ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሰሞኑን ከተለያየ አቅጣጫ ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየው የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና የስኮላስቲክ አፕቲቲውድ ውጤትን ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ተስተካክሎ እንደሚለቅየሀገር አቀፍ ፈተናና ምዘና ኤጀንሲ ገለጸ::
ኤጀንሲው ከፈተናው የመልስ ቁልፍ ጋር ተያይዞ የነበረው እርማት ተጠናቆ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ በድረ ገጹ እና በአጭርየጽሑፍ መልዕክት መመልከት እንደሚቻል ማረጋገጫ ሰጥቷል:: የዘንድሮው ፈተና በጥንቃቄ መካሄዱን ያስታወሱት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓርዓያ ገብረ እግዚአብሄር “የፈተናው ኮድ 21 እና 22 ” ግን ችግር እንደነበረባቸው አምነዋል::
ውጤቱ ቀደም ሲል በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እና በድረ ገጽ ሲለቀቅ ለተማሪዎቹ ይፋ የሆነው ውጤት ያልተስተካከለው ነበር ሲሉም ዘግይተውም ቢሆን አሳዛኙን ስህተት አምነዋል:: በአጭር የፅሁፍ መልዕክት የተለቀቀውን መረጃ ማጥፋት የሌላ አካል ሓላፊነት ነው ሲሉም ተደምጠዋል:: ከፈተናው ጋር ተያይዞ ለኤጀንሲው 10 ሺህ ያህል ቅሬታዎች ቀርበዋል:: አሁን ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ::
የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት እርማት ሃምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ቢጠናቀቅም ፈተናው ይፋ እስከሚደረግ ድረስ ባሉት ጊዜያትም መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ የማጣራት ሥራ ሢሰራ የተቋሙ ባለሙያዎች ሰሞኑን በተለያዮ ሚዲያዎች ሲገልፁ ነበር::
የማትሪክ ፈተና ማረሚያ ሶፍት ዌር እና የማረሚያ ማሽኑ ከእንግሊዝ ሀገር መጥቶ አገገልግሎት መስጠት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል:: ዘመናዊ ነው የተባለው ይህ ማሽን ከመምጣቱ በፊት “ኮብል” የሚባል ሶፍት ዌር ለፈተና ማረም አገልግሎት ይውል እንደነበር ሰምተናል::
የተፈጠረውን የውጤት መሳሳት ተከትሎ ወቀሳ ከትግራይ ክልል ከኦሮሚያ ክልል እና ከአዲስ አበባ መስተዳደር ት/ቢሮዎች በኹለት ቀናት ልዮነት የቀረበበት አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የሚያዘጋጀው የ10ኛ ክፍል ፈተናን ብቻ ነው::
የ12ኛ ክፍል ፈተና የዩንቨርስቲ መግቢያ በመሆኑ የሚያዘጋጀው እና የፈተናው አውጪ አዲስ አበባ ዮንቨርስቲ እንደሆነ ም በዛሬው ዕለት ተነግሯል:: የኤጀንሲው የሥራ ድርሻ ፈተናውን መረከብ ማሰራጨት ማረም እና ውጤት የመግለፅ እንዲሁም ሥራውን በበላይነት ማስተዳደር ነው:: የ12ኛ ክፍል የመልስ ቁልፍ የሚመጣውም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው::