ከመፈታትህ እንዳልጨቃጨቅ ብየ እንጅ… || መስከረም አበራ

ከመፈታትህ እንዳልጨቃጨቅ ብየ እንጅ… || መስከረም አበራ

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር ተፈቶ ትንሽ ወራት ካስቆጠረ በኋላ በስልክ ስናወራ (አንዳንዴ እየደወልኩ እጠይቀዋለሁ፣ የምከራከረው ነገር ሲኖር ለክርክርም እደውላለሁ) “ከመፈታትህ እንዳልጨቃጨቅ ብየ እንጅ በአንተም በፓርቲህም ላይ የተቃውሞ ፅሁፍም ልፅፍ አምሮኝ ነበር” አልኩት፡፡

“እንዲህ የሚባል ነገር የለም፤ ማንንም ቢሆን መታገል ነው” አለኝ፡፡ “ነገሩ ግን ምንድን ነው? እስኪ ልስማው” አለኝ:: “እዚህ ሃገር የፖሊተካ አዝማሪነት በዝቷል፣ የእናንተ ፓርቲማ ለመንግስት መሲንቆ ይዞ መቆም ነው የቀረው” ብየ ቀጠልኩ፡፡ “አንተስ ብትሆን እንዲህ እንዲህ ሲሆን ዝም ብለህ የምታየው ለምንድን ነው?” ብየ የክርክር ነጥቦቼን አስቀመጥኩ፤ ሲስቅ ይሰማኛል!

የማልቀበለው ነገር ቢበዛም አንዳንድ ነገሮችን ሊያስረዳኝ ሞከረ፤ከነገረኝ ነገር ውስጥ የማልስማማበት፣ የማያሳምነኝ ነገር እንዳለ ነግሬ ንግግራችንን አበቃን፡፡ ሌላም ቀን ክርክር ገጠምኩ! “እንቶኔ ጓደኛህ ስለሆነ አይደል እንዲህ ያለ ፋወል ሲሰራ ዝም ያልከው” አልኩኝ፡፡ “እኔ በፖለቲካ እና  በድርጅት ጉዳይ ጓደኛ ምናምን አላውቅም፤ እንዳልተናገርኩስ በምን አወቅሽ?” ሲል አፋጠጠኝ፡፡ “ከሆነ ጥሩ” ብየ ቋጨሁ፡፡ ከሁልጊዜው ንግግራችን የምረዳው አንዳርጋቸው ምንም ለመባል የተዘጋጀ ሰው መሆኑን ነው፡፡ በአንፃሩ ያመነበት ነገር ለመናገር ማሽሞንሞን የለም፤ ለእኔ በግል የነገረኝን ራሱኑ ሃሳብ በአደባባይ ሲናገር እሰማለሁና የአደባባይ እና የግል ማንነቱ አንድ እና ያው መሆኑ ይገርመኛል፣ እሳቤው ስህተት ነው ብለው ሲያስረዱትም ጠንካራ ሃሳብ ይዘው ከሄዱ የመቀበል ትህትና አለው፡፡ ለእርሱ ወገቤን ይዤስከራከር የምታውቁኝ እኔ ከዚህ ቀደም ለራሱ በስልክ የምሞግተውን ሙግት ዛሬ ለእናንተም ላጋራ ወደድኩ፡፡ አንዲ በህይወት ወጥቶ ለመሞገት በመብቃቱም “ፈጣሪ ይክበር” እላለሁ !

ክርክሬ አቶ አንዳርጋቸው በመፅሃፉ ምርቃት ወቅት በተናገራቸው በሁለት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ አንደኛው “እስክንድርን ለዚህ ትግል ያበቃው ጃዋር ነው” ያለው እጥብቄ የማልስማማበት ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም እውነታው ያ ስላልሆነ! እስክንድር ጃዋር የተባለ አንድ ግለሰብ ያወራውን ብቻ ተከትሎ ትግል ውስጥ አይገባም፡፡ እስክንድርን ትግል ውስጥ ያስገባው ኦዴፓ የተባለ መንግስት የሆነ ፓርቲ አዲስ አበባን የኦሮሞ ለማድረግ እሰራሁ የሚል ቀጥ ያለ መግለጫ ማውጣቱ፣ ይሄው መንግስት በአዲስ አበባ ካውንስል ውስጥ ያልተመረጠ ግለሰብ እንደ ምንም ስቦ አሳስቦ ለትልቅ ከተማ ከንቲባ ከጎረቤት ትንሽ ከተማ አምጥቶ በመሾሙ ነው፡፡ ህጉን ተከትሎ ቢኬድ ከዛው ከአዲስ አበባ ካውንስል ዋና ከንቲባ የሚሆን ሰው በማይጠፋበት ሁኔታ ኦዴፓ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሚል ኢህአዴጋዊ ህገ-ወጥነትን ለማሳካት ሆን ተብሎ የህግ ክፍተት የመፈለግ ዘረኝነት እና መሰሪነት የተቀላቀለበት መንገድ በመሄዱ ነው፡፡ የመታወቂያው ነገርም ንጉስ ኦዴፓ ምክትል ከንቲባ ሲል ባመጣው ሰውየ እጅ የሚያሰራው ሌላ ተጨማሪ ጉዳይ ነው፡፡ የኮየ ፈጬው ክስተት፣ የአዲስ አበባን ድንበር ለማስመር ከስድስት የኮሚቴ አባላት ውስጥ አራቱ የነገሰው ፓርቲ የኦዴፓ አባላት መሆናቸው ወዘተ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ጃዋር በሚታይ መንገድ የተሳተፈው በኮየ ፈጬው ክስተት ነው ያውም ማንን ተማምኖ (ምናልባትም ተመካክሮ) ነገሩን እንዳደረገ መገመት አያዳግትም፡፡ ጃዋር “ኦዴፓ አጋራችን ነው፤ አብረን ነው የምንሰራው” ሲል ጆሮየ ሰምቷል፡፡ ስለዚህ እስክንድርን ለትግል ያስወጣው ግለሰቡ ጃዋር ሳይሆን መንግስቱ ኦዴፓ ነው የሚለው ሚዛን ይደፋል ማለት ነው፡፡ አንዲ ይህን ያጣዋል ብየ አላስብም፣ በዚህ ሁኔታ አህያ ፈርቶ ዳውላ ለመምታት እየሞከረ መስሎ እየታየኝ ነው….አዝናለሁ !

ሌላው ነጥቤ “ከኢትዮጵያዊነት ውጭ አማራ የሚባል ብሄርተኝነት የለም” ያለው ነገር ነው፡፡ ለዚህ ንግግሩ ያመጣው አመክንዮ አማርኛ ቋንቋ ያኔ በአክሱማዊያን ዘመን ከሃረሬ እስከ ጉራጌ ተውጣጥተው በመጡ ወታደሮች የተፈጠረ በመሆኑ፣ አማርኛ ቋንቋ አማራ የሚለው ነገድ ከመፈጠሩ አስቀድሞ መፈጠሩን ነው፡፡ እኔ በዚህ አልስማማም፣ ልክም አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ቋንቋው ከነገዱ ቀድሞ ከዛሬ ስንት ምዕተ-ዓመት በፊት መፈጠሩ ዛሬ ላይ የአማራ ብሄርተኝነት ላለመኖሩ ምስካሬ ሊሆን አይችልም፡፡ የአማራም ሆነ ማኛውም የዘውግ ብሄርተኝነት መነሻው የዘውግ ማንነት መፈጠር ነው፡፡ የዘውግም ሆነ ማንኛውም ማንነት ለለውጥ ክፍት የሆነ እንጅ በአክሱም ዘመን በተከሰተ ጉዳይ ላይ ተተክሎ የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ የዘውግ ማንነት ደግሞ ሰዎች ለራሳቸው በሚሰጡት የማንነት ትርጉም ወይም ሌሎች ለእነሱ በሚሰጡት የማንነት ትርጉም አለያም በሁለቱ መዋጮ ሊፈጠር ይችላል፡፡

የአማራ ብሄርተኝነትን የወለደው የአማራ ማንነት ወደሚባለው ነገር ስመጣ በርግጥ ይህ ማንነት የፖለቲካ ማታገያ እስከመሆን በደረሰ ሁኔታ በራሳቸው በአማሮቹ ያልተጀመረ ሊሆን ይችላል፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት በዚህ ከራስ ለራስ በሚሰጥ የማንነት ትርጉም አልተፈጠረም ቢባል እንኳን በሁለተኛው መንገድ ስለመፈጠሩ ጥርጣሬ ማሳደር አውቆ መተኛት ነው፡፡ “ሁለተኛው መንገድ ምንድን ነው?” ከተባለ ሌሎች አማራ ለሚባለው ህዝብ የሚሰጡት የማንነት ትርጉም ማለት ነው፡፡ ይህ ለአማራ ህዝብ በሌሎች የተሰጠው የማንነት ትርጉም በዋለልኝ ተጀምሮ፣ በኦነግ አልፎ መለስ ዜናዊ ጋር ሲደርስ የ1968ቱን ማኒፌስቶ ያፃፈ እጅግ አደገኛ ትርጉም ነው፡፡ ይህ ትርጉም በአማራ ህዝብ የደም ረዳትነት ወደስልጣን መጥቶ ወንበር ሳይረጋጋ የበደኖ እና የአርባጉጉ የሞት አዋጅ በራሱ በአማራው ላይ ያሳወጀ፣ 77ሽ የአማራ ዘር ሰባት ጉልበቱ እየተቆጠረ ከጉራፈርዳ እንዲፈናቀል ያስደረገ፣ በኢትዮጵያ ዳርቻ አማራው እንደ ኦሪት ለምፃም እንዲሳደድ ያደረገ፣ የሃገሪቱን ሃጢያት ሁሉ ድርሰቱን የፃፈ አማራው ተደርጎ የተተረከበት ይቅር ለማለት የሚያስቸግር የማንነት ትርጉም ነው፡፡ ይህ ከሌሎች ለአማራው የተሰጠው ትርጉም አማራውን ከብሄርተኝነት በላይ ሌላም ካለ የሚያሳስብ በደል ነው፡፡ ሆኖም የአማራ ህዝብ ስነ-ልቦና ወደ ተጋፋጭነት እንጅ ወደ አልቃሻነት የማያደላ ጠንካራ በመሆኑ ብሄርተኝነቱ ከመምጣት ዘግይቶ ኖሯል፡፡ ዘገየ ማለት ቀረ ማለት አይደለምና የአማራ ብሄርተኝነት በክፉ ጉትጎታ ምክንያት ዛሬ እውን ሆኗል፡፡ ይህ ሃቅ ነው! ይህን መካድ አይቻልም፤ ከትናንት ይልቅ ዛሬ ብዙ አማራ ከኢትዮጵያዊነቱ ይልቅ የመሳደጃው ምክንያት የሆነው የአማራ ማንነቱ ላይ እያተኮረ ነው – እድሜ ለመለስ አይባል መቼም !

LEAVE A REPLY