ሕዝበ ውሳኔዎች የሚካሔዱባቸው ጉዳዮች ላይ ቋሚ እና ዓለም ዐቀፋዊ የሚባል ሥምምነት የለም። ነገር ግን የፖለቲካ ልኂቃኑን እንዲሁም ብዙኀንን በሚከፋፈሉ እና በተለምዷዊ የፖለቲካ ሒደቶች መፍታት ያልተቻሉ ጉዳዮችን ወደ ሕዝበ ውሳኔ መውሰድ የተለመደ ነው። በፍቃዱ ኃይሉ በዛሬው የግል አስተያየቱ የሲዳማን ሕዝበ-ውሳኔ ይቃኛል።
ሐምሌ 7፣ 2011 የሲዳማ ሽማግሌዎች እና ኤጄቶ በሚል ሥም የሚታወቁት የክልልነት ጥያቄው ወጣት አራማጆች በአደባባይ ተገናኝተው የሲዳማን የክልልነት ማዕረግ በበኩላቸው “ሃላሌ ጉቴ” ብለው በጠሩት ባሕላዊ ሥነ ስርዓት ማወጃቸውን ተናግረው ነበር። ሥነ ስርዓቱን ያጠናቀቁትም ለክልሉ ያዘጋጁለትን ባንዲራ በመስቀል ነው። ሥነ ስርዓቱ ‘እኛ ክልልነቱን ወስነናል፤ ቀሪው ሥራ [ዕውቅና መስጠቱ] የፌዴራል መንግሥቱ ነው’ የሚል መልዕክት ያዘለ ነበር። ከዚያ ትንሽ ቀደም ብለው ሐምሌ 11 ክልልነቱን እንደሚያውጁ በየብዙኀን መገናኛዎች ሲዝቱ የነበሩት ተሟጋቾችም ይሁኑ፥ በዚህ የአደባባይ ጉባዔ ላይ የተሳተፉት ሽማግሌዎች እና ወጣቶች የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ላይ ሕዝበ ውሳኔውን ከይስሙላ ሒደት በላይ የቆጠሩት አይመሥሉም። ታዲያ ሕዝበ ውሳኔው ለምን ይካሔዳል?
ሕዝበ ውሳኔ ለምን ያስፈልጋል?
ሕዝበ ውሳኔዎች የሚካሔዱባቸው ጉዳዮች ላይ ቋሚ እና ዓለም ዐቀፋዊ የሚባል ሥምምነት የለም። ነገር ግን የፖለቲካ ልኂቃኑን እንዲሁም ብዙኀንን በሚከፋፈሉ እና በተለምዷዊ የፖለቲካ ሒደቶች መፍታት ያልተቻሉ ጉዳዮችን ወደ ሕዝበ ውሳኔ መውሰድ የተለመደ ነው። እንደ ምሣሌ የአውሮፓ ኅብረትን ለመቀላቀል ሕዝበ ውሳኔ ያላደረገችው እንግሊዝ መቆየት እንዳለባት እና እንደሌለባት ለመወሰን ሁለት ጊዜ ሕዝበ ውሳኔ አካሔዳ በሁለተኛው ለመልቀቅ ወስናለች።
በኢትየጵያ ቀደምት ሊባል የሚችለው የሕዝበ ውሳኔ የተካሔደው በደርግ ዘመነ መንግሥት የተካሔደው እና ኢትዮጵያ በአንድ የኮሙኒስት ፓርቲ እንድትተዳደር የሚወስነው ሕገ መንግሥት “81 በመቶ ድጋፍ አግኝቶ ፀደቀ” የተባለበት ሕዝበ ውሳኔ ነበር። ከዚያ በኋላ የኤርትራ መገንጠል የተወሰነበት ሕዝበ ውሳኔ የተከተለ ሲሆን፥ “ነፃነት” ወይስ “ባርነት” የሚል አማራጭ በማቅረብ የተካሔደው እና 99 በመቶ ተሳታፊዎች “ነፃነት” መርጠው የተጠናቀቀው ሕዝበ ውሳኔ ነበር። የመጀመሪያው ሕዝበ ውሳኔ በወታደራዊ አምባገነናዊ ስርዓት እና በእርስ በርስ ጦርነት መሐል የተካሔደ እንደመሆኑ መጠን ዜጎች ያለ ስጋት፣ ሁሉም አማራጮች ቀርበውላቸው፣ ተወያይተውበት እና ተረድተውት የሰጡት ሕዝበ ውሳኔ ነው ልንለው አንችልም። ሁለተኛውም በተመሳሳይ መንገድ ከእርስ በርሱ ጦርነት በኋላ በጦርነቱ ድል የተቀናጀው ኀይል በተግባር ሥፍራውን ተቆጣጥሮ ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ ያካሔዳቸው ስለሆኑ ነፃ ሕዝበ ውሳኔ ነው ለማለት ይቸግራል። ይልቁንም ለተመልካች ይምሰል የተተወኑ ፖለቲካዊ ትዕይነቶች ነበሩ ማለት ይቻላል።
በየክልሎቹ ልዩ ዞኖችን ለማቋቋም ከዚያ በኋላ የተካሔዱት ሕዝበ ውሳኔዎችም በተመሳሳይ መልኩ የተጠናቀቁ ነበሩ። ሕዝበ ውሳኔ ተካሔዶባቸው የተለየ ውጤት የተገኘባቸው ቢኖሩ ድንበር ለማካለል የተሞከሩት ብቻ ናቸው። ካለፉት የኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ሒደቶች የምንረዳው እስካሁን የተካሔዱት ዐቢይ ሕዝበ ውሳኔዎች የተካሔዱት ለይስሙላ መሆኑን ነው።
አሁንም የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ከመካሔዱ በፊት የሲዳማ ዞን ፖለቲከኞችም ይሁን የደቡብ ክልል ፖለቲከኞች የተሥማሙ ይመስላል። በዝግ ከተካሔደው የደኢሕዴን የቅርብ ጊዜ ስብሰባ የተገኙ የተባሉት “ምሥጢራዊ” መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ንቅናቄው የሲዳማን ክልልነት ተቀብሎታል። ይሁንና በክልሉ ከ10 በላይ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ቢያነሱም ንቅናቄው የሲዳማን ብቻ አንስቶ መወያየቱን በመቃወም የወላይታ ዞን አስተዳዳሪዎች ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን ተናግረዋል። ስለሆነም፣ አሁንም ሲዳማን በተመለከተ የሚካሔደው ሕዝበ ውሳኔ በገዢ ቡድኖች ሥምምነት ብቻ ነው። ውጤቱንም አስቀድሞ መገመት አይቸግርም።
ለሕዝበ ውሳኔ ምን ያስፈልጋል?
በርግጥ በኢትዮጵያ የክልልነት ጥያቄን ለማስተናገድ የግድ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ እንደሚገባት የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ያዛል። ነገር ግን ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ምን ያስፈልጋል የሚለው ላይ ውይይት ጨርሶ አይደመጥም። ሕዝበ ውሳኔዎች መራጭ ብዙኀን ከምንና ከምን እንደሚመርጡ፣ እያንዳንዱ አማራጮች ያላቸው የሚያገኙት ጥቅም እና የሚደርስባቸው ጉዳት ምን እንደሆነ፣ ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ሁነቶች በቂ መረጃ ሊኖራቸው ይገባል። ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ሥምምነት የተደረገው እነዚህ አማራጮች ለብዙኀን ተገልጸው ከተጠናቀቁ በኋላ ነው የሚል መከራከሪያ ካልተሰጠ በስተቀር፥ ሕዝባዊ ግጭቶች እና አለመረጋጋት ባለበት ሁኔታ የሚካሔድ ሕዝበ ውሳኔ የይስሙላ ከመሆን በስተቀር ነጻ የሕዝብ ውሳኔ ሊባል አይችልም። በሌላ በኩል ውጤቱን ሁሉም ሰው ያለ ምንም ጥርጥር የሚያውቀውን ሕዝበ ውሳኔ ማሰናዳት የሕዝብን ወጪ ማባከን ስለሚሆን፥ ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊም ቢሆን በፖለቲካ ድርድር መፍታት የተሻለ አማራጭ ሊሆን ይችላል።
ከሕዳር 2012 በፊት ሕዝበ ውሳኔው ይካሔዳል?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማን ሕዝበ ውሳኔ ከሕዳር ወር በፊት አካሒዳለሁ ብሎ ቃል ገብቷል። ይሁንና ይህንን ለማድረግ ያስፈልጉኛል ያላቸውን ሁኔታዎችን አስቀምጧል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የደኅንነት እና ፀጥታ ጉዳይ ነው። በቅርቡ እንደተመለከትነው የሕዝበ ውሳኔው መራዘም ያላስደሰታቸው ወጣቶች ፈጥረውታል በተባለው ግጭት በዞኑ የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል፣ ንብረት ወድሟል። ይህ ግጭት የተከሰተበት ጊዜ ሕዝበ ውሳኔው ይካሔዳል ተብሎ ከሚገመትበት አምስት ወር ባልበለጠ ጊዜ እንደመሆኑ መጠን ነጻ ሕዝባዊ ውይይቶችን ለማካሔድ አስቸጋሪ ወቅት ነው።
ዞኑ መልሶ ተረጋግቶ እና በበቂ ሁኔታ ነዋሪዎቹን አወያይቶ ለሕዝበ ውሳኔው የማዘጋጃ ጊዜ አለው ወይ? በዞኑ የክልልነት ጥያቄውን የሚቃወሙ ነዋሪዎች በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደምን ሐሳባቸውን መግለጽ ይችላሉ? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚጠቁመን ሕዝበ ውሳኔው በጊዜው የሚካሔድ ቢሆንም እንኳን ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እንደታዩት ሕዝበ ውሳኔዎች የይስሙላ የመሆኑ ዕድል ሰፊ ነው።
አሁንም ድርድር…
ሕገ መንግሥታዊ ነው በሚል የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ከተካሔደ፥ ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረቡ የደቡብ ክልል ዞኖችም ተመሳሳይ ምላሽ ማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነው የሚሆነው። ቸል ከተባሉ ተቃውሞ መቀስቀሱ አይቀርም፤ ጥያቄያቸው መልስ ይሰጠው ከተባለ በደቡብ ክልል ብቻ ደርዘን የሚያክል ሕዝበ ውሳኔ ማካሔድ ሊያስፈልግ ነው። ያውም ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ። ይህ አለባብሰው ሊያልፉት የሚችሉት ነገር አይደለም። ስለሆነም፣ የደቡብ ክልል ክልልነት ጥያቄ አቅራቢዎችን በሙሉ ያካተተ የልኂቃን ድርድር በገለልተኛ እና በሚያምኗቸው ወገኖች አመቻችነት እንዲዘጋጅ ተደርጎ እና ለክልሉ አዲስ አወቃወቀር በመፍጠር ለሁሉም ነዋሪዎች በበቂ ሁኔታ ውይይት የተደረገበት ሕዝበ ውሳኔ አንዴ ማካሔድ የተሻለ ይበጃል።
|| ከ ዲ.ደብሊው የተወሰደ ||
በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የዶይቸ ቬለ (DW)ን አቋም አያንጸባርቅም።