የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የእስልምና እምነቶች – አብሮነትና ፈተና || መሐመድ አሊ መሐመድ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የእስልምና እምነቶች – አብሮነትና ፈተና || መሐመድ አሊ መሐመድ

|| የበኩሌን ጠጠር ለመወርወር ያህል ||

በነገራችን ላይ የጊዜ ቅደም-ተከተል ጉዳይ እንጅ ሁለቱም እምነቶች ሀገር በቀል አይደሉም፡፡ ሁለቱም መነሻቸው መካከለኛው ምሥራቅ ሲሆን ቀደምት ኢትዮጵያውያን አባቶች በምርጫቸውና በየፊናቸው እምነቶቹን ተቀብለው አብረው ኖረዋል፡፡ ስለሆነም አንዱ ሀገርኛ ሌላው መጤ የሚባልበት መነሻ የለም፡፡ ይሁን እንጅ በሁለቱ ቤተ-እምነቶች መካከል መገፋፋትና አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ በቀጥታ ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ባይኖሩም ከግዛት ማስፋፋትና የፖለቲካ የበላይነትን ከማረጋገጥ ጋር በተያያዘ የአገዛዝ ሥርዓቶቹ ርዕዮተ-ዓለም ከእምነቶቹ አንፃር የተቃኘ እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ ስለሆነም አሸናፊው ወገን የራሱን እምነትና ኃይማኖታዊ እሴቶች ማጉላቱና፣ በአንፃሩ የተሸናፊው ወገን እምነት ተከታዮች በመገፋትም ሆነ ራሳቸውን በማግለል በተገዥነት መንፈስ መኖራቸው ያገጠጠ እውነት ነው፡፡

ይህ ሁኔታ በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደቱ ላይ የራሱ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖና/አንደምታ አለው፡፡ አዎንታዊ ተፅዕኖው/አንደምታው የሀገረ-መንግሥት ግንባታው የተሳካው በአሸናፊው ወገን ኃይል/ጫና ብቻ ሳይሆን በተሸናፊው ወገን ይሁንታና ሁለንተናዊ ትብብር መሆኑ ነው፡፡ ተሸናፊው ወገን በቀላሉ እጅ ባይሰጥና እምቢተኛ ቢሆን ኖሮ አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያ እውን ማድረግ አስቸጋሪና፣ ምናልባትም የማይቻል ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ሆኖም ግን አንዱ ሌላውን በኃይል/በስምምነት የማስገበሩ ሂደት መልክ ከያዘ በኋላ የውጭ ወራሪ ኃይላትን ለመከላከል ኢትዮጵያውያን የዘር/የቋንቋና/የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው በአንድነት (ቀፎው እንደተነካ ንብ) ሆ! ብለው መነሳታቸውና ጠላቶቻቸውን አሳፍረው መመለስ ለመቻላቸው ከአድዋ ድል በላይ ምስክር ሊሆን የሚችል የለም፡፡

አሉታዊ ተፅዕኖው/አንደምታው፣ በአንድ በኩል አሸናፊው ወገን ራሱን የሀገረ-መንግሥት ግንባታው መሐንዲስና ባለቤት አድርጎ ማሳቡና፣ በሌላ በኩል ተሸናፊው ወገን የተሸናፊነት መንፈስ የተጫነውና በሀገር ጉዳዮች ላይ ባይታወር መሆኑ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ አንዱ ወገን ለሀገር አንድነት፣ ደህንነትና ህልውና እንደሚቆረቆር ተደርጎና፣ በአንፃሩ ሌላው እንደሥጋት መታየቱ የፈጠረው ሰፊ ክፍተት መኖሩም መታወቅ አለበት፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደቱ ውስጥ ሁሉም ወገን በየፊናው የተጫወተውን አዎንታዊ ሚና ማጉላትና የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ቅን ተነሳሽነት ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ረገድ የሁለቱ ታላላቅ ቤተ-እምነቶች፣ (ክርስትና እና እስልምና) የእምነት አባቶችና ሊቃውንት ብዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በእርግጥ ከፖለቲካዊ አውዱ በመለስ፣ በሀገራችን የእምነት አባቶች መካከል ያለው ግንኙነት በመልካምነቱና በአርኣያነቱ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ወደ ተራው ህዝብና የሁለቱ እምነት ተከታዮች ስንገባ ደግሞ በፈርጀ-ብዙ መስተጋብሮች የተሳሰረ አብሮነታችን እጅጉን የሚያስደምም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስሊም – ክርስቲያኑ እንደ ንግድ፣ ዕቁብ፣ ዕድር፣ ሠርግ፣ ቀብር … በመሳሰሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነቶች፣ እንዲሁም ሌሎች ባህላዊ ሥርዓቶች በጥብቅ ከመተሳሰሩም ባለፈ ህዝቡ በተለያዬ መንገድ የተዛመደና በደም የተዋሃደም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም አንዱ በሌላው ሃይማኖታዊ በዓል “እንኳን አደረሰህ” እየተባባለና (የተገኘውን) አብሮ እየተቋደሰ በደስታና በፍቅር የሚያሳልፍበት ማራኪ ሁኔታ መኖሩን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡

መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ እውነት ይኸ ሆኖ ሳለ ተገቢ ያልሆነና አላስፈልጊ ጽንፍ ይዞ “ውረዱ – እንውረድና ይለይልን” የሚል አንደምታ ያለው መልዕክት ማስተላለፍ ከማንም አይጠበቅም፡፡ በተለይ ከእምነት አባቶችና ሊቃውንት የሚጠበቀው ሌሎችን መገሰፅ፣ ይቅርባይነትና ፍቅርን መስበክ እንጅ ሁሉም በየፊናው ተከታዮቹን ለግጭት ማነሳሳት አይደለም፡፡ ለሀገር አንድነት፣ ለዘላቂ ሰላምና ለአብሮነታችንም የሚበጅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘርም ሆነ የሃይማኖት ግጭት ቀስቅሶ/እሳት ለኩሶ ከዳር ሆኖ መመልከት ወይም ቁጭ ብሎ መሞቅ የሚቻልበት ዕድል የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ተወደደም/ተጠላም፣ የዘር/የቋንቋ/የሃይማኖት ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ የወደፊት ዕጣ-ፈንታችን ግን የተሳሰረ መሆኑ መዘብጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ ሆነን ማሰብ፣ በጥሞና መነጋገር፣ መደማመጥና መግባባት መቻል የውዴታ – ግዴታችን መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ከዚህ አንፃር በተለይ በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመነ-መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ባለፉት አገዛዞች ውስጥ በመጨቆኛ መሣሪያነትና በተጠቃሚነት ተፈርጃ የሥርዓቱ ዒላማ መደረጓ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ከዚህ እሳቤ በመነሳትም ከውጭ ከመፈረጅም ባለፈ በቤተ-ክርስቲያኗ የውስጥ አሠራር ጣልቃ በመግባት ተቋማዊ ነፃነቷን እንድታጣ ተደርጓል፡፡ የእምነቱን አባቶችና/መሪዎች በመከፋፈልም የሀገር ውስጡና/የውጩ ሲኖዶስ እየተባባሉ እርስ በርስ በመካሰስና በመወቃቀስ የእምነቱ ተከታዮች አንገታቸውን የሚደፉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡ የዶ/ር አብይ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ በእምነቱ አባቶችና/መሪዎች መካከል የነበሩት ልዩነቶች ተፈትተው የቤተ-ክርስቲያኗ ተቋማዊ አንድነት ቢረጋገጥም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚፈጠሩ/የሚከሰቱ ግጭቶችን አስታክኮ ቤተ-ክርስቲያኗ የጥቃት ዒላማ መደረጓ ሁላችንንም የሚያነጋግር ነው፤ መሆንም አለበት፡፡

በመሆኑም የእስልምና እምነት ተከታይ የሆንን ወገኖች በተለያዩ አጋጣሚዎችና/አካባቢዎች የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን በማቃጠልና የእምነቱን አባቶች በመግደል የሚፈፀሙ አስነዋሪ ድርጊቶችን አምርረን ስንቃወምና ስናወግዝ ቆይተናል፡፡ ከእኛም ባለፈ እንደ ክቡር ዶ/ር፣ ተቀዳሚ ሙፍቲ፣ ሐጅ፣ ሸህ ዑመር እንድሪስን የመሳሰሉ የእስልምና እምነት አባቶች/መሪዎችና ሊቃውንት ከሌላው እምነት ተከታይ ጋር ስላለን ወንድማማችነት፣ ሊኖረን ስለሚገባው አብሮነትና መቻቻል በአደባባይና አበክረው ሲሰብኩ ሰምተናል፡፡ ከዚያ በመለስ ሙስሊም – ክርስቲያኑ በዝምድና፣ በጉርብትና፣ በሥራና በሌሎች መንገዶች ያሉንን መልካም ግንኙነቶችና አዎንታዊ መስተጋብሮች መነሻ በማድረግ አንዳችን ለሌላችን ምን ማለት እንደሆንን ከእኛው ከራሳችን የተሻለ ምስክር ሊሆን የሚችል አይኖርም፡፡ በዚህ ሁኔታ ሰሞኑን የተወሰኑ የኦርቶዶክስ እምነት አባቶችና/ሊቃውንት በቤተ,ክርስቲያኗ ላይ ለሚፈፀሙ ጥቃቶች የእስልምና እምነት ተከታዮችን በጅምላና/በጠቅላላ፣ በተለይም የእምነቱን መሪዎች ተጠያቂ በማድረግ ያስተላለፉት (ማስፈራሪያ አዘል) መልዕክት ግርታን የሚፈጥርና አነጋጋሪ ነው፡፡

አንደኛ ነገር ሙስሊሙ ማህበረሰብ (በእምነት ደረጃ) የኦርቶዶክስ እምነትነትን ለማዳከም በመንግስት ደረጃ በተወሰዱ እርምጃዎች፣ እንዲሁም በአብያተ-ክርስቲያናቱና በእምነቱ አባቶች ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ተባባሪ መሆን የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እንዳውም በሙስሊሙ ላይ ሲፈፀሙ/ሲደርሱ የነበሩት ግፎችና መከራዎች እጅግ የከፉ ከመሆናቸውም በላይ ሙስሊሙ ራሱን መከላከል የሚችልባቸው ዕድሎችም አልነበሩም፡፡ ይህም ሆኖ በኦርቶዶክስ ቤተ-እምነቶችና የሃይማኖት አባቶች ላይ ጥቃቶች በተሰነዘሩባቸው አጋጣሚዎች የእስልምና እምነት ተከታዮች ጥቃቶቹን ከመከላከል አንስቶ ከተፈፀሙም በኋላ በግልፅ እስከማውገዝ ድረስ የሄዱበት ርቀትም መዘንጋት የለበትም፡፡ በአንፃሩ በአማራ ክልል በእስቴ፣ በብቸና … እንዲሁም በአዲስ አበባና በሌሎችም አካባቢዎች መስጊዶች ሲፈርሱና/ሲቃጠሉ የክርስትና እምነት ተከታዮችና አባቶች ምን ያህል ድምጻቸውን አሰምተዋል? የሚል ጥያቄ ማንሳትም ተገቢ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ እንደሶማሌ ክልል ካሉ ሙስሊሞች ከሚበዙባቸው አካባቢዎች ውጭ በሲዳማና በመሳሰሉት ሌሎች ቦታዎች በአብያተ-ክርስቲያናቱና የእምነቱ አባቶች ላይ ለተሰነዘሩ ጥቃቶች ሁሉ ተጠያቂው ሙስሊሙ ብቻ ነው ወይ? የሚለውም ጉዳይ አነጋጋሪ ነው፡፡ ለመሆኑ ሙስሊሙ እስከመቼ ነው በጥርጣሬና በሥጋት የሚታየው?

አንዱ በሌላው ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብ አለበት ስንልኮ የሌላው እምነት ተከታይም በሙስሊሙ ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብ አለበት ማለታችን ነው፡፡ ሙስሊሙ እንደመጤ ተቆጥሮና በሀገር ጉዳይ ባይታወር ሆኖ መቆየቱ አልበቃ ብሎ ዛሬም እንደሥጋት የሚታይበትና ተሳቅቆ የሚኖርበት ሁኔታ ወዴት ሊያመራን ይችላል? ይልቁንም በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደቱና በተለያዩ ታሪካዊ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ ክፍተቶችን በመሙላት ሙስሊሙ ማህበረሰብ በሀገሩ ጉዳይ “ያገባኛል” በሚል ስሜት ተገቢውንና/ገንቢ ሚና እንዲጫወት ማበረታታት የሀገርን አንድነትና ህልውና ለማረጋገጥ አይበጅም ወይ? ከዚህ በተቃራኒው፣ በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን “በአሸናፊነትና ተሸናፊነት መንፈስ” አብሮ መኖር የሚቻልበት ሁኔታ/ዕድል አለ ወይ? እያንዳንዱ ዜጋ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የዘር … ወዘተ ልዩነቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው በሀገሩ ጉዳይ እኩል የሚያገባው፣ እኩል የሚቆረቆርና እኩል የሚጠቀም (ዕድሎች ያሉት) መሆኑ ካልተረጋገጠ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ልትኖር ትችላለች ወይ? እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን በአግባቡ ለማዬትና ለመግባባት አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ ሆነን ማሰብ ይኖርብናል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያን አንድነትና ህልውና ለማረጋገጥ የግድ የሌላው ማንነት መገለጫዎችና እሴቶች መደፍጠጥ የለባቸውም፡፡ በዚህ ረገድ የክርስትናም ሆነ የእስልምና እምነቶች የየራሳቸውና የሚጋሯቸው እሴቶች እንዳሏቸው እሙን ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ሀገረ-ኢትዮጵያን በመገንባቱ ሂደት ከነበራት ሚና እና ካሳረፈችው ትልቅ አሻራ አንፃር እንደ (እምነት) ተቋም ትልቅ የሀገር ቅርስና መኩሪያ ናት፡፡ ግልፅ በሆኑ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች በቂ ዕድል ያልነበረው የእስልምና እምነትም ኢትዮጵያውያንን በባለብዙ ክሮች ከማስተሳሰርና የሀገርን አንድነት ከማጠናከር አንፃር የራሱን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች ቤተ-እምነቶችም ሀገራዊ ህልውናችንን በማረጋገጡና አንድነታችንን በማጠናከሩ ሂደት የየራሳቸውን ተገቢና/አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉና፣ እንደሚገባም መታወቅ አለበት፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መዘንጋት የሌለበት ኢትዮጵያውያን በዘር/በቋንቋ ተለያይተው እርስ በርስ እንዲተላለቁ በሚፈልጉ ኃይሎች ሴራና/ሥራ ዛሬ ላይ ምን ያህል ወደ ጫፍ እንደተገፉ ነው፡፡ በርግጥ ኢትዮጵያውያንን በዘርና/በቋንቋ መከፋፈል እንደታሰበው ቀላል ባይሆንም ላለፈው ግማሽ ምዕተ-ዓመት ያለማቋረጥና በስፋት ተሠርቶበታል፡፡ ይህን ተከትሎም የአንድነታችን መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ የጋራና/ሀገራዊ እሴቶቻችን ተሸርሽረው ህልውናችን (እንደ ሀገር) በቋፍ ላይ ያለበት ሁኔታ መፈጠሩን መካድ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት የማዳከምና እንደሀገር ህልውናችንን የማጥፋት ዓላማ/ፕሮጀክት ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ኢትዮጵያውያን በቀላሉ እርስ በርስ ሊበላሉ/ሊተላለቁ የሚችሉትና የነሱም ዓላማ/ፕሮጀክት ፍፃሜውን ሊያገኝ የሚችለው የሃይማኖት ግጭት በመቀስቀስ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ስለሆነም ወደ ሃይማኖት ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ ጉዳዮችን በጥንቃቄ ከመያዝ ይልቅ በአጉል ጀብደኝነት እነሱ ወዳስቀመጡት ወጥመድ ከማምራት መቆጠብ ይኖርብናል፡፡

አላህዬ/እግዚአብሔር ሆይ፣ ኢትዮጵያን አንተ ጠብቃት!!!

LEAVE A REPLY