የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም

እነ ብ/ጀነራል ተፈራ ማሞ ለተጨማሪ አስር ቀናት በማረሚያ እንዲቆዩ ተወሰነ

በባህርዳር ከተማ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ (ርዕሰ መስተዳደሩን ጨምሮ) በተፈጸመው ግድያ ተጠርጥረው ከታሰሩ ሰዎች መሐል ሃምሳ ሰባቱ ሲለቀቁ ቀሪዎቹ ፖሊስ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ለተጨማሪ አስር ቀናት በዕስር እንዲቆዩ ተወስኗል፡፡

በእዚህም መሰረት ብ/ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ኮ/ል አለበል አማረና ኮ/ል በአምላኩ አባይን የመሳሰሉ የክልሉ ከፍተኛ የጸጥታ ሓላፊዎች፤ እንዲሁም ፖሊስ ድርጊቱን ከማቀነባበር እስከ ማስፈጸም ዋነኛ ተዋናይ ናቸው ካላቸው ከብ/ ጀነራል አሳምነው ጽጌ ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቸው በሚል የተጠረጠሩ ሌሎች ግለሰቦች አሁንም ከዕስር አልተፈቱም፡፡

እነብ/ጀነራል ተፈራ ማሞ በጊዜው የተፈጠረውን ችግር ለመከላከል ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸው እየተካሄደ ባለው ሁኔታ መረጋገጡና እስካሁንም በወንጀሉ ተባባሪ መሆናቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ አለመገኘቱን ጠበቆቻቸው በፍርድ ሂደቱ ላይ አሰምተዋል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በጉዳዩ ተሳታፊ አለመሆናቸው እየተካሄደ ባለው ምርመራ የታየ በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጣቸው መዝገቡ ተዘግቶ እንዲለቀቁ ጠበቆቻቸው ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ጉዳያቸው ተጣርቶ በነጻ ከተለቀቁት በተጨማሪ ፖሊስ ያልጨረስኩት ማጣራት ለብኝ ምርመራ አለ በሚል አስራ አራት ቀን ጊዜ ቀጠሮ ቢጠይቅም ፤ ችሎቱ ምርመራውን ለማጠናቀቅ  አስር ቀን በቂ መሆኑን በመግለጽ ለሐምሌ 29 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ እና እስከዚያው ድረስ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በሰኔ አስራ አምስቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ወቅት በጀነራል አሳምነው ቀጥተኛ ትዕዛዝ ባሉበት ቦታ ታግተው እንዲቆዩ ተደርገው የነበሩት ብ/ጀነራል ተፈራ ማሞበተለይም የልዩ ኃይሉ አባላት በአሳምነው ጽጌ ቁጥጥር ስር ሆነው የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ  በስልክ ግንኙነቱን መስበር እንደቻሉና ፌደራል ፖሊስና መከላከያ ከመድረሱ በፊት ችግሩን በማክሸፍ ረገድ ዓይነተኛ ሚና መጫወታቸው እየተነገረ የነበረው በአደጋው ማግስት እንደሆነ ይታወሳል፡፡

እስካሁን ድረስ ለምን እንደታሰበ ማረጋገጥ ያልተቻለውንና ሰኔ 15 ቀን ምሽት ላይ በጀነራል አሳምነው ጽጌ ትዕዛዝ ወደ ጎንደር እየተጓዘ የነበረውን ሁለት ኤፍ.ኤስ.አር መኪና ሙሉ የታጠቀ የልዩ ኃይል አባላትን ወደባህርዳር እንዲመለስ ከማድረግ ባሻገር “ከእንግዲህ ወዲያ የትኛውም የልዩ ኃይል አባል ከእኔ ውጪ የሌላ ሰው ትዕዛዝ መቀበል አይችልም” በማለት የልዩ ኃይሉን ከጥፋትና ከተጨማሪ ስህተት በመታደግ፤ ብሎም የአሳምነው ጽጌን እንቅስቀሴም በመግታት ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡

ብ/ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ኮ/ል አለል አማረና ኮ/ል በአምላኩ አባይ በተጠቀሰው ቀን በጀነራሉ ታማኝ ወታደሮች አማካይነት እንዲታገቱ የተደረገ ቢሆንም፤ ባሉበት ቦታ ሆነው ችግሩን ለመቅረፍ ያደረጉት ከፍተኛ ትግል በምርመራ ወቅት ከመረጋገጡ ጋር ተያይዞ ችሎቱ ክሳቸውን ያቋርጣል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አድሮ ነበር፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ፖሊስ 218 ሰዎችን አስሮ ከቆየ በኋላ ጉዳያቸው ተጣርቶ 103 ሰዎች ቀደም ሲል ተለቀዋል፡፡ ከዛሬው ችሎት ውሳኔ በኋላ ደግሞ 57 ሰዎች ይለቀቃሉ፡፡

“ ኦሮሞና ማዳጋስካርን የሚያገናኝ ፖለቲካ እንዳለ አላውቅም”

  የትነበርሽ ንጉሴ

በድሬደዋ ተካሂዶ በነበረው “የአዲስ ወግ” ምክክር መድረክ ላይ ብሔር ሚለው ቃል ሃገር የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ ለማስረዳት የተጠቀመችው ቋንቋ ወይም ምሳሌ በተዛባ መንገድ በመተርጎም ስብዕናዋን  የሚጋፉ አላስፈላጊ አስተያየቶችን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መመልከቷ በእጅጉ እንዳበሳጫት የትነበርሽ ንጉሴ ገለጸች፡፡

ዎች “ልበ ብርሃኗ” እያሉ የሚጠሯት የት ነበርሽበድሬደዋው የምክክር መድረክ ላይ “ አማራ፣ ኦሮሞ፣ እንዲሁም ትግሬ የትም ይኖራል፤ኦሮሞ የትም ይኖራል፡፡ ኦሮሞ ቋንቋ ነው እንጂ ብሔር አይደለም ፤ትግርኛም እንዲሁ፡፡ ማዳጋስካር ደሴት ውስጥ ኦሮሞ አግኝቼ አውቃለሁ” በማለት የጠቀሰችው ምሳሌ ጽንፍኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች ነገሩን በሌላ አቅጣጫ በማዞር ውዥንብር እየፈጠሩ  መሆናቸው በይፋ እየታየ ነው፡፡

“ኦሮሞ የትም ይኖራል ብዬ አንድ ምሳሌ ሰጥቻለሁ” የምትለው  የትነበርሽ፤ “ ምሳሌ ያደርገኳት ሃገር ማዳጋስካር ናት፡፡ እኔ ለማለት የፈለግሁት ደሴት ውስጥ እንኳን ሰው ይገኛል እንኳን አገር ውስጥ የሚል ነው፡፡እውነት ለመናገር  እስከ ትናንት ጠዋት ድረስ ኦሮሞና ማዳጋስካርን የሚያገናኝ ፖለቲካ እንዳለ አላውቅም፡፡ ባውቅ ኖሮ እንደዚህ ዓይነት ምሳሌ አልጠቀምም፤ ሌላ አገር መጥራት እችል ነበር፡፡ ማሳየት የፈለግሁት እንኳን ትልልቅ ሃገራት ማዳጋስካር ደሴት ውስትኦሮሞ አግኝቼ አውቃለሁ የሚለውን ነው ”  በማለት ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ እውነታውን በግልጽ አስቀምጣለች፡፡

ይህንን ቃል የመዘዙ ሰዎች ስለተነሳው ሃሳብ ሳያወሩ፤ ኦሮሞ ማዳጋስካር አግኝቻለሁ የሚለው  አይቻለሁ” ወደሚል ተቀየረ፡፡ እሷ እንዴት ነው ያየቸው? ወደሚል የዓይነ ስውርነት ክርክር ተገባና ዛ መንገድ የራሳቸውን ሃሳብ ማራመድ የሚፈልጉ ሰዎች አቅጣጫውን በመቀየር ነገሩን በፍጥነት ሊያራግቡት እንደቻሉም ተናግራለች፡፡

“መጀመሪያ ላይ ያላልኩት ነገር አለች መባሌና የኔ ዕምነት ባልሆነ ነገር ሲወነጅሉኝ ተበሳጭቼ ነበር፡እያደር ሳስበው የምንታገለው ለሃሳብ ነፃነት እስከሆነ ድረስ ተውኩት፡፡ እነዚህ ሰዎች ኦፖርቹኒስቲክ ናቸው፤ አጋጣሚ እየጠበቁ ታዋቂ፣ተሰሚ ለመሆን  የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው፡፡” በማለት በብሔርተኝነት ክፉ ደዌ የተለከፉ ሰዎች የዜግነት ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ታዋቂ ሰዎች ብሔርን የሚገልፁበትን ቋንቋ የተሳሳተ ትርጓሜ እንዲሰጠው ሆን ብለው ቃለትን እንደሚያዛቡም አስታውቃለች፡፡

የቁልቢ ገብርኤል አመታዊ የንግስ በዓል በሰለም ተጠናቋል

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ  ሐምሌ 19 ቀን የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል አመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም ጸጥታ ችግር  መጠናቀቀቁ ተገለጸ፡፡

በሐረር ከተማ የተደራጁ ቡድኖች ፈላጭ ቆራጭ የሆኑበት ሂደት በየጊዜው እየተጠናከረ መምጣቱ፣በተደጋጋሚ የክልሉን ባንዲራ እያነሱ የኦነግን  አርማ በይፋ መተካታቸውጋር ተያይዞ የተነሱ ግጭቶች ተድበስብሰው የቆዩበት ሁኔታ መኖሩ ህገ ወጥ ቡድኖቹ ይህንን ክብረ በዓል ተገን አድርገው ሁከት ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ፈጥሮ ነበር፡፡

በተጨማሪም በዘንድሮው የረመዳን ጾም ወቅት  በድሬደዋ ከተማ በዕለተ እሁድ በተከናወነ አንድ የክርስቲያን ሰርግ ላይ “ለሙሽሮቹ መኪና መንገድ ዘጋህ” በሚል በባጀጅ ሹፌሮችና በሰርገኞች መሀል የተፈጠረው አለመግባባትከ”አፍጥር” በኋላ  ወደለየለት የሃይማኖት ጸብ ተሸጋግሮበከተማዋ ለሁለት ቀናት የዘለቀ የሙስሊሞችና የክርስቲኖች ግጭት መከሰቱና ሰዎች መጎዳታቸው ዘነጋም፡፡

በተለይም የቁልቢ ተጓዦች በብዛት በድሬደዋ ከተማ የሚያርፉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በሃገሪቱ ያልተረጋጋ ስርዓት እንዲኖር የሚሹ ኃይሎች አጋጣሚውን በመጥፎ ጎኑ ሊጠቀሙበት ይችላል የሚል ጥርጣሬ በጸጥታ  ኃይሎች ዘንድ የነበረ ቢሆንም በትናንትናው ዕለት የተከበረው ቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በአል ግን በሰላም ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

መንግስት አመታዊ የንግስ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ  በማሰብ የጸጥታ ኃይሉ በመከላከያ፣ከሐረርና ድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን በተውጣጡ ኃይሎች እንዲዋቀር በማድረግ ከፍተኛ ቁጥጥርና ጥበቃ ሲያካሂድ ይቷል፡፡

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ሓላፊ ኮማንደር ሰለሞን ሙሊሳ በአመታዊ የንግስ በዓሉ ላይ የእጅ ስልክ፣ጫማና የተሸከርካሪ ስፖኪዮ ከመሰረቃቸው ውጪ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡ በጊዚያዊነት ለበዓሉ የተቋቋመው ችሎትም ወንጀሉን በፈጸሙና በሰባት መዝገብ በቀረቡ ተከሳሾች ላይ ከስምንት ወር እስከ አንድ ዓመት ከስምንት ወር የሚደርስ  የእስራት ቅጣት ብይን ሰጥቷል፡፡

ኤል ቲቪ በኪሳራ ምክንያት ከ20 በላይ ሠራተኞች ሊያበርር ነው

ኤል ቲቪ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኪሳራ ገጥሞኛል በሚል ከ20 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞቹን ከስራ ገበታቸው ሊያሰናብት መሆኑን ታማኝ ምንጮቹን  በመጥቀስ አዲስ ማለዳ አስነብቧል፡፡ በ2010 ዓ.ም በተደረገው የውጪ ኦዲተር ሪፖርት መሰረት ድርጅቱ መክሰሩ ተረጋግጧል፡፡ ድጅቱ እስካሁን የሠራተኛ የወር ደምዎዝ እና የሳተላይት ክፍያን ለመሸፈን ባለመቻሉ ምክንያት የተወሰኑ ሠራተኞችን ቀንሷል፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ብሩ ግን ሠራተኞቹ የተቀነሱት በመስሪያ ቤቱ በተደረገው ዓመታዊ ግምገማ የብቃት ማነስ ስለታየባቸው እንደሆነ በመግለጽ በቅርብ ቀናት ባረሩትን ሠራተኖች ወቀሳ ያጣጥላሉ፡፡ ይሁንና በድርጅቱ ላይ የደረሰውን ኪሳራ ግን ሓላፊው አምነዋል፡፡

ኤል ቲቪ ከሶስት ዓመት በፊት በሙከራ ስርጭት ስራ የጀመረ ሲሆን፤ በዶክተር ገመቺስ ቡባ ባለቤትነት የተጀመረህ ቴሌቪዥን ጣቢያ መቀመውን ያደረገው በሰሜን አሜሪካ ነው፡፡ ኤል ቲቪ በአገር ውስጥ ተገቢውን የስርጭት ፍቃድ ሳያገኙ (በ2008 ዓ.ም) ስርጭት ከጀመሩ ሦስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መሀል አንዱ እንደነበረ ይታወሳል፡፡

ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ያስወጡት ግድቦች ተበላሹ 

በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መካከለኛው እና ታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ላይ  የተገነቡት  የከሰምና ተንዳሆ የመስኖ ግድቦች ለተደጋጋሚ ብልሽት እየተዳረጉ መሆናቸው ታወቀ፡፡

ግድቦቹ ተሰርተው እስከሚጠናቀቁ ተይዞላቸው የነበረው 5 ነጥብ 1ቢሊዮን ብር ወጪ ወደ 11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ከፍም ብሏል፡፡ የመስኖ ግድቦቹ ወጪ ከ6ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር 120 ነጥብ 4 በመቶ ማሪ ማሳየቱን በተመለከተ የፌደራል ዋና ኦዲተር የ2010 በጀት ዓመትን ሒሳብ አያያዝ ለፓርላማው ባቀረበበት ወቅት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ብዙነህ ቶልቻ ግንባታውን በተያዘለት የጊዜ ገደብና ወጪ አጠናቀው ለሚያስደድረው አካል እንዳስረከቡ እንጂ በዋና ኦዲተር ተገኘ ስለተባለው የ120 በመቶ ጭማሪ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ኹለቱም ግድቦች የተጠናቀቁት ከዓመታት በፊት ቢሆንም አሁንም በሚያጋጥማቸው የቴክኒክ ችግር ምክነያት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡        

LEAVE A REPLY