ፓርቲዎቹ ለምን ረቂቅ አዋጁን ተቃወሙት? || በፈቃዱ ዘ. ኃይሉ

ፓርቲዎቹ ለምን ረቂቅ አዋጁን ተቃወሙት? || በፈቃዱ ዘ. ኃይሉ

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የተጀመረው የሕግጋት ማሻሻያ ሒደት አንዱ አካል የሆነው የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ረቂቅ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ ለውይይት ቀርቧል። ይሁንና 27 የተቃዋሚ ፓርቲ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ ረቂቁን የመረረ ተቃውሞ አስደምጠውበታል። ለመሆኑ “የተቃዋሚዎቹ” ተቃውሞ ምንጩ ምንድን ነው?

ከዚህ በፊት በዚህ አምድ ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች “የተፎካካሪነት መሥፈርቱ ምንድን ነው?” በሚል በጠየቅኩበት ጽሑፌ፥ ብዙዎች “ተቃዋሚ” ፓርቲዎች የሚባሉት በጨቋኝ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ያለ ለማስመሰል የተፈጠሩ እና ሕጋዊ መሥፈርቶችን ሳያሟሉ እንዲንቀሳቀሱ የተፈቀደላቸው “ፓርቲዎች” መሆናቸውን ጠቅሼ፥ በፍትሐዊ ሜዳ እንዲጫወቱ ቢፈቀድላቸውም ብዙዎቹ ሕዝባዊ መሠረት ስለሌላቸው እንደሚሸነፉ ገልጬ ነበር። በመጋቢት ወር 2011 “የ107 ፓርቲዎች ወግ” በሚል ርዕስ ባስከተልኩት መጣጥፍም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥናት ላይ ተመሥርቼ በሕጋዊ መሥፈርቶቹ እና ዓመታዊ ኦዲቶች አግባብ ሲታዩ “ንቁ” ሊባሉ የሚችሉት ፓርቲዎች ሰባት አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች እና 9 ክልላዊ ፓርቲዎች ብቻ እንደሆኑ ጠቅሼ ነበር። (ጊዜው በርካታ ፓርቲዎች ሕልውናቸውን የሚያውጁበት ጊዜ እንደመሆኑ ቁጥሩ አሁን ተቀይሮ ሊሆን ይችላል፤ ጠቅላላ እውነታው ግን አልተቀየረም።)

ቀሪዎቹ ፓርቲዎች ለምን “ንቁ” ለመባል የሚያስችል አቅም ጎደላቸው? አሁንስ ፓርቲዎቹ የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቁን ለምን ይቃወሙታል? ተቃውሟቸውንስ ዜጎች እንዴት ገመገሙት?

ዴሞክራሲ የሚያከስማቸው ፓርቲዎች

ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የይስሙላ ከመሆናቸውም ባሻገር ሕዝባዊ መሠረት እና በሕግ አግባብ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሊያሟላ የሚገባውን የሚያሟሉ ድርጅቶች አይደሉም። ቋሚ ጽሕፈት ቤት ከሌላቸው ጀምሮ፣ ሥራ አስፈፃሚ የሌላቸው ወይም የሥራ አስፈፃሚ አባላቶቻቸው የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ፣ አልፎ ተርፎም ምርጫ ሲመጣ በቲቪ ከመቅረብ እና ሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ከመታደም የበለጠ ተሳትፎ የሌላቸው ናቸው። ተቀናቃኞቻቸው “ሱቅ በደረቴ” ይሏቸዋል። እነዚህን የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለፈው ስርዓት እውነተኛ ተፎካካሪ ስለማይሆኑበት በቸልታ ሲያልፋቸው ከርሟል። አሁን ግን የአዋጁ መሻሻል እና ምናልባት ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ፉክክር ፊት ለፊታቸው አደጋ ሆኖ ተደቅኗል።

ምርጫ ቦርድ በአንድ በኩል ሁሉንም የፖለቲካ ስብስቦች ላለማስከፋት በማሰብ፣ በሌላ በኩል የቦርድ አባላቴ አልተሟሉልኝም እንዲሁም ሕግጋቱ ፍትሐዊ አልነበሩም እና እየተከለሱ ነው በሚል ሥም እነዘህ የይስሙላ ፓርቲዎች ሕጋዊ መስፈርቶችን የማያሟሉ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊ መሠረት የሌላቸው የግለሰብ ክብር ወይም ጥቅም ለመጠበቅ የተቋቋሙ መሆናቸውን ችላ በማለት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚል ማዕረግ በመስጠት በሕግ ማሻሻል እና ሌሎችም ሒደቶች ሲያሳትፋቸው ከርሟል። ይሁንና ይህ ተስፋ በለውጥ ጊዜም ሳንለወጥ መቀጠል እንችላለን የሚል የልብ ልብ የሰጣቸውን የይስሙላ ፓርቲዎች የአዋጅ ክለሳው አስቆጥቷቸዋል። በትብብር እንዲቆሙም ረድቷቸዋል።

ፓርቲዎቹ ከተቃወሟቸው አንቀፆች ውስጥ አንዱ የተቃውሟቸውን መንሥኤ በቅጡ ለመረዳት ይበጃል። ይኸውም በረቂቁ አንቀጽ 64/1/ሀ አገር አቀፍ ፓርቲዎች ለመመሥረት 10 ሺሕ መሥራች አባላቶች እንደሚያስፈልጉ መጥቀሱ ነው። ይህ ቁጥር በኢትዮጵያ ካሉት ቀበሌዎች ቁጥር ያነሰ ነው፤ የቀበሌዎቹ ቁጥር ከ15 ሺሕ በላይ ነው። ይሁንና 27ቱ ፓርቲዎች ይህንን አንቀጽ ሲቃወሙ የመዳራጀትን ነጻነት ይገድባል በሚል ነው። የፓርቲዎቹ ቅሬታ እዚህ አንቀፅ ላይ ብቻ ባይሆንም ይህ ክርክር በአንድ በኩል ፓርቲዎቹ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ለመወከል ድርጅት ሲመሠርቱ 10 ሺሕ መሥራች አባል ማሰባሰብ እንደሚቸግራቸው ሲያሳብቁ፣ በሌላ በኩል የመደራጀት መብት መኖሩን ተገን አድርጎ ብቻ ፓርቲዎችን መፈልፈል ተፈፃሚ ላልሆነ የዴሞክራሲያው ስርዓት ሊዳርግ እንደሚችል አመላካች ነው።

በ2007ቱ አወዛጋቢ አገር ዐቀፍ ምርጫ ሒደት ወቅት፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ ከ12 በላይ ዕጩዎች በመቅረባቸው ምክንያት ምርጫ ቦርድ ችግሩን ለመፍታት የተከተለበት ሒደት ራሱን የቻለ ሌላ ውዝግብ የፈጠረ ነበር። መጀመሪያ የግል ዕጩዎችን ያለቅድመ ሁኔታ ከውድድር አገደ። በማስከተል ቀሪዎቹን ፓርቲዎች (ከኢሕአዴግ በስተቀር) በዕጣ በመለየት ለውድድር የሚበቁትን ዕጩዎች አሳወቀ። ይህ አሠራር አወዛጋቢ ቢሆንም ቅሉ ቦርዱ በአንድ የምርጫ ወረዳ ከ12 በላይ ዕጩዎችን የማሳተፍ አቅም የለኝም ማለቱ ለፖለቲካ ግብዓት ተብሎ የተደረገ ሳይሆን ከአፈፃፀም (ሎጅስቲክ) አንፃር የማይቻልም ስለሆነ መሆኑ አያጠያይቅም። ለዚህ መንሥኤው ፓርቲዎች ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሥፈርት አለመኖሩ ወይም አለመከበሩ ነው።

የመደራጀት መብትን ለማፈን የሚደረጉ ፖለቲካዊ ጫናዎች እና ቅድመ ሁኔታዎች ሁልጊዜም ቢሆን ተቀባይነት አይኖራቸውም። ከተፈፃሚነት አንፃር የማይጨበጥ ሕልም ይዞ ፓርቲዎች በየጉሮኖው ውስጥ እንዲፈለፈሉ ማድረግም መድብለ ፓርቲ ለመገንባት ይህ ነው የሚባል ፋይዳ አይኖረውም። የረቂቅ አዋጁን ይህን መሰል አንቀፆች የተቃወሙት 27 የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ይህንን መሠሉን መሥፈርት ከመቃወም ይልቅ ኅብረት በመመሥረት አንድና ትልቅ የፖለቲካ ድርጅት መፍጠር ቢችሉ፣ መሥፈርቱን በቀላሉ ከማሟላታቸውም ባሻገር የተፎካካሪነት አቅም ማዳበር በተቻላቸው ነበር።

ሕዝባዊ ምላሹ

የረቂቅ አዋጁን በመቃወም ረገድ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹና ሥመ ትልልቆቹ ፓርቲዎች ሲቃወሙት አልተደመጠም። ከዚያም በላይ ብዙ አስተያየት ሰጪዎች ረቂቁን የተቃወሙ ፓርቲዎችን በቀልድ ሲሳለቁባቸው ነው የተስተዋለው። ጥያቄያቸው ፓርቲዎቹ እንዳሉት የመደራጀት መብት ጥያቄ ተደርጎ አልተወሰደም። ይልቁንም ያለ ምንም ሕዝባዊ መሠረት ያገኙትን ማዕረግ ሊነጠቁ፣ አልያም ሠርተው ምንነታቸውን እንዲያስጠብቁ ሲጠየቁ የፈጠሩት የመቀነቴ አደናቀፈኝ ዓይነት ተቃውሞ እንደሆነ ነው የተወሰደባቸው።

ጋዜጠኞች ግን የፖለቲካ ድርጅቶቹን ቅሬታ ለማስተጋባት እና ከምርጫ ቦርድ ኀላፊዎች መልስ በመጠየቅ ጉዳዩን የውይይት አጀንዳ ለማድረግ ሞክረዋል፤ የሙከራቸውን ያክል አልተሳካላቸውም እንጂ። ሕዝባዊ ምላሹ የሚያረጋግጠው አንድ ነገር ቢኖር እነዚህ ፓርቲዎች ወደ ራሳቸው ተመልክተው እውነቱን ለመጋፈጥ እና አንድም ከስሞ ለሐቀኛ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች መስኩን መልቀቅ፣ አልያም ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን የሚመጥኑ መሥፈርቶችን በማሟላት በሙሉ ቁመና መደራጀት እንዳለባቸው ነው።

LEAVE A REPLY