ካለፉት 40 ዓመታት ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ የፖለቲካ ትግልና የሥነ መንግሥት ቅርፅ የሆነው ሕወሓት እንዴት የትግራይ ሕዝብ ነባራዊ ሀቅ ከሆነው ታሪክ፣ ባህል፣ ሥነ ልቦናና እምነት ያፈነገጠ እንደሆነ ብዙዎች ይኮንናሉ፡፡ እኔም ይኼንን ግምገማ እጋራለሁ፡፡ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ለሥልጣንና ለሥነ መንግሥት ያለው አመለካከት አዎንታዊ ሆኖ ሳለ፣ ሕወሓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ማዕከላዊ መንግሥት ፊትአውራሪ ሆኖ በቆየባቸው ሦስት አሥርት ዓመታት ገደማ፣ ለኢትዮጵያዊያን ባዕድ የሆነ የሥነ መንግሥት ፍልስፍናና የአስተዳደር ዘይቤ እንዲከተል የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው? ይህ መጣጥፍ ለእነዚህና ተዛማጅ ጥያቄዎች መልስ ያፈላልጋል።
የትግራይ (የኢትዮጵያ ሕዝብ) ታሪካዊና ሥነ ልቦናዊ መሠረቶች
በመሠረቱ የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ግንባታ ትልቅ ድርሻ የያዘ ነው፡፡ በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያ የአምስት ሺሕ ዓመት ታሪክ ጉልህ ሥፍራ አለው። በርካታ ጸሐፍትና የታሪክ ሊቃውንት እንደጻፉት፣ የኢትዮጵያ የጥንት ሥልጣኔ የመንፈሳዊ ሥልጣኔ ነው፡፡ የቁሳዊ ሥልጣኔ አልነበረም። የመንፈሳዊ ሥልጣኔው አሻራ የሆኑት ደግሞ ፈሪኃ እግዚአብሔር፣ የፈጣሪ መንገድ የሆኑትን ሃይማኖቶች አለመዳፈር፣ ለሕግ መገዛት፣ ሥርዓተ መንግሥትን ማክበር፣ ውለታ አለመርሳት፣ ለይቅርታና ለዕርቅ ዋጋ መስጠት፣ ይቅር ባይንና አስታራቂን ማክበር ከብዙ በጥቂቱ ናቸው። የተጠቀሱት መልካም እሴቶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ (ለትግራይ ሕዝብ) የታሪኩ፣ የባህሉ፣ ትውፊቱ፣ እምነቱ መሠረት የሆኑ በአጠቃላይ የኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና ወይም ተክለ ሰብዕና መገለጫዎች ናቸው።
የቀደሙት የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥታት
በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ሥርዓተ መንግሥታትና መሪዎች፣ ከፍ ሲል ከእነዚህ አትዮጵያዊ መገለጫዎች ተነጥሎ የማይታይ የአስተዳደር ዘይቤ ይከተሉ የነበሩ፣ ዝቅ ሲል እነዚህን መልካም እሴቶች በድፍረት የሚጨፈልቁ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም ለሕዝባዊ አንድነት መሠረት የሆኑትን የበጎ ሥነ ምግባር እሴቶች ለሆኑት መከባበር፣ መተማመንና መተሳሰብ ዋጋ የሚሰጡ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለክብርና ኩራቱ የሚጋደል መሆኑን ጠንቅቀው የተረዱ፣ ኢትዮጵያዊ ለሕገ ህሊናው የሚገዛ፣ ሰው ወዳድ፣ ካልነኩት የማይነካ፣ ከራሱ በላይ ለእንግዳው ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ፍርድ ሲጓደል ለምን የሚል፣ ለማህተቡ (ለእምነቱ) ሟች መሆኑን በመልካም ወስደው፣ እነዚህን ሕዝባዊ እሴቶች ሊተናኮሉ (ሊሸረሽሩ) ይቅርና የፖለቲካ ፍጆታ ወይም የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ለማድረግ ድፍረት አላሳዩም።
ሥልጣን የሕዝብ ማገልገያ እንጂ የጭቆና መሣሪያ አይደለም የሚለውን መርህ በግላጭ ለመዳፈር አልሞከሩም፡፡ የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን የአገራዊ አንድነት ማረጋገጫ ማህተም እንጂ በጥበብ የመከፋፈያ መሣሪያ አድርገው አልተጠቀሙም፡፡ በፖሊሲዎቻቸው የመንግሥት ሥልጣን የተመሪው ሕዝብ በጎ እሴቶቹን እንዲጠብቅ መሠረታዊ ተቋማት የሆኑትን ማለትም ሃይማኖት፣ ቤተሰብና የትምህርት ተቋማትን ቢያንስ ለማዳከም ሴራ አልሸረቡም።
ታዲያ ሕወሓት ከነባራዊው ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ለምን አፈነገጠ?
ዛሬ ሕወሓት መራሹን መንግሥት ስገመግም ከቀደሙት የኢትዮጵያ የተለየ ሆኖ አገኘሁት። ለአንባቢያን ሕወሓት ከትግራይ (ኢትዮጵያ) ሕዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ ሥነ ልቦና በብዙ መልኩ የሚፃረር የፖለቲካ መስመር ይከተላል ለሚለው አስረጅ ማቅረብ ለቀባሪ እንደ ማርዳት ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሕወሓት ለምን እንዲህ አፈንጋጭ የአስተዳደር ዘዬ ይከተላል ብሎ ማጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። በእኔ ግንዛቤ ለዚህ መልሱ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ነው።
የሕወሓት የፖለቲካ መሥመር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው። በሕወሓት ቤት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከ‹አይዲዮሎጂም› በላይ ነው፡፡ ሃይማኖት ነው። አብዮታዊ ዴሞክራሲ በእሳቤው የትኛውንም አገራዊም ሆነ ሕዝባዊ ጉዳይ የመሸጋገሪያ እንጂ ግብ አይደለም። በመሆኑም የሥነ መንግሥት እሳቤው መርህ መሠረት (ወይም) መገለጫ የሆኑት ሕገ መንግሥት፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ቢሮክራሲ፣ ዴሞክራሲ፣ ፖሊሲ ወዘተ የታክቲክ ጉዳዮች ናቸው። በመሆኑም በሕወሓት የአስተዳደር ዘመን በኢትዮጵያ ግልጽ የሆነ፣ ርዕይ ያለው፣ ስትራቴጂካዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ተዓማኒ (Legitmate)፣ የሚገመት (Predictable) የሕዝብ አስተዳደር መስመርና ተቋማት እንዳይኖር አድርጓል።
ሕወሓት ለምን በሕዝብ ይጠላል?
ሕወሓት በብዙ ኢትዮጵያዊያን እንዲጠላ የሆነበት ምክንያት የሚከተለው ሶሻሊስታዊ መስመር ከሰውኛ እሴቶች (Human Values)፣ በተለይም ከኢትዮጵያዊ እሴቶች (Ethiopian Values) በብዙ መልኩ የማይገጥም መሆኑ ነው። ይህን በዝርዝር በአዲስ መስመር ስንመለከተው፣ የሕወሓት የፖለቲካ ኢኮኖሚው መሠረት የኢትዮጵያን ታሪክ በማይመለከተው የማርሲስት ሌኒኒስት የበዝባዥ ተበዝባዥ አስተምህሮ መቃኘቱ ነው።
ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሥነ ልቦና በተፃራሪ ሁሉንም የሕዝብ መስተጋብር በዲያሌክቲካዊ ቁስ አካላዊነት ለመግለጽ መሞከሩና የማኅበረ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎቹ መነሻና መድረሻ ማድረጉ ነው። ሕወሓት የሚከተለው ሶሻሊስታዊ የአስተዳደር ዘይቤ መጠራጠርንና መከፋፈልን መሠረቱ ያደረገ፣ ሕዝብን ወይም የማኅበረሰብ ክፍሎችን በጠላትና ወዳጅ (Friend-Foe Dictum) የሚከፋፍል በመሆኑ ነው። የሕወሓት አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሶሻሊስት አስተምህሮ የተቃኘ፣ ከግለሰብ ይልቅ ቡድንን የሚያስቀድም መሆኑ ከዜግነት እሴቶች ይልቅ ቡድናዊነትን ስለሚሰብክ ነው።
አብዮታዊ ዴሞክራሲ ታሪክን የሚረዳበት መነጽር ቁስ አካላዊነትን መሠረት ያደረገ (Historical Materialism)፣ የታሪክ ሁነቶችን የሚተነትንበት አግባብ ደግሞ ሕዝብን በጠላትና በወዳጅ የሚለያይ (Class Conception of History) መሆኑ ነው።
ሕወሓት የሚከተለው ሶሻሊስታዊ መስመር በዘመናት ሒደት የሕዝብን የማኅበረ ፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ ሥነ ልቦናና ተክለ ሰብዕና የማዕዘን ድንጋይ ለሆኑት እንደ ባህል፣ ታሪክ፣ ትውፊት፣ እምነት፣ ሥነ ትምህርት፣ ሥነ ምግባርና የመሳሰሉት ዕውቅና ከመስጠት ይልቅ፣ አፈራርሶ ሶሻሊስታዊ (ቁሳዊ) ማንነትን በሕዝብ ላይ ለመጫን (Mass Inclulcation of Socialist Ideals) መሞከሩ ነው፡፡
በዚህም ሁሉንም ነገር ፖለቲካ የማድረግ ዝንባሌው ለዘመናት የፖለቲካ አይነኬ የሆኑትን ሕዝባዊ (የመንፈሳዊ ወይም የሃይማኖት) ተቋማት ላይ ሳይቀር ጣልቃ በመግባት፣ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ለማድረግ መሞከሩ ነው።
በመጨረሻም
ፈጣሪ የሕወሓት ሰዎች ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አጥፊ መንገድ ይመለሱ ዘንድ ልቦና ይሰጣቸው ዘንድ እፀልያለሁ፡፡ ለትግራይ ሕዝብ ደግሞ (የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን አፍ ልዋስና) ‹‹ከንቐደምና-እንደድሯችሁ›› የሚል መልዕክት ለመስደድ እወዳለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ፣ አሜን!
ከአዘጋጁ ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው
ruhe215@gmail.com ወይም hab200517@yahoo.com ማግኘት ይቻላል።
|| ከሪፖርተር የተወሰደ ||