ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ያለእድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የተዘጋጀ ብሄራዊ ፍኖተ ካርታ ይፋ ተደረገ::
በስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ የአለም ፀጋይ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ተወካይ አዴሌ ኮድር ተገኝተዋል።
ፍኖተ ካርታውን ይፋ ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፍኖተ ካርታውን ተግባራዊ ለማድረግ ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ የአለም ፀጋይ ፍኖተ ካርታው መንግስት የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚያደርገውን ጥረት በማገዙ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል::
የዩኒሴፍ ተወካይ አዴሌ ኮድር በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት የሴት ልጅ ግርዛትን እና ያለ እድሜ ጋብቻን በፈረንጆቹ 2025 ለማስቆም አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውሰው ይህን ተግባራዊ ለማድረግም ባለ ድርሻ አካላትን በማሳተፍና እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያግዝ መልኩ የመደበውን በጀት በእጥፍ በማሳደግ እየሰራ ይገኛልም ብለዋል::
በኢትዮጵያ ከ10ሩ አራቱ ልጃገረዶች 18ኛ አመት የልደት በዓላቸውን ሳያከብሩ ትዳር ይይዛሉ::
ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ያለ እድሜ ጋብቻ ከሚፈጸምባቸው አምስት ሃገራት አንዷ መሆኗን ያነሱት ተወካይዋ፥ በመላ ሃገሪቱ 15 ሚሊየን ሴቶች ያለ እድሜ ትዳር መያዛቸውን አስታውቀዋል።
ለፍኖተ ካርታው ተግባራዊነትና ስኬታማነትም አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ክትትል፣ በማድረግና በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፍኖተ ካርታው ከፈረንጆቹ 2020 እስከ 2024 ድረስ የሚተገበር ሲሆን፥ ቁልፍ ስትራቴጂዎችን በመተግበርና የባለ ድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማሳደግ ያለ እድሜ ጋብቻን እና የሴት ልጅ ግርዛትን ማስቆም እንደሚያስችል ታምኖበታል።