የአዲስ አበባ ባለአደራው ምክር ቤት የፓርላማውን ውሳኔ ተቃወመ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ተወያይቶ ያፀደቃቸው አዋጆችን እንደሚቃወም የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ፓርላማው የአዲስ አበባና የድሬድዋ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ እንዲራዘምና ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታዎችን ለሚለቁ ግለሰቦች የሚከፈል ካሳን ለመወሰን የሚያስችሉ አዋጆችን በአስቸኳይ ጉባኤው ማፅደቁ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
የአዲስ አበባና ድሬድዋ ምክር ቤት ምርጫ መራዘሙ በከተማዎቹ ነዋሪዎች ሆነ በሃገሪቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ያለው የባለአደራው ምከር ቤት ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ፤ አሁን ያለው መስተዳድር መሬትን በሚመለከት ያለ አድልኦ ይንቀሳቀሳል በሚለው ላይ የፍትሐዊነት ጥያቄ አለን ብሏል፡፡
የሚቀጥለው ምርጫ እስኪካሄድ ነገሮች ባሉበት መቆየታቸው የተሻለ ይሆናል ያለው የባለአደራው ሊቀመንበር የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርም ሆነ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፣ የከተማዋን ሕዝብ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እየተንቀሳቀሱ እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡ ይሄ ሥራውን በአግባቡ ማከናወን ያልቻለ መስተዳድር የሥልጣን ጊዜው በአንድ ዓመት ተራዝሞለት፣ ያንንም ጊዜ ስለጨረሰ፤ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትና የሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመሆን ገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደር እንዲያቋቁሙም የባለአደራው ም/ቤት ጠይቋል፡፡
“ምክትል ከንቲባውም ሆኑ በኢህአዴግ የተሞላው የመስተዳድሩ ምክር ቤት፣ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን ተቀብሎ ለማስፈፀም እየሰራ ነው” ያለው እስክንድር ነጋ ከዚህ የተነሳ የከተማዋ ሕዝብ አሁን ሥልጣን ላይ ባሉት አካላት በትክክል ተወክሏል ብሎ እንደማያምኑን ይፋ አድርገዋል፡፡
በሜቴክ ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ተጠያቂ ነው ተባለ
የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በሃገር ሀብት ላይ ላደረሰው መጠነ ሰፊ ዘረፋና ብክነቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተጠያቂ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
የተቋሙ ዳይሬክተር ብ/ጄ/ል አህመድ ሀምዛ “የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክትና የታላቁ ህዳሴ ግድብን በቀጥታ እያዘዘ፣ ለኮርፖሬሽኑ ገንዘብ ሲሰጥ የነበረው፤ እንዲሁም የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር “መንግስት ወስኗል” እያሉ ጉዳዩን ሲያስፈፀሙ ነበር” በማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ለዘረፋና ብክነቱ ተጠያቂ የሚሆንበትን እውነታ ይፋ አድርገዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክም ኮርፖሬሽኑ ከውጭ የሚገዛቸውን ዕቃዎች ሳያወዳድር መግዛት እንዲችል ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የኮርፖሬሽኑን የግዥ ስርዓት የሚወስነው ቦርዱ ሆኖ ሳለ ጣልቃ መግባቱ ትክክል ካለመሆኑም በላይ፤ ኮርፖሬሽኑ የወሰደውን የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ ተከታትሎ አላወራረደም፡፡ ያሉት ጀነራል አህመድ ይህ አሠራር ዕቃ ተገዝቶ ያልተወራረደ 12 ቢሊዮን ብር እንዲኖርና ተቋሙ አስፈላጊውን ዕቃ እንዳይገዛ ጭምር አድርጎታል ሲሉ ተችተዋል፡፡
በቀድሞው የኮርፖሬሽኑ አመራር ዘመን የነበሩ ብልሹ አሰራሮችና የሀብት ብክነቶችን በዝርዝር የተናገሩት ሐላፊ ይህ ሁኔታ በየትኛውም መንግስታዊ ተቋም ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ ሰፊና ውስብስብ ጥፋት እንደሆነም አረጋግጠዋል፡፡
“የታጋይ፣ የወታደር ልጅ በማለት የተቀጠሩ አሉ፡፡ የሠው ሀይል አስተዳደሩ ልጁን ቀጥሮ አግኝተነዋል፡፡ ይህ በየትኛውም የመንግሥትም ሆነ የልማት ድርጅት አሠራር አይታወቅም” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ 179 ሰዎች በሀሰት የትምህርት ማስረጃ ተቀጥረው እንደተገኙና፣ ከነዚህ ውስጥ 12ቱ ወታደሮች መሆናቸውን ጠቁመው ኮርፖሬሽኑ የሠራተኛ ቅጥር የሚያካሂደው በቤተሰብ መስፈርት መሆኑን አጋልጠዋል፡፡
“በብሔራዊ ባንክ መወራረድ ያለበትና ከ960 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ የያዘ ሰነድ በግለሰብ መሳቢያ ተገኝቷል፡፡ አሰራሩ ዝርክርክ ስለነበር፤ በማሸሽ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በእንዝላልነት የጠፉ ሰነዶችም አሉ” ያሉት ጀነራል አህመድ ሀምዛ ኮርፖሬሽኑ የመንግሥት ቢሆንም በየጊዜው የሚያቀርበው ሪፖርት እንደሌለ፣ ለመንግስት የሚታዘዝም እንዳልነበረ፣ የገንዘብ ወሰኑ እንደማይታወቅ፣ እንዲሁ የሆነ ሰው እንደፈለገ የሚያዝበት፣ የማፊያ ዓይነት አሰራር እንደነበረም ገልጸዋል፡፡
“ለዚህ ዝርፊያና ብክነት ዋነኛ ተጠያቂው የኮርፕሬሽኑ ቦርድ ነው፡፡ ተቋሙ ዕቃዎችን መግዛትም ሆነ መሸጥ ሲፈልግ ውሳኔ ማሳለፍ ያለበት ቢሆንም መርከብ ሲገዛና ሲሸጥ የሆቴሎችና ህንፃዎች ግዥ ሲፈፀም ቦርዱ አልወሰነም” ያሉት የሜቴክ ዳይሬክተር ፤ “ኮርፖሬሽኑ የተከመረበት ዕዳ ከባድ ነው፡፡ እዳው የመጣው በኮርፖሬሽኑ ችግር ብቻ ሣይሆን በባንክ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም በመንግሥት ቸልተኝነት በመሆኑ፤ መንግሥት መሰረዝ ያለበትን እንዲሰረዝ፣ ባንክም ብድሩንና ወለዱን ያንሣልን ብለን ባንጠይቅም ቀስ ብለን እንድከፍል እድል ሊሰጠን ይገባል፡፡ በተለይ ባንኩ ከዚህ በፊት የነበረውንም ሆነ አሁን ያለብንን ቅጣት ሙሉ በሙሉ ማንሳት አለበት” ብለዋል፡፡
ይህ የማይሆን ከሆነና ከተቀጣን ባንኩ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላለው ተቋም 17 ቢሊዮን ብር ብድር በመስጠቱ መጠየቅ ይኖርበታልም ያሉት ሓላፊ ሜቴክ ያለበትን ዕዳ ለመክፈል 15 ዓመት እንደሚፈጅና የጉምሩክ ዕዳው ካልተሰረዘ ደግሞ 30 ዓመት ሊወስድ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ለ481 አውሮፕላን አብራሪዎች የሙያ ፈቃድ ሰጠ
የኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ባለስልጣን ለአራት መቶ ሰማኒያ አንድ አውሮፕላን አብራሪዎች የሙያ ፈቃድ ሰጠ፡፡ የአቪየሽን ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አንሙት ለማ ባለስልጣኑ በ2011 በጀት ዓመት ለ481 አብራሪዎች ፈቃድ እንደሰጠ ዛሬ አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ ዓመት አውሮፕላን አብራሪዎችን ጨምሮ ለቴክኒሻኖችና ዲስፓቸሮች 719 አዳዲስ የሙያ ፍቃድ መስጠቱም ተሰምቷል፡፡ በተያያዥነት ለ5 ሺህ 465 ነባር ደንበኞች የሙያ ፍቃድ ዕድሳት እንደተካሄደ የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ዘግበዋል፡፡
ለ3 ሺህ 963 ነባር የበረራ ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መታደሱን የጠቆሙት አቶ አንሙት ለማ፤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ለኢስት አፍሪካ አቪየሽን፣ የበረራ ሠራተኞች፣ ፓይለቶች፣ ቴክኒሻኖች፣ የኤሮክራፍት ስሙሌተር አስተማሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች የብቃት ማረጋገጫ እንደተሰጠ አስታውቀዋል፡፡
ኢዜማ እና ኢሶዴፓ በስያሜ የተነሳ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ስያሜዬ በኢ.ዜ.ማ (በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ) ተወስዶብኛል ሲል ለምርጫ ቦርድ ክስ መስርቷል፡፡ የፓርቲው ሊ/መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ “ኢ.ዜ.ማ የሚባለው ቡድን “ማ” የምትለዋን ፊደል ማህበራዊ ፍትህ ብሎ ይተረጉመዋል፤ ይህ ደግሞ ሶሻል ዴሞክራሲ ከሚለው የፓርቲችን ስያሜ ጋር ተመሳሳይ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
“የኢዜማን ዝርዝር ፕሮግራም አናውቅም” በማለት በጉዳዩ ላይ እርስ በርሱ የሚጣረስ አስተያየት የሰጡትና ድምፃቸው ጠፍቶ የከረሙት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ “ኢ.ዜ.ማ የሚለው ፓርቲ ስያሜ ከእኛ ፓርቲ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ በዚህም ሕብረተሰቡን እያሳሳቱ ነው” በማለት መኖሩ ስለሚያጠራጥረው ፓርቲቸው ምንነት ለማመልከት አስገራሚ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ኢ.ዜ.ማ ከመመስረቱና ሰባቱ ፓርቲዎች ወደ ውህደት ከመምጣታቸው በፊት የነበሩት ሰማያዊና ኢ.ዴ.ፓን የመሰሉት ፓርቲዎች የሊብራል ዓላማ አራማጆች ናቸው ያሉት አንጋፋው የፖለቲካ ሰው “አሁን ሐሳብ አለቀባቸው መሰለኝ ማህበራዊ ፍትህ እያሉ ነው” በማለትም ተሳልቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የህዝብ ግንኙነት ሐላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ “ኢ.ዜ.ማ” የሚለው ስያሜ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ይመሳሰላል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸው እስካሁን ለፓርቲውም ሆነ ለምርጫ ቦርድ የቀረበ ቅሬታ እንደሌለ አስታውቀው እንዲህ ዓይነቱ እሳቤ ካለ በህጋዊ መንገድ ታይቶ ፓርቲያቸው ምላሽ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡
በጆሀንስበርግ 1.200 ኢትዮጵያውያን በጅምላ ታሰሩ
በደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበርግ ከተማ ከፖሊስ ጋር በተደረገ ግጭት 1200 ኢትዮጵያውን መታሰራቸው ተሰማ፡፡ ዕስሩ በጅምላ አፈሳ እንደተከናወነም ታውቋል፡፡
ትናንት ነሃሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች ከተለያየ መስመር በመሆን ቦታውን እንደዘጉትና ህገወጥና ሐሰተኛ ምርቶችን እንቆጣጠራለን በማለት ኢትዮጵያውያኑ ላይ የጅምላ ዕስር ፈፅመዋል፡፡
በጂፒ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተከስተ ሹምዬ ጉዳዩን አስመልክተው ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ከፖሊሶች ጋር በነበረ ግጭት አፈሳ ሊኖር ይችላል በሚል የንግድ ቦታቸውን ዘግተው እንደነበር ጠቁመው፤ በአካባቢው የተገኙ ፖሊሶች ያለምንም ማጣራት መታፈሳቸውንና ወደ ዕስር ቤት መወርወራቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ከሳምንታት በፊት ከፖሊሶች ጋር በነበረ ግጭት ያልተሳተፉ፣ ድንጋይ ያልወረወሩ እንዲሁም ሕጋዊ ወረቀት ያላቸው ተጣርቶ ይለቀቃሉ ቢባልም እስካሁን ድረስ ግን ተግባራዊ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ፖሊሶቹ ከሄዱ በኋላ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ማምሻውን ለዘረፋ ወጥተው የነበረ ቢሆንም መጠነኛ ግጭት ከመፈጠሩ ውጪ ጉዳዩ ሳይባባስና የከፋ ችግር ሳይደርስ በሰላም እንደተፈታም ከዜናው መረዳት ችለናል፡፡
የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ መገጠም ተጀመረ
የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ ለመግጠም የወጣው መመሪያ ተግባራዊ መደረግ ተጀመረ፡፡ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በሰጠው መግለጫ በሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረገውን የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ ስለመግጠም እና ስለማስተዳደር የወጣውን መመሪያ (አዋጅ) ተግባራዊ ማድረግ ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡
በመመሪያ ቁጥር 27/2011 መሰረት ሥራው ተጀምሯል ያሉት የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ መመሪያው የወጣው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የትራፊክ አደጋ ዋና መንስኤ አሽከርካሪዎች ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከራቸው መሆኑ ስለተረጋጋጠ ነውም ብለዋል፡፡
የፍጥነት መቆጣጠሪያው መሳሪያው ከትናንት ነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ ተሽከርካሪዎች ላይ መገጠም ተጀምሯል፡፡ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በቅድሚያ ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከካሪዎች ላይ መግጠም የሚጀምር ሲሆን፣ በሂደት ሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ የገጠማ ስራው ይከናወናል፡፡