ችግኞችን ለማፍላት 40 ቢሊዮን ብር ወጪ ሆኗል ተባለ
በያዝነው ዓመት የክረምት ወር በጠቅላላው ይተከላሉ ተብለው ለሚጠበቁት 4 ቢሊየን ችግኞችን ለማፍላት 40 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ተደርጓል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ እስከ ጳጉሜ መጨረሻ በምታደርገው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻና በመላ ሃገሪቱ ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ 4.7 ቢሊዮን ችግኞች መፍላታቸው ተገልጿል፡፡ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ በተከናወነውና ሃገሪቱ በአለም የክብር መዝገብ ላይ በአዲስ ምዕራፍ እንድትፃፍ አስችሏታል በተባለው ዘመቻ፣ ከ23 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውን እንደተሳተፉበትም እየተነገረ ነው፡፡
የብሔራዊ ደን ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ተፈራ ለቢቢሲ እንደገለፁት 40 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የወጣበት የዘንድሮው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም፤ ባለፉት ሶስት ወራት መርኃ ግብር ተዘርግቶ እንደተሰራና ዝግጅቱ ግን አመቱን ሙሉ ሲካሄድ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ችግኞቹ ከክምችት ጣቢያው ወጥተው ከመሰራጨታቸው አኳያ ለእያንዳንዱ ስነ ምህዳር አካባቢ የትኛው ይጠቅማል? የሚል ጥናት አለመደረጉን ግን ሓላፊው አልሸሸጉም፡፡ ከዚህ በመነሳትም አንዳንድ ችግኞች ካላቸው የአካባቢ መስተጋብር አኳያ በተሻለ ሁኔታ ሊፀድቁ የሚችሉበት ዕድል መኖሩም ተነግሯል፡፡
“ችግኝ ተከላው ካለ በቂ ዝግጅት፣ በስፋትና በዘመቻ የተካሄደ ከመሆኑ አንፃር የህዝቡን መነቃቃት መፍጠር የዘንድሮው ተከላ ዋነኛ ትርፍ መሆኑ ታውቋል:: ለዝንድሮው ችግኝ ተከላ ዝግጅት ለአራት ቢሊየን ችግኞች 40 ቢሊየን ብር መውጣቱን ሓላፊው ይፋ አድርገዋል፡፡
የምዕራብ ጎንደር ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ተመለሱ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተከስቶ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው የቆዩ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው እንደተመለሱ ተነገረ፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መንበሩ አዳሙ በዞኑ በተለያዩ ስፍራዎች በተነሱ ግጭቶች 3.500 ገደማ ቤቶች በመቃጠላቸው መንግስት በራሱ ወጪ 3.200 የሚሆኑ ቤቶችን መልሶ በመገንባት ተፈናቃዮቹ እንዲመለሱ አድርጓል ብለዋል፡፡
የሦስት መቶ ቤቶች ባለቤቶች ግን እንጨት ስላላቀረቡ ቤቱ አልተሰራላቸውም፡፡ ለእነዚህ ሰዎች መንግሥት አሁን ላይ በጀት ይዞ ቤታቸውን ሠርቶና አጠናቆ ለማስረከብ የእንጨት ግዥ እያከናወነ መሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ 300 የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ሥራዎች ባለመጠናቀቃቸው ጠገዴ ወረዳ “ሶርቃ” በሚባል ጊዜያዊ መጠለያ እንዲቆዩ መደረጋቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህም መሰረት ከ“ሶርቃ” በስተቀር ተፈናቃዮች ይገኙባቸው የነበሩ ሁሉም ጣቢያዎች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በዓለም ላይ አዲስ ከተፈናቀሉ ሰዎች መካከል ኢትዮጵያውያን ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡ የተፈናቃዮች ቁጥር 1.5 ሚሊዮን ሲሆን 98 በመቶ የሚሆኑት እዚያው በሃገር ውስጥ የተፈናቀሉ ናቸው፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው አካል በተለያዩ አካባቢዎች በማህረበሰቦች መካከል ባለፈው ዓመት ያጋጠሙ ግጭቶች የተፈናቃዩን ቁጥር እንዳናሩት አመልክቷል፡፡
ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ በሲዳማ ዙሪያ ዕርምጃ እየወሰደ ነው
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰተው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የሚጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን በክልሉ የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡
በተለያዩ የሲዳማ ከተሞች ለተከስቱት አስቃቂ ግድያና ውድመት የተጥርጠሩ ዘጠኝ ሰዎች ፍርድቤት ቀርበዋል:: የሲዳማ ሚድያ ኔትዎርክ ዋና ሰራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ደጉየ ይገኝበታል:: አሁንም በሲዳማ ዞንና አካባቢው ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር ንክኪ አላቸው በሚል በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ናቸው፡፡ የተወሰዱ ንብረቶችም ለባለቤቶቹ የማስመለስ ስራ ጎን ለጎን እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ከ12 ቀናት በፊት የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ስራውን እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዜጎች ላይ ጥቃት መፈፀም፣ ያልተፈቀዱ ሰልፎችን ማድረግ፣ የሰላም ማደፍረስ እንቅስቃሴ ማሳየትና ማድረግ በኮማንድ ፖስቱ በጥብቅ ተከልክለዋል፡፡
ኢንጂኔር ታከለ ኡማ በቀጣይ ዓመት አዲስ አበቤን የቤት ባለቤት አደርጋለሁ አሉ
መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ያለው የአዲስ አበባ ም/ቤት በቅርቡ አዲስ የቤቶች ልማት ፕሮግራም እንደሚጀምር ገለፀ፡፡
የ2011 አፈፃፀም ሪፖርት በተሰማበት በዛሬው ጉባኤ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ችግር ለመቅረፍ አዲስ የቤቶች ፕሮጀክት እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡1.500 ሄክታር መሬት ለዚህ ተግባር የተዘጋጀ ሲሆን፣ የግሉ ዘርፍም በፕሮጀክቱ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በ2011 ዓ.ም በጀት ለልማት ተወስደው የቀሩ 25 ሺኅ ቦታዎች (600 ሄክታር) ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል ያሉት ከንቲባ ታከለ ኡማ፣
በተካሄደው የመኖሪያ ቤቶች ቆጠራ፤ በሕገ ወጥ የተያዙ 3 ሺህ የቀበሌ ቤቶች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦችና አረጋውያን መከፋፈሉን አረጋግጠዋል፡፡
163 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረናል ያሉት የከተማዋ አስተዳዳሪ፣ በ2012 ዓ.ም ደግሞ ለ250 ሺህ ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳር ጎዳና ላይ የነበሩ 10 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችና ሕፃናትን ከመንገድ ላይ በማንሳት የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ የተቀሩት ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን ያስታወሱት ም/ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፣ አዲስ በቀረፁት የቤቶች ልማት ፕሮጀክት አዲስ አበቤን የቤት ባለቤት ለማድረግ እንደተዘጋጁ ከወዲሁ ይፋ አድርጓል፡፡
የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልሎች የፀጥታ ጉባኤ ተጀመረ
ምስራቅ ኢትዮጵያ ክልሎች የጸጥታ ጉባኤ ዛሬ ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በሀረር ከተማ መጀመሩን የሀረሪ ክልል የመንግስት ጉዳዮች ቢሮ ይፋ አድርጓል፡፡
በእዚህ ጉበኤ ላይ የኦሮሚያ፣ የሀረሪ፣ የሶማሌ፣ የአፋር ክልሎች እና የድሬድዋ ከተማ መስተዳድር የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም የፌደራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮችም በጉባኤው ታድመዋል፡፡
የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልሎች የፀጥታ ጉበኤ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የሕግ የበላይነትን የማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ እንቅስቃሴና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የትግራይ ዓለም አቀፍ ዲያስፖራ ፌስቲቫል ዛሬ ተከፈተ
ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የትግራይ ዓለም አቀፍ የዲያስፖራ ፌስቲቫል በመቐለ ተከፍቷል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልም ጉባኤውን አስጀምረዋል፡፡
የትግራይ ዓለም አቀፍ የዲያስፖራ ፌስቲቫል የክልሉን ህዝብ ከድህነት ለማላቀቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚካሄድ ተሰምቷል፡፡ በዛሬው ዕለት የፌስቲቫሉ አካል የሆነ አውደ ርዕይም ተከፍቷል፡፡ የትግራይ ዓለም አቀፍ ዲያስፖራ ፌስቲቫል ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡