ትህነግ/ሕወሓት ቦታውን በኦዴፓ ተቀምቷል። ኦዴፓ ትህነግን በእስር መሰል ጉዳዮች ለማስገበር ጥረት አድርጓል። የተሳካለት አይመስልም። ትህነግ ድሮ ኦህዴድን ያደርገው እንደነበረው ኦዴፓ በትህነግ ላይ አዛዥ መሆን አልቻለም። ይልቁን ሁለቱ ድርጅቶች “ቀዝቃዛ ጦርነት” ውስጥ ገብተዋል።
“ቀዝቃዛው ጦርነት” የሚባልው የዓለም ጦርነት ትልቁ መገለጫው ሀገራት የባላንጣቸውን ተቃዋሚዎች ከመቸውም ጊዜ በላይ በይፋ በመደገፍ የውክልና ጦርነት ያደረጉበት ወቅት ነበር። የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች ከአሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አንደኛው የአንደኛውን ተቃዋሚ በመደገፍ ተጠምደዋል።
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የትግራይ ተቃዋሚዎችን ወደ ቤተ መንግስት በማስጠጋት ሲሰሩ ቆይተዋል። እነ አብርሃ ደስታ፣ እነ አረጋዊ በርሄና ሌሎቹም ወደ ቤተ መንግስት መጠጋት ሲያበዙ ትግራይ ውስጥ ግን መንቀሳቀስ አልቻሉም። ከጠ/ሚ ዐቢይ እና የ”ለውጥ ኃይሉ” ጋር ያላቸው ቅርበት እንደ ክህደት የተቆጠረባቸው የትግራይ ተቃዋሚዎች ለትህነግ ባዕዳ የሆነችው አዲስ አበባ ላይ እንደፈለጉ መንቀሳቀስ ቢችሉም መቀሌ ላይ የሚደርስባቸው ወከናና እንግልት የከፋ ሆኗል። አረጋዊ በርሄ መቀሌ ላይ የገጠማቸውን ወከባ ማስታወስ ይቻላል። በቅርቡ የትግራይ ተቃዋሚዎች በሚዲያ ቀርበው “ደርግ ያልከለከለንን መብት ሕወሓት እየከለከለን ነው” ሲሉ አማርረዋል።
በተቃራኒው የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስት የኦሮሞ መንግስት እንዲመሰርት ቀን ከሌት የሚደክሙት የኦሮሞ ተቃዋሚዎች ሰሞኑን ወደ ትግራይ አዘውትረዋል። እነ ለማ መገርሳ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደርነት ሲነሱ በእነ ዐቢይ አህመድ ላይ ጠንካራ ትችት ያሰሙት እነ በቀለ ገርባ ሰሞኑን ከእነ ዐቢይ ይልቅ አሳሪዎቻቸውን መርጠዋል። በተመሳሳይ እነ እዝቅኤል ጋቢሳም ወደ መቀሌ በማምራት ከቀድሞዎቹ ገዥዎች ጋር አጀንዳ ለመጋራት እየጣሩ መሆኑን ለማየት ችለናል።
ትህነግ/ሕወሓት ባወጣው መግለጫ “ከፌደራሊስት ኃይሎች” ጋር ግንኙነቱን እንደሚያጠናክር ገልፆ ነበር። ፌደራሊስት የሚባሉት የኦሮሞ ፅንፈኞች መሆናቸው ነው። በእርግጥ ትህነግ ትግራይን የመገንጠልም ሀሰብ እንዳለው መግለፁ አይዘነጋም። በዚህ ሀሳብ ወደመቀሌ ከሚጋብዛቸው ሀይሎች ጋር ጥሩ ተግባቦት እንደሚኖረው ግልፅ ነው።
ትህነግም ሆነ የኦሮሞ ፅንፈኞች አንድ የሚያደርጋቸው የአማራ ጥላቻቸው ነው። ፌደራላዊ ስርዓቱን የሚያፈርሰው አማራው ነው በሚል ነው ሁለቱም የሚዶልቱት። የአማራ ጥላቻቸው በዋነኝነት የሚያቀራርባቸው ይሁን እንጅ በዚህ ወቅት አንድ የሚያደርጋቸው ከየብሔር ድርጅቶቻቸውና ፖለቲከኞቻቸው ጋር ያላቸው እሰጣ ገባ ነው። የአማራ ጥላቻ ለግንኙነታቸው ማጣፈጫ ነው። ትህነግ ተቃዋሚዎቹ የእነ ዐቢይ አህመድ መጠቀሚያ እንደሆኑ ያስባል። እነ ዐቢይ አህመድ ከላይ እስከታች ኦሮሞን ስልጣን ላይ ባስቀመጡበት በዚህ ወቅት ፅንፈኛ ብሔርተኞች “ተበድለናል” የሚለውን አታሟቸውን ከመደለቅ አልተቆጠቡም። አማራው በሚሰቃይበት በዚህ ወቅት እነ ዐቢይን ጎትቶ አህዳዊ ስርዓት እንዲመሰርቱ እያደረገ ነው ብለው የሚቆዝሙ ሞኞች ሆነዋል። በተመሳሳይ ትህነግም የሚያቃዠው የአማራ ጥላቻ አለቀቀውም። እነ ዐቢይ በአማራው የፖለቲካ ፍልስፍና ተጠልፈው አህዳዊ ስርዓት ሊመሰርቱ እየታተሩ ነው” ብሎ የሌለ እውነታን ፈጥሮ ከኦሮሞ ፅንፈኞች ጋር ሽር ጉድ ለማለት እየጣረ ነው።
በዚህ ሁሉ የተዛባ የፖለቲካ አረዳድ ሁለቱም አማራጭ ያደረጉት የተቀናቃኝን ተቃዋሚ በመደገፍ ቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ መግባትን ነው።
ኦዴፓ እና ትህነግ ሁለት የተለያየ ሀገር እንደሚያስተዳድሩ መንግስታት አንደኛው የሌላኛውን ተቃዋሚ በመደገፍ የወቅቱን የፖለቲካ ፍትጊያ ለማሸነፍ ጥረት እያደረጉ ይገኛል። የትግራይ ተቃዋሚዎች ከመቀሌ ይልቅ አዲስ አበባን ሲመርጡ፣የኦዴፓ ተቃዋሚዎች ወደ መቀሌ ሽርጉድ አብዝተዋል። አማራው ላይ የተፈጠረው ክስተት የሸፈነው ቢመስልም የኦሮሞም ሆነ የትግራይ ፖለቲካ በውስጥ ችግር የተወጠረ፣ በተለይ ተቃዋሚዎችና “ገዥዎቹ” እርስ በእርስ መካካድ ውስጥ የገቡ መሆኑን የሚያሳይ ነው። የራሳቸውን ሕዝብ ይወክላል ከሚሉት ጋር በተፈጠረ ችግር የሌላን ድጋፍ የሚሹ፣ ለሌሎች መጠቀሚያ የሚሆኑ እርሰ በእርሰ የመካካድ ፖለቲካ፣ የድሮው የቀዝቃዛው ጦርነት አይነት የሴራና የውክልና ፖለቲካ ላይ የተጠመዱ መሆናቸውን ሰሞነኛው ክስተት ጥሩ አስረጅ ነው።
የትግራይም ሆነ የኦሮሞ ድርጅቶች ለስሙ ለአንድ ሕዝብ ቆምን ቢሉም በውስጣቸው በተፈጠረ ችግር የአንደኛው ተቃዋሚ የሌላኛው ገዥ ፓርቲ ተላላኪ መሆናቸውን እያየን ነው።