ኢትዮ ኤፍ.ኤም || በአዲስ አበባ ለባለዕድለኞች ያልተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በቡድን በተደራጁ ወጣቶች ቁልፋቸው እየተሰበሩ መሆኑ ተገለጸ!
የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለባለ ዕድለኞችና ለልማት ተነሺዎች ቤት ሲያስተላልፍ ከ10 ዓመት በላይ ሆኖታል። ግንባታቸው የተጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በየጊዜው በዕጣ ማስተላለፉም ይታወሳል። ቂሊንጦ፣የካአባዶ፣ቦሌ ቡልቡላና ሌሎች ስፍራዎች ደግሞ በቅርብ የተገነቡ ቤቶች የሚገኙባቸው የግንባታ ሳይቶች ናቸው።
ይሁንና በነዚህ አካባቢዎች ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች በህጋዊ መንገድ የተላለፉ ቢኖሩም ለነዋሪዎች ተላልፈው ያልተሰጡ ቤቶች መኖራቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም በሳይቶቹ ባደረገው ቅኝት አረጋግጧል። እነዚህን ቤቶች ወጣቶች በቡድን በቡድን በመሆን ቁልፍ እየሰበሩ እየገቡባቸው እንደሆነ ኢትዮ ኤፍ ኤም ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምቷል።
እነዚህ በቡድን የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ለደህንነታቸው እንዳሳሰቧቸውና መንግስት ህግ እንዲያስከብርላቸው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል። በአቃቂ ቃሊት ክፍለ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከተገነባባቸው ወረዳዎች መካከል አንዱ ወረዳ 9 ሲሆን ቂሊንጦ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይት ደግሞ ዋነኛው ነው።
የወረዳው ዋና ስራ አስፋፃሚ አቶ በላይ ደምሴ እንዳሉት በቂሊንጦ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይት ዕጣ የወጣላቸው ባለድለኞች ያልገቡበት ቤት እና የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደርም በእጣ ያላስተላለፍቸው ቤቶች አሉ ብለዋል።
በወረዳው የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸው ዜጎች ብዙ ናቸው የከተማ ቤቶች አስተዳድሩ ለእኛ ቢሰጠን ልናስተላልፈው እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።
አስተዳድሩ ይሄንን ማድረግ ካልቻለ ለባለዕድለኞች ያልተላለፉ ቤቶችን ያስተላልፍ አልያም ሌላ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም በጉዳዩ ዙሪያ የከተማ አስተዳድሩን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ኢንጂነር ሰናይት ዳምጤን ጨምሮ ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ እና የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ስለ ጉዳዩ መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ተገቢ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።