ከጀነራል ሰዓረ ገዳይ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አልተቻለም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአማራ ክልል ባለስልጣናትና ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ላይ ከደረሰው ጥቃት ጀርባ ታስቦ የነበረውን መፈንቅለ መንግስት በፍጥነት መቆጣጠር ባይቻል ኖሮ፣ አስከፊ ነገር ይዞ ይመጣ እንደነበር ትናንት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ላይ ገልጸዋል፡፡
መንግስት የሰዎችን ድምፅ የማፈን ፍላጎት የለውም፣ እንደውም ከዚህ ቀደም በመንግሥት ተዘግተው የነበሩ መገናኛ ብዙሃን እንዲከፈቱ ማድረጉ ለእዚህ በቂ ማሳያ ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በበለፀጉት ሃገራት ሰዎች ኢንተርኔትን ለበጎ እንደሚጠቀሙበት ጠቁመው፣ በእኛ ሀገር ካለው የመረጃ አቀራረብ አኳያ የሰዎችን ህይወት እና ንብረት ከጥቃት ለማትረፍ አስፈላጊ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ ለሳምንት ሳይሆን እስከወዲያኛው ሊዘጋ እንደሚችልም አረጋጠዋል፡፡
ዲሞከራሲያዊ ስርዓት እንዲስፋፋ መንግስታቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሚናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰብኣዊ መብት አያያዝን በተመለከተ መንግስት እየተተቸ ያለበትን ሂደትም አጣጥለዋል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ “አሁን ጨለማ ቤት የታሰረ የለም፣ ሰው አይገረፍም፣ ጥፍርም አይነቀልም” ሲሉ ነው እማኝነታቸውን የሰጡት፡፡
ከሰኔ 15ቱ መፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘ ጀነራል ሰዓረመኮንን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ በህይወት እንዳለና አንገቱ ላይ በጥይት በመመታቱ የህክምና እርዳታ እየተደረገለት እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ግለሰቡ መናገር ባለመቻሉ፣ ከእርሱ የሚፈለገውን በቂ መረጃ እስካሁን ድረስ ማግኘት እንዳልተቻለም ይፋ አድርገዋል፡፡
ተጠርጣሪው ግለሰብ በስልክ ሲገናኛቸው የነበሩ ሰዎችን በሕግ ጥላ ስር በማዋል፣ ከእነርሱ ብዙ መረጃ ሰብስበናል ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ተጨማሪ ጀነራሎችን ለመግደል እንቅስቃሴ ሲደረግ እንደነበር የሚያረጋግጥ መረጃ መገኘቱንም በጋዜጣዊ መግለጫው ተናግረዋል፡፡
ቻይና ለኢትዮጵያ የስንዴና ሩዝ እርዳታ አደረገች
የኢትዮጵያን ቢዝነስ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ የተቆጣጠረችውና ባለፉት በርካታ ዓመታት በብዙቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከሃገሪቱ የሰበሰበችው ቻይና በሰብዓዊ ዕርዳታ ብቅ ብላለች፡፡
ከፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ብቻ የምትታወቀው ቻይና ለኢትዮጵያ 9 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ነው ያደረገችው፡፡
ይህ የሠብዓዊ እርዳታ በተለያዩ ግጭቶች ለተፈናቀሉ፣ እንዲሁም በኤንሊኖ (የአየር መዛባት) ምክንያት ችግር ላጋጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚውልም ተገልጿል፡፡
በዛሬው ዕለት ከቻይና መንግስት የተበረከተው ዕርዳታ ስንዴና ሩዝ ሲሆን፣ ምርቱ በገንዘብ ሲሰላ 7 ሚሊዮን 201 ሺህ 300 የአሜሪካ ዶላር ያወጣል፡፡
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳና የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አድማሱ አበበ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ከሆኑት ሚስተር ታን ጆያን እጅ እርዳታውን ተቀብለዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ልጃገረዶች ጨዋታ”ን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ፤ አማራና ትግራይ ተስማሙ
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ለዘመናት ሲከበር የቆየውን የ”ሻደይ” እና የ”አሸንዳ” በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የትግራይና የአማራ ክልሎች ከስምምነት ላይ ደርሰው፣ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸው ታወቀ፡፡
በቅርቡ ሕወሓት ሰኔ 15 ቀን ለደረሰው ከባድ አደጋና ግድያ አ.ዴ.ፓ ሓላፊነቱን ወስዶ በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ሲል ያወጣው መግለጫና ከአማራ ክልል አስተዳዳሪ አ.ዴ.ፓ የተሰጠው ምላሽ፣ በሁለቱ ክልሎች ሕዝብ መሐል ያለውን ቅራኔ ያሰፋዋል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ አሳድሮ ነበር፡፡
ይሁንና በአማራና ትግራይ ክልሎች በተለያዩ ቦታዎች የሚከበሩትን “ሻዴ” እና “አሸንዳ” በዓሎችን፣ “የኢትዮጵያ ልጃገረዶች ጨዋታ” በሚል ስያሜ፤ በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ቅርስነት ለማስመዝገብ ሁለቱ ክልሎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
ዩኔስኮ በዓሉን ለመመዝገብ በሂደት ላይ መሆኑን የጠቆሙት የቢሮው ሓላፊ አቶ ግዛት አብዩ፤ የሴቶች እኩልነት፣ ነጻነትና አንድነት ተምሳሌት የሆነው የሻደይና የአሸንዳ በዓል ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ከታሪካዊ አመጣጥና አከባበሩ በመነሳት አስረድተዋል፡፡ የትግራይ ክልል ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊት ይህንን ታሪካዊ በዓል በብቸኝነት በክልሉ ስም ለማስመዘገብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ኬንያ ውስጥ “ኢየሱስ ታየ” የተባለው ሀሰት መሆኑ ታወቀ
ሰሞኑን በኬንያ ውስጥ “ኢየሱስ ታየ” በሚል ከማህበራዊ ሚዲያዎች እስከ ተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ድረስ በፍጥነት የተዛመተው ወሬ ሀሰት መሆኑን የሚያረጋግጡ ትክክለኛ ማስረጃዎች በአሁኑ ሰዓት እየወጡ እንደሚገኙ ታወቀ፡፡
“ኪሴሪያን” ተብላ በምትጠራውና ከኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ በደቡብ ምዕራብ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ሥፍራ ነው ኢየሱስ ታየ የተባለው፡፡
ለመታየቱ ማረጋገጫ ነው በሚል ከዜናዎች ጋር በስፋት ምስሉ የተሰራጨውና አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው ግለሰብ፤ ማይክል ጆብ ሲሆን አሜሪካዊው ጆብ በሙያው የፊልም ተዋናይና ሰባኪ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ላይ ንግግር እንዲያደርግ ተደጋጋሚ ግብዣዎች ይቀርቡለታል፡፡
ከተለያዩ ሃገራት በሚቀርቡለት የ“እንፈልግሃለን”ጥያቄዎች ራሱን “ህያው የመጽሐፍ ቅዱስ ሙዚየም” ብሎ የሰየመውና በኦርላንዶ ፍሎሪዳ የሚኖረው ማይክ ጆብ “ዘሆሊላንድ ኤክስፒሪያንስ” በሚል ፊልም ፣እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ተውኗል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ዓይነት የአለባበስ ስልት በመጠቀም፣ የተለያዩ ቪዲዮዎችንና ፎቶግራፎችን በመልቀቅ የሚታወቀው ይህ ግለሰብ፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ቪዲዮ፤ ኬንያ ውስጥ ያሉ የግብርናና የቤት ቁሳቁሶች የሚሸጡባቸው ሱቆች መታየታየቱ “ኢየሱስ በኬንያ ታየ” የሚለውን ሀሰተኛ ወሬ ፈጥሯል፡፡ ቦታውን ከደቡብ አፍሪካ ሱቆች ጋር በማመሳሰል “መሲሁ በማንዴላ ሃገር ተከሰተ” የሚሉ መረጃዎችም በስህተት መሰራጨታቸውን የመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል፡፡
ሲኖትራክ አስመጣለሁ በሚል 73 ሚሊዮን ብር የዘረፉት ግለሰብ ተፈረደባቸው
ለበርካታ ሰዎች የሲኖትራክ ተሸከርካሪዎችን በሶስት ወራት ለማስመጣት ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተቀብለው በመሰወር ክስ የቀረበባቸው፣ የዙና ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ዘሪሁን ጌታሰው የ14 ዓመት ፅኑ ዕስራትና የ300 ሺኅ ብር ቅጣት ተወሰነባቸው፡፡
በአንድ ወቅት በመላ ሃገሪቱ የመነገጋገሪያ ርዕስ ሆኖ የነበረውን የማጭበርበር ተግባር የፈፀሙት ግለሰብ፤ ከአን ድመቶ ዘጠኝ ሰዎች የሰበሰቡትን ገንዘብ ይዘው ከተሰወሩ በኋላ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ከተደበቁበት ዱባይ በኢንተርፖል ተይዘው ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸው ይታወቃል፡፡
የዙና ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ዘሪሁን ጌታሰው ከባድ መኪናዎችን አስመጣለሁ በማለት በሙሉ ክፍያና ግማሽ ክፍያ 73 ሚሊዮን ብር ተቀብለው ተሰውረዋል በማለት፣ ዓቃቤ ሕግ 122 ክሶችን መስርቶባቸው ሲከራከሩ ነበር፡፡
ግለሰቡ ባደረጉት የክርክር ሂደት ከ13 ክሶች ውጪ 109 ክሶችን ማስተባበል ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ዓቃቤ ህግ እንደ ክሱ ዓይነት በሰነድና በሰው ባቀረበባቸው ክሶች ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡
ጉዳዩን ሲመረምር የከረመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት፤ አቶ ዘሪሁን በ14 ዓመታት ፅኑ እስራትና በ300 ሺኅ ብር እንዲቀጡ ማክሰኞ ሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ዙና ትሬዲንግ በሪልስቴት፣ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ሃገር ኤክስፖት በማድረግ፣ አውቶ ሞቢሎችንና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን በማስመጣት ዘርፍ የሚሰራ ድርጅት ነበር፡፡