማህበራዊ ተቋማት ማጠናከሪያና ለተሸከርካሪ ግዢም ከፍተኛ በጀት ተመድቧል፡፡
ካለፈው ዓመት በጀት በ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለውን የ47 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የ2012 ዓ.ም በጀትን የምክር ቤቱ አባላት ሙሉ በሙሉ አፅድቀውታል፡፡
110 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የያዘ ግለሰብ በጎንደር በቁጥጥር ስር ዋለ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንድ ግለሰብ ምንጩ ያልታወቀና 110 ሺኅ የአሜሪካ ዶላር በህገ ወጥ መንገድ ይዞ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል፡፡
ግለሰቡ ይህን ያህል ዶላር ይዞ መንቀሳቀሱ ብቻ ሳይሆን ማንነቱን በሚገልጸው መታወቂያው ላይ “ስራ ፈላጊ” የሚል ጽሁፍ መስፈሩ ግርምት ከመፍጠሩ ባሻገር፤ ከተጠርጣሪው ግለሰብ ጀርባ ያለውን እንቅስቃሴ የበለጠ አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡
አቶ ገብረሕይወት አስማረ የተባለውን ግለሰብ አስመልክቶ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት ምክትል ኮማንደር አስማማው ካሴ እንደገለፁት ከሆነ ተጠርጣሪው ግለሰብ እጅ ላይ ከ100 ሺኅየአሜሪካ ዶላር በተጨማሪ በርካታ የእንግሊዝ ፓውንድ መገኘቱ ታውቋል፡፡
ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሞተው ከተገኙ አንድ ዓመት ሞላቸው
በኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ የሚታመንለት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ፤ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ (ራሳቸው አጥፍተዋል በሚል ፖሊስ ሲገለጽ) አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡
የእዚህ ታሪካዊ ፕሮጀክት ሓላፊ በለውጡ ማግስት መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውሥጥ ሕይወታቸው አልፎ ከተገኙ በኋላ፤ ፌዴራል ፖሊስ ኢንጅነሩ ራሳቸውን እንዳጠፉ በምርመራ ደርሼበታለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ ብዙዎች መግለጫው ባይዋጥላቸውም፤ፖሊስ መኪናው ውስጥ የተገኘውም ሽጉጥ የኢንጅነሩ እንደነበር አረጋግጫለሁ ማለቱ አይዘነጋም፡፡
እስካሁን ድረስ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የመነጋሪያ ርዕስ የሆነው የኢንጅነር ስመኘው በቀለ አሟሟት የተለያዩ መላምቶችን እያስተናገደ እነሆ ድፍን አንድ ዓመት ሞልቶታል፡፡ ከጅማሬው አንስቶ የህዳሴውን ግድብ በዋና ስራ አስፈፃሚነት ሲመሩ የቆዩት እኚህ ሰው ከዚህ ዓለም ከሞት ከተለዩ በኋላ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በቦታው ቢተኩም፤ አሁንም ፕሮጀክቱ ባለበት እንደቆመ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መንግስትም የሥራ ውሉ ለተጓተተው ኢንተርናሽናሉ ሳሊኒ ካምፓኒ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከመክፈል አልዳነም፡፡
በአቶ በረከትና አቶ ታደሰ ጉዳይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ አቃቤ ሕግ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች በእንግሊዘኛ ቋንቋ የቀረቡ በመሆኑ፣ ማስረጃዎቹን አቃቤ ህግ እስከ መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በአማርኛ ቋንቋ አስተርጉሞ እንዲያቀርብ አዟል፡፡
ፍርድ ቤቱ በተባለው ጊዜ የሚቀርቡትን የሰነድ ማስረጃዎች መርምሮ ብይን ለመስጠት መስረከም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡
በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት፤ በጥረት ኮርፕሬት የሀብት ምዝበራ ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያለው አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) “በሙስና እና ስራን በአግባቡ ባለመስራት” ወንጀሎች አራት ክሶች እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል፡፡
ኢቦላ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ጥብቅ ቁጥጥር ተጀመረ
በዴሞክራቲክ ሪፕብሊክ ኮንጎ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
በኮንጎ “ጎማ” ግዛት የኢቦላ ቫይረስ ምልክት በመታየቱና የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብክ ኮንጎ “ጎማ” ከተማ በሳምንት ሰባት ቀን በረራ ማድረጉ፣ የቫይረሱ ስርጭት ወደ ሃገር ቤት የሚገባበትን ዕድል ይፈጥራል የሚል ስጋት በመኖሩ፤ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የማጣሪያ ፍተሻ እየተካሄደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የጤና ሚንስትሩ ዶክተር አሚን አማን በሶማሌላንድ፣ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መግቢያና መውጫ በሮች ላይም የጥንቃቄ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ኢቦላ በአሁኑ ወቅት ከኮንጎ አልፎ አሜሪካና ስፔን ላይ መከሰቱን የጠቆሙት ዶ/ር አሚን፤ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ትልቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ለእዚህ የመከላከል ስራ መንግስት 250 ሚሊዮን ብር መድቧል፡፡ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ትኩሳትና ልዩ ምልክቶች ሲታዩ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት በማምራት ሊታይ እንደሚገባም ሚኒስትሩ በመግለፅ ይፋዊ ጥሪን አቅርበዋል፡፡
የቦይንግ ማክስ 8 አደጋና መዘዙ በዝቷል
ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 ከተከሰከሰ በኋላ በመላው ዓለም አውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ እገዳ የተጣለበት ቦይንግ በአውሮፕላኖቹ መዘዝ በሩብ ዓመት ውስጥ ብቻ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የ3.4 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠመው ይፋ አድርጓል።
በዚህ የተነሳም “በተለያዩ ቀጠናዎች ከሚገኙ አየር ተቆጣጣሪዎች ጋር የሚደረገው ትንቅንቅ የሚቀጥል ከሆነ እና አውሮፕላኖቹን በአጭር ግዜ ውስጥ ወደ በረራ መመለስ ካልቻልኩ ማክስ 737 አውሮፕላኖችን ማምረቴን ሙሉ በሙሉ አቆማለሁም” ብሏል። የኢትዮጵያ አየር መንገዱ አውሮፕላን ከመከስከሱ አምስት ወራት ቀደም ብሎ የኢንዶኔዢያው ቦይንግ 737 ማክስ መከስከሱ የሚታወስ ሲሆን የሁለቱ አውሮፕላኖች ለአደጋ መጋለጥ ምክንያት ዝርዝር ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች እንዲሁም የአየር በረራ ደህንነት ባለስልጣናት አውሮፕላኖቹ ኤምካስ ተብሎ የሚጠራው መተግበሪያቸው ላይ እክል መኖሩን ጠቁመዋል። ቦይንግም በኤምካስ ስርዓቱ ላይ ችግር እንዳለ አምኖ እሱን ለማስተካከል እየሰራ ይገኛል። ሁለቱ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከተከሰከሱ በኋላ ቦይንግ በወር ያመርት የነበረውን 737 ማክስ ከ52 ወደ 42 መቀነሱን የኩባንያው ሊቀመንበር ለባለሀብቶች ተናግረዋል። በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ኩባንያው በሶስት ወራት ውስጥ 3.4 ቢሊየን ዶላር ከስሯል።