ባለፈው ሳምንት ውስጥ ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዬጵያኖችን ጨምሮ “ህገወጦች ናችሁ፣ህገወጥ ንግድ እያካሄዳችሁ ነው” በሚል ሽፋን ዝርፊያ ያካሄዱባቸው የ ደ/አፍሪካ ፖሊሶች መዲናይቱ ጆሀንስበርግ ውስጥ ከፍርድ ቤት ቀረቡ።
በትላንትናው ሰኞ እለት ከጆሀንስበርጉ የመጀመሪያ ደረጃ የወንጀለኛ ችሎት የቀረቡት ወደ አስር የሚጠጉ የፖሊስ አባላት ከኢትዬጵያኖች እና መሰል አፍሪካዊያን ስደተኞች መደብሮች “በህገወጥ ዕቃ” ሽፋን የወረሷቸውን ሸቀጦችን በመስረቅ እና ለገበያ በመሸጥ፣ከአንዳንድ ስደተኞች ጉቦ በመቀበል ፣የፍትህ ሂደትን በማዛባት እና ምስል ክሶች እንደቀረቡባቸው ታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ የፖሊስ አባላት ከችሎት በቀረቡበት ወቅትም ሂደቱ በመገናኛ ብዙሀናት በምስል እና በድምጽ እንዲቀረጽ መመሪያ የተሰጠ ሲሆን አንድ ተጠርጣሪ ፖሊስ ግን “መልካም ዝናዬን ስለሚያጎድፍ መቀረጽ የለብኝም “በማለት ቢቃወምም ዳኛው ሉቃስ ቫንዴር” ሁልጊዜ የህዝብ ጥቅም ከግለሰብ ጥቅም (የማንነቱ ምስጢርን መጠበቅ)ስለሚቀድም የህዝብን ጥቅም እናስቀድማለን” በማለት የፖሊሱን ጥያቄ ውድቅ አድርገውበታል።
ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ብዛት ካላቸው ኢትዬጵያኖች ጋር በቁጥጥር ስር የሚገኙት ወደ አስር የሚደርሱት የደ/አፍሪካ ፖሊሶቹ በችሎት ውሏቸው የመጸጸት ስሜት እንዳልተሰማቸው ከአንዱ በቀር ሁሉም ፊታቸውን ሳይሸሽጉ በተረጋጋ መንፈስ የክስ ሂደታቸውን መከተተላቸውን የአፍሪካ ኒውስ ዜና አገልግሎት ዘገባ ገልጿል።ተጠርጣሪዎቹ ፖሊሶች የዋስትና መብታቸው ለጊዜው ተነፍጎ ገሚሶቹ ለቀጣዩ የችሎት ሂደት ዛሬ ማክሰኞ የተቀሩት በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ እለት እንዲቀርቡ እና የዋስትና መብታቸው በተመለከተ እንደ ሚወስን ችሎቱ ትእዛዝ አስተላልፏል ።
ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ያልተገለጸ ታሳሪ ስደተኞች በትላንትናው እለት ከጆሀንስበርጉ ችሎት የቀረቡ ሲሆን በደ/አፍሪካ የኢትዬጵያ ኮሚኒቲ ሀላፊዎች እና አንድ መቶ የሚጠጉ አባላት ከፍርድ ቤት ደጃፍ ተገኝተው በአሁኑ ወቅት በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙት ጓደኞቻቸውን መጎብኘት እንዳልቻሉ፣በቂ ምግብ እንደማያገኙ እና በፖሊሶችም ወከባ እየደረሰባቸው መሆኑን ጓደኞቻቸው ከችሎቱ ደጃፍ ባነገቡት የተቃውሞ ጽሑፎች አማካኝነት ለዜና ሰዎች ገልጸዋል። የኮሚኒቲው ሀላፊ የሆኑት አቶ ታደሰ የማነ በበኩላቸው “እነዚህ ተጠርጣሪ ፖሊሶች እኛንም ሆነ ጓደኞቻችንን ህገወጦች እንደ ሆንን እና ህገወጥ ሸቀጦችን እንደምንሸጥ በማስመሰል ከግድያ ያልተናነሰ ግፍ ፈጽመውብናል፣ዛሬ ከችሎት አደባባይ የመጣነውም ድምጻችንን እና ቅሬታችንን ለማሰማት ነው ” ብለዋል። አንዳንድ ስደተኞች ህገወጥ ስደተኛነኝ ብላችሁ ከፈረማችሁ ትለቀቃላችሁ የሚል የፖሊስ ጫና እንደደረሰባቸው የመብት ተሟጋቾች እኩይ ድርጊቱን ሰሞኑን አጋልጠዋል።
እንደ የአፍሪካ የዜና አገልግሎት ዘገባ ከሆነ ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ታሳሪ ስደተኞች ሊንዳላ ከተባለ ጊዜያዊ ማቆያ ማእከል ለአንድ ወር እንዲሰባሰቡ ተደርገው ጉዳያቸው ሲጣራ ወደ መጡበት አገራቸው እንዲላኩ ፍ/ቤቱ መመሪያ አስተላልፏል።