ደሃን በማጥፋት ድህነትን መዋጋት አይቻልም! || ያሬድ ኃይለማርያም

ደሃን በማጥፋት ድህነትን መዋጋት አይቻልም! || ያሬድ ኃይለማርያም

የአዲስ አበባ መስተዳደር የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ በሚል የፈረጃቸውን የእኔ ቢጤዎች እና ሴተኛ አዳሪዎችን ከከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ለማወገድ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ሽር ጉድ እያለ መሆኑን እና ሕግ ያረቀቀ መሆኑን በቅርቡ ገልጿል። ህብር ሬዲዮ እንደገለጸው በመስተዳድሩ የከንቲባው ጽ/ቤት የፕሬስ ጉዳይ ሹም ከፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (ኤኤፍ ፒ) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የአገሪቱን እና የከተማዋን መልካም ገጽታን የሚያበላሹት ከ50ሺህ በላይ የእኔ ቢጤዎች እና 10ሺህ የሚገመቱ ሴተኛ አዳሪዎች ከከተማው ጎዳናዎች የሚወገዱበት እርምጃ ሊተገበር ተቃርቧል” በማለት መግለጻቸውን ዘግቧል።

ከ90 በመቶ በላይ ድሃ ሕዝብ የያዘች እና በአለምም የድሃ ድሃ በሚል ማዕረግ የምትታወቅ አገር ድህነትን ለመቅረፍ ገና እረብ ያለው እርምጃ ሳትወስድ ድሃን ለማጥፋት መጣደፏ አጃይብ የሚያሰኝ ነው። ለነገሩ ለአንዳንድ ችግሮቻችን መስተዳድሩም ሆነ በአገር ደረጃ የሚወሰዱቱ እርምጃዎች እጅግ አስገራሚ እና በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች በመሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር ምን ያህል ያህል ይተዋወቃሉ የሚለውን እንድንጠየቅ የሚያደርጉ ነገሮች ደጋግመን እያየን ነው። ለምሳሌ ያህል ሌብነት በእግረኛ፣ በሞተረኛ፣ በመኪና እና በሌሎች የተደራጁ ቡድኖች በአደባባይ በሚፈጸምባት መዲና፤ አዲስ አበባ ሌብነት ለመከላከል ተብሎ በሞተር አሽከርካሪዎች ላይ የተወሰደው የጅምላ እቀባ፣ ፈተና እንዳይሰረቅ በሚል የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናዎች ሲቃረቡ የኢንተርኔት አገልግሎት ለቀናቶች ማቋረጥ እና እነኚህን የመሳሰሉ አንዱን ችግር በሌላ ችግር የመቅረፍ አካሄድ ግራ ከማጋባት ባለፈ የአስተዳዳሪዎቹንም ብቃት እና ለሕዝብ ችግር ያላቸውንም ቀረቤታ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። የተደራጀው ሌብነት በመኪና ቢሆን የሚካሄደው ምን ሊደረግ ይሆን?

ወደ ተነሳሁነት ዋና ጉዳል ልመለስና በልመና እና በሴተኛ አዳሪነት ሥራ በተሰማሩ የአገሪቱ ዜጎች ላይ መስተዳድሩ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ሰብአዊነት የጎደለው እና መንግስት ድህነትን ለማጥፋት በቅድሚያ ማከናወን የሚገባውን ሥራዎች ሰርቶ ሳይጨርስ በድሃ ላይ ለመዝመት ማሰቡ ደግሞ የአስተዳደሩን ብልሹ አተያይ ከወዲሁ የሚያሳይ ነው። እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለ የድሃ ደሃ አገር አይደለም በሰለጠኑት እና በሃብት በተትረፈረፉት አገሮች እንኳን የመንገድ ላይ ለማኝ እና ሴተኛ አዳሪ አይታሰርም፣ አይሳደድም ወይም ከከተማ እንዲወገድ አይደረገም። አንዳንዱ አገር ሴተኛ አዳሪነት እንደ ማንኛውም የንግድ ሥራ ጭምር ተቆጥሮ የግብር ከፋይ ኮድ ተሰጥቷቸው እና ፍቃድ ተሰጥቷቸው በአደባባይ እንደልባቸው እና ሙሉ ጥበቃ ተደርጎላቸው ይሰራሉ። እኛ ጋ ይህ ይሁን እያልኩ አለመሆኑ ይታወቅልኝ። ነገር ግን እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ከጎዳና ላይ ለማጽዳት ሕግ ከማርቀቅ እና ከመፎከር በፊት ዜጎችን ለልመና እና ለሴት አዳሪነት የሚዳርጉትን ዋና ዋና ምክንያቶችን በቅጡ ማጥናት እና ምንጩን ለማንጠፍ ማቀድ ይቀድም ነበር።

ኢንጂነር ታከለም ሆኑ አብረዋቸው ሃሳቡን የሚገፉ የመስተዳድሩ አካላት የሚያስተዳድሯትን ከተማ እና የሚመሩትን አገር ባህሪ በቁጡና በደንብ ያጠኑት እና ያወቁት አልመሰለኝም። የአዲስ አበባ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና ሴተኛ አዳሪዎች ለመስተዳድሩ ተሿሚዎች እና በቅንጦት ለሚኖረው የከተማዋ ነዋሪ የአይን ቁስል እንደሆኑባቸው ግልጽ ነው። የአዲስ አበባን አውራ ጎዳናዎች ከእነዚህ ድህነት ገፎት አደባባይ ላይ ካሰጣቸው ዜጎች በማጽዳት ግን የኢትዮጵያን ድህነት ወይም የከተማዋን እውነተኛ ገጽታ መሸፈን አይቻልም። ከንቲባው ከጥቂት ወራቶች በፊት የአዲስ አበባን የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ ተለያዩ የማኖሪያ ተቋማት ለማስገባት ዘመቻ ጀምሬያለው በማለት በየጎዳናው ላይ ሕጻናት ሲሰበስቡ የተነሱትን ፎቶ በየማህበራዊ ድህረ ገጹ ለቀው እና ዜናውም በአገሩ ተናኝቶ አይቻለው። ያን ጅምራቸውን የት አድርሰውት ይሆን? በወቅቱ የተሰማኝ ነገር ነገርየው እጅግ ተገቢ እርምጃ ቢሆንም ከገጽታ ግንባታ የዘለለ መሆኑ ስጋት ፈጥሮብኝ ነበር። ዛሬም የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በመንገድ ላይ ተዳዳሪዎች እንደተሞሉ ናቸው። ያንን ፕሮጀት ፍሬውን ሳያሳዩን ድሆቹን ከመንገድ ለማጥፋት ሕግ ማርቀቅ መጀመራቸው የበለጠ ለገጽታ ግንባታ የሰጡትን ክብደት እንጂ ሰብአዊነታቸውን አያሳይም።

ወያኔም ይችን ድሃን ከጎዳና ላይ የማራቅ ስልት በከፋ ሁኔታ ደጋግማ ሞክራዋለች። አዲስ አበባ ከሚመጡ አለም አቀፍ እንግዶች አይን ድሃን ለማራቅ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የእኔ ቢጤዎች እና ሴተኛ አዳሪዎችን አፍሰው በሌሊት ከአዲስ አበባ አርቀው በመጣል እና ወደ ከተማዋ እንዳይመለሱ በማድረግ የጅብ እራት ያደረጓቸው ዜጎች ነበሩ። ይህ አስነዋሪ እርምጃ በወቅቱ በኢሰመጉ ተጣርቶ መግለጫ ወጥቶበታል። ዛሬ መስተዳድሩ ይህን አይነት አስነዋሪ ድርጊት ይፈጽማል ብዮ ባላስብም የእነዚህን መጠጊያ የሌላቸው ድሆች እንቅስቃሴ በሕግ ለመገደብ የጀመረው እንቅስቃሴ ግን አልሸሹም ዞር አሉ ነው የሚሆነው።

የዛሬ ሃያ አመት ግድም በአዲስ አበባ ከተማ በልመና እና በሴተኛ አዳሪነት በተሰማሩ ዜጎች ላይ ያተኮረ እና አንድ አመት ተኩል ግድም በወሰደ ጥናት ላይ የመሳተፍ እድል ገጥሞኝ ነበር። በአዲስ አበባ ውስጥ እንኳን መንግስት የከተማው ነዋሪ ጭምር የማያውቀው ብዙ ጉድ እንዳለ የታዘብኩበት እና እንደ ዜጋ እራሴም የተሸማቀቅኩበት ብዙ ገበናችንን አይቻለሁ። አዲስ አበባ ቢያጠኗት የማታልቅ የጉድ ከተማ ነች። በውስጧ ብዙ አይነት ሕይወትን የያዘች እና ብበዙ ድሃ ዜጎች ገበና ሸፋኝ ከተማ ነች። ችግሩ ገበናዋን አስተዳዳሪዎቿም ሆኑ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ አያውቀውም። የሚያስተዳድሯትን ከተማ የማያውቁ አስተዳዳሪዎች ታክተው ትተዋት እሲኪሄዱ የነሱንም ገበና ተሸክማ የምትቆይ ጉደኛ ከተማ ነች።

በሴተኛ አዳሪዎች ላይ ያደረግነው ጥናት እና የሰማናቸው የህይወት ታሪኮች ቢጻፉ መጻህፍት ይወጣቸዋል። ከ14 ዓመት ህጻን ሴተኛ ዳሪ አንስቶ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ታናናሽ ወንድም እና እህቶቿን ለማስተማር እና ለማስተዳደር በአንድ ምሽት ከ24 ወንዶች ጋር በየተራ ግንኙነት አድርጋ በስተመጨረሻ እራሷን ስታ የወደቀችውን የጎጃም በረንዳ ወጣት ሴት ታሪክ ከራሳቸው ከባለታሪኮቹ አንደበት ሰምቻለሁ።

ባለሥልጣናት በሚሊዮን ገንዘብ በሚቆጠር ወድ መኪኖች፣ በጠንጣለሉ ቪላዎች፣ በውድ ሆቴሎች በሚንፈላሰሱባት እና ባስነጠሳቸው ቁጥር ከአገር ውጭ ውጥተው በአውሮፓ እና በአሜሪካ ህክምና እንዲያገኙ በምታደርግ አገር ውስጥ የኑሮ ዋስትና አጥተው ጎዳና ላይ የሚለምኑ እና ሰውነታቸውን የሚሸቅጡ ዜጎች ቁጥር ቢበረክት ምን ይገርማል። እያንዳንዱ ዜጋ በአገሪቱ ሃብት እኩል የመጠቀም መብት እና ድርሻ እንዳለው ባልተቀበለች አገር ውስጥ የሺዎችን ድርሻ ለአንድ ድንቁርና ለተጫነው እና ሰብአዊነት ከውስጡ ተንጠፍጥፎ ላወጣ ባለስልጣን ምቾት እና ድሎት የምታውል አገር በጎዳና ተዳዳሪ ዘጎች ብትወረር ምን ይደንቃል።

ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ከድህነት እና ከድሃ ጋር በተያያዘ የሚናገሩት ሁለት ቁምነገር ይህን እየጻፍኩ ወደ አዕምሮ ስለመጣ ላካፍላችሁ። አንዱ “ድሃ ባይኖር ኖሮ ሃብታም ተብድሎ አያድርም ነበር” የምትለዋ ነች። አዎ ማህበራዊ ፍትህ በተጓደለበት፣ ሙስና ያለቅጥ በተንሰራፋበት፣ ግለኝነት በነገሰበት እና ለድሃ አሳቢ መንግስት በሌለበት ስፍራ ሁሉ የሚሊዎኖች ድህነት የጥቂቶች የብልጽግና ምንጭ ይሆናል። ዘርፎ የበለጸገውን ባለሃብት እንተወው እና ለአንድ ባለሥልጣን ምቾት ተብለው የሚበጀት ገንዘብ ለስንት ድሃን የመኖር ዋስትና እና መሰረታዊ ነገሮች ሟሟያ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን ለእናንተው እተዋለሁ።

ሁለተኛው የፕ/ሮፍ ምክረ ሃሳብ ድህነትን የመርሳት በሽታችንን የሚያሳይ ነው። ምን ይላሉ “እንደ ድህነት ቶሎ የሚረሳ ነገር የለም፤ እኔም ድህነቴን እንዳልረሳ ድሆች ያሉበት አካባቢ መኖርን እመርጣለሁ። ድህነቴን ካልረሳው ድሃንም አረሳም፤ ያለኝን በወር በወር ከድሃ ጋር እካፈላለሁ።” እያሉ ድህነታችንን ቶሎ እንዳንረሳ እና በድሃ ላይ እንዳንጨክን እና እንዳንከፋ ደጋግመው ያስተምሩን ነበር። ድሃ ሰው ድህነቱን ቢረሳ ኩነኔው ለራሱ ነው። በሌሎች ድሆች ላይ የሚያደርሰውም ጉዳት ያን ያህል ላይሆን ይችላል። ድሃ ሕዝብ የሚያስተዳድር ድሃ መንግስት ድህነቱን ቶሎ ሲረሳ እና ከተማዋን የኃብታሞች ደሴት ለማድረግ እንቅልፍ ሲያጣ ግን አደጋው ብዙ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው ሕዝቧ ትልቁን ቁጥር በሚይዝበት አገር ድሃን ከመንገድ ለማራቅ መዳከር ውድቀትን መለመን ነው። በሞቀ ጎጇቸው ውስጥ እየሆሩ በድህነት አቅሙ የጣላትን ደሳሳ ጎቾ በላዩ ላይ አፍርሰው ሲያበቁ መንገድ ላይም ለምኖ እንዳያድር ሕግ የሚያወጡ እና ስልት የሚነድፉ ሹመኞች ጸባቸው ከድሃ እንጂ ከድህነት ሊሆን አይችልም። ባለፉት 27 የታከለ ኡማ ፓርቲ ኢህአዴግ መኖሪያ ቤታቸውን እያፈረሰ ለጎዳና ላይ ሕይወት የዳረጋቸውን ዜጎች የፈረሰው ቤት ይቁጠራቸው።

የአዲስ አበባ መስተዳድርም ሆነ የአገሪቱ መንግስት እንዲህ አይነት የዜጎችን መሰረታዊ መብት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እና በተለይም ድሃውን የአገሪቱን ሕዝብ የመኖር ዋስትና የሚያሳጡ እርምጃዎችን ለመውሰድ ከመሞከር በፊት ለዜጎች ድህነት እና ለጎዳና ሕይወት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ለማንጠፍ ቢሰራ መልካም ነው። ይህ ደግሞ እንዲህ በጥድፊያ በአንድ አመት አይደለም በአምስት እና አስር አመትም ውስጥ የሚሳካ ነገር ስላልሆነ ቅድሚያ ድህነትን ለማጥፋት ይሰራ። ድሃነት መአረግ ስላልሆነ ማንም መርጦ የገባበት ህይወት አይደለም እና ድህነት ሲጠፋ ድሃም እቤቷ ትሰበሰባለች። ድሃ ላይ ያነጣጠሩ የጽዳት ዘመቻዎች ግን ወጡ ሳይወጠወጥ … ነው የሚሆነው።

በቸር እንሰንብት!

LEAVE A REPLY