የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ”አስተራረም” እያወዛገበ ነው || ሙሼ ሰሙ

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ”አስተራረም” እያወዛገበ ነው || ሙሼ ሰሙ

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ”አስተራረም” አሳፋሪ በመሆኑ እያወዛገበ ነው፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው አካልም በቂ መረጃ በወቅቱ መስጠቱ ባለመቻሉ ክስና እንካስላንታው፤ መልስና የመልስ ምቱ የብሔር ፖለቲካውን መስመር ተከትሎ የተለመደውን የጥላቻ መርዙን በሚረጭ መልኩ እየተካሄደ ነው፡፡ የግጭት አደጋውም በዛው ልክ እየተራገበ ነው፡፡

ዝርዝር መረጃው በፍጥነት እና በተለያየ መስፈርት ግልጽ እስከሚሆን ድረስ ከመላ ምት በመቆጠብና ችግሩን ከተቋምና ከግለሰብ ወይም ከቡድን ሚና አውጥቶ ወደ ብሔር ማሸጋገሩ ሊታሰብብት የሚገባው ለዚህ ነው፡፡ በማንኛውም ጉዳይ ብሔር እያንጠለጠሉና የብሔር ሰልፍን እያሳመሩ መጠዛጠዙና የጥላቻ መርዝ መረጫጨቱ ከቀጠለ ከፊታችን የተጋረጠውን አደጋ ከማባበስና በተቀጣጠለው እሳት ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ ውጭ አንዳች ፋይዳ ያለው ጉዳይ እንደማናገኝበት ለመረዳት ያዳግተን አይገባም፡፡

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና መሰረቅና ውጤቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተዛብቶ መጠናቀቅ በሀገራችን የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ከደርግ የስልጣን ማብቂያ ዘመን ጀምሮ ፈተናዎቹ ቀድመው እየተሰረቁ ከነመልሳች ገበያ ላይ ይቸበቸቡ እንደነበር ያተወቃል፡፡ አክቲቪስቶችና የነጻነት ታጋችም ፖለቲካ ማገቻና መታገያ መሳርያ አደርገው ሲጠቀሙበት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በርካቶችም በዚህ መንገድ በተገኘ ሃሰተኛ ውጤት ወደ ዩኒቨርስቲዎች በመግባት ዝግጅት የነበራቸውን ተማሪዎች እድል ያመከኑ ቢሆኑም፣ እነሱም በአቅምና ዝግጅት ማነስ አንድ ሰሚስተር አንኳን ማለፍ እያቃታቸው ከዩኒቨርስቲዎች ለመባረረር በቅተዋል፡፡ የችግሩ መንስኤውም ሆነ መዳረሻውና ውጤቱ ይህው ነው፡፡ ከብሔር ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር የለም፡፡

በእርግጥ የዛሬውን ለየት የሚያደርገው የውጤቱ መዛባት መጠነ ሰፊ መሆኑና ጣት መጠቋቆሙ እንደ ፖለቲካው ብሔር ተኮር ቅርጽ መያዙ ነው፡፡ ለዚህም በቂ መነሻ አለ፡፡ የብሄር ፖለቲካ ሁሌም እራሱን ችሎ፤ በራሱ መቆም ስለማይሆንለት፣ በሌላው ላይ ካልተንጠለጠለ እርካታ አያገኝም፡፡ በሌላው ላይ ካልተንጠላጠለ አቀጣጣይ የሆነ የመታገያ አቅም ትንፋሽ ስለሚያጥረው ብዙ ርቀት መሄድ አይችልም፡፡ የብሔር ፖለቲከኞቹም ከብሔር ማንነታቸው የከረረ የስበት መዘውር የተነሳ ሚዛናዊነት ስለሚጎድላቸው፣ እሮሯቸውን ለማስተጋባትና ብሶታቸውን ከፍ አደርጎ ለመጮህ ብሔረተኝነቱ ስለሚጠቅማቸው ማንኘውንም አጀንዳ ከብሄራቸው ጋር ማያያዝ የትግል ስልታቸው ነው፡፡ ዘንድሮም የመጭው ትውልድ ወሳኝ አጀንዳ ሆነው የትምህርት ስርዓት ይህንኑ መስክ ተቀሏል፡፡

ላላፉት ሶስት ዓመታት በአንጻራዊነት ቢሆንም በሁሉም ክልሎች ሊባል በሚችል ደረጃ ወጣቱ ዋነኛ ተግባሩ የሆነውን መማር እርግፍ አድርጎ ትቶ በጥላቻ በመጠመድ ፋብሪካ፣ ኢንዱስትሪና የእርሻ ልማት ተቋማትን እንዲያቃጥልና እንዲያወድም አልፎ ተርፎም ጎራ ለይቶ እርስ በርሱ እንዲተላለቅ ሲያበረታቱት የነበሩት ሃይሎ ዛሬ ላይ የዘሩትን በከፊልም ቢሆን ማጨድ መጀመራቸውን በዓየናቸው መመልከት ሲጀምሩ ቀኝ ኃላ ዙር ብለው ጭዳ ሲያደርጉት የነበረው ትውልድ ተቆርቋሪ በመምሰል በአዲስ ቅላጼ ብቅ ሲሉ እየተመለከትን ነው፡፡

ቀጣዩ ትውልድ የሚጠቅመው በጥላቻ ፈረስ ተጭኖ ሌላውን መጤ እያለ ማሳደድ ወይም ነገ ተቀጥሮ የሚሰራበትን የልማት ተቋማት ማቃጠልና መዝረፍ አልነበረም፡፡ እርግጥ ነው፤ ቀሳቃሾቻችን ትውልዱን ለማዳን ዛሬ የተከሰተውን አጀንዳ ማንሳታቸው ከስህተታቸው ተምረው ከሆነ ቁም ነገሩ የት እንዳለ መረዳታቸውን በከፊልም ቢሆን ስለሚያመለክት አካሄዱ መልካም በሆነ ነበር፡፡ ( ተምረው ከሆነ መገመት ስለሚያዳገት)፡፡ ነገር ግን ዛሬም የሚያሳዝነው ጉዳይ፤ የችግሩ መንስኤ ቴክኒክዊ አሰረራ ግድፈት ወይም በቡድናዊ አሊም ግለሰባዊ መሆኑ በቅጡ ተተንትኖ ማብራርያ እስኪሰጥ ድረስ እንኳን መታገስ አቅቷቸው ችግሩን ወደ ብሔር አጀንዳ በመለወጥ የተለመደውን የጥላቻ መዝራት ለመርጨት ሲጣደፉ እየተመለከትን ነው፡፡

በዚህ ዓመት በተለይ የተከሰተው ችግር ጥልቀት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከአንድ ወይም ከሌላው ብሔር ጋር ሲነጻጸር ለዩኒቨርስቲ የሚያበቃ ውጤት ያሚያገኙት ተማሪዎች ቁጥር በአንጽራዊነት ከፍ ወይም ዝቅ ማለቱ የፈተና ባህርይ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በቁጥር ጥቂት ግን ከፍተኛ ውጤት በማዝመዝገብ ረገድ እንደ ዛሬ በክልል የሚሰፈር ባይሆንም ወለጋዎችና ጎጃሞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ የተለመደ ነው፡፡ ውጤቱ የሚመዘገበው ከተማሪዎች ጽናት፣ ከመምህራን ትጋት፣ ከትምህርት አሰጣጥ ሂደቱና ከቀደምት ተማሪዎች ዝንባሌ መንጭቶ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ከሁሉም ክልሎች በቁጥር፣ በጥራትም ሆነ በብቃት የተሸሉ ትምህርት ቤቶች አሏት፡፡ ይህም ሆነ ግን በአንጻራዊነት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ለዩኒቨርስቲ በማብቃት ረገድ የተለየ ውጤት የሚመዘገብባት ከተማ አይደለችም፡፡

እርግጥ ነው፡፡ በአንዳአንድ ክልሎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የወረዳ እና የቀበሌ መስተዳድሮች በፈተና አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ጣልቃ እየገቡ ተማዳች እንዲኮራረጁ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በአንድ ወረዳን ቀበሌ ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ባህል ከሆነ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ይህም ሆኖ በመቶ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ላመጡት ውጤት ብሔርን ተጠያቂ ማድረግና መውቀስ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡

የዛሬዎቹም ሆነ የትናንቶቹ ኢህአዴጎች የትምህርት ስርዓታችን በዚህ ደረጃ እንዲፈጠፈጥ የበኩላችሁን ድርሻ መወጣታችሁ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ከዚህ ተጠያቂነት ልታመልጡ አትችሉም፡፡ አዳዲሶቹ ታጋዮችና አክቲቪስጽ ነን ባዮች ግን እስከዛሬ የብሄር ፖለቲካ ሊወስዳችሁ የሚችለውን ርቀት ያህል በመሄድ እርስ በርሱ ልታጫርሱት የነበረው መጨው ትውልድ ተጨራርሶ አላልቅ ሲላችሁ የእውቀትና የትምህርት ጉዳናና ሌላኛው የጥላቻ መርዝ መርጫ በማድረግ ትውልዱን በቀጣይ ለሌላ ዙር ጥላቻና እልቂት ለማመቻቸት ሽር ጉድ ማለታችሁን ልታቆሙ ይገባል፡፡ ”መከበር በከንፈር” እንዲሉ የራሳችሁ ብሔር ክብር፣ ለሌላው ብሔር በምትሰጡት ክብር ላይ የሚመሰረት መሆኑን ለአፍታም ልትስቱት አይገባም፡፡

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤት እንዲዛባ ያደረገ ሃይል፣ ቡድን፣ ተቋም ወይም ግለሰብ ካለ ለሕግ አንዲቀርብና ውጤቱ እንዲመረመር መታገል አግባብ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን በጅምላ አንዱን መይም ሌላውን ብሔር ተወቃሽ በማድረግ የጥላቻ መርዝ መነስነስችሁን ልታቆሙ ይገባል፡፡ አስር በመቶ ለማይሞላ ውጤት ”አንጸባራቂ ውጤት ተቀዳጀን” በሚል ከንቱ ውዳሴ ተጠምዳችሁ የላቀ ውጤት ለማግኝት ከመትጋትና ከመዘጋጀት ይልቅ ጉዳዩን ወደ ብሔር ብሽሽቅ በመግፋት የተመዳችሁ ኃይሎች ብሽሽቃችሁ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ከወዲሁ ተረድታችሁ ከሕዝብ ላይ እጃችሁን ብታነሱ ይበጃል፡፡

በብሔር ተቧድናችሁ የምትረጩት የጥላቻ፣ የቂም በቀል፣ የብሽሽቅ አዙሪት ውሎ አደሮ ከእልቂት በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ አትራፊ ሃይል እንደማይፈጥር ከወዲሁ ልትረዱት ይገባል፡፡

LEAVE A REPLY