ሐሙስ ዕለት በውጫሌ ከተማ ሕይወታቸው ካለፉት ሰዎች መካከል ሁለቱ ሴቶች ናቸው

ሐሙስ ዕለት በውጫሌ ከተማ ሕይወታቸው ካለፉት ሰዎች መካከል ሁለቱ ሴቶች ናቸው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በደቡብ ወሎ ዞን፤ አምባሰል ወረዳ ውጫሌ ከተማ በአካባቢው ወጣቶችና በፀጥታ ኃይል መካከል በተፈጠረ ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል:: በግጭቱ ሰባት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ሐሙስ ዕለት ውጫሌ ከተማ በተፈጠረው አለመግባባት ሕይወታቸው ካለፉት ሰዎች መካከል ሁለቱ ሴቶች ናቸው።

በሥፍራው በተነሳው ግጭት ከሞቱት በተጨማሪ አምስት ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በደሴ ሆስፒታልና በተለያዮ የጤና ተቋማት ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ:: ነሐሴ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ለሰው ሕይወት መጥፋት መንስዔ የሆነው ግጭት የተቀሰቀሰው ለአርሶ አደሮች ካሳ ተከፍሎ ለመንግሥት ሠራተኞች የተሰጠ መሬት ነው::

ይህ ግጭት ከመፈጠሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነሐሴ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ቦታውን ለመለካት የሄዱ ባለሙያዎች በአካባቢው ወጣቶች ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል በሚል በርካታ ወጣቶች በፖሊስ መታሰራቸውን ተከትሎ ግጭቱ እንደተከሰተ አንዳንድ የአካባቢው ተወላጆች ይናገራሉ:: ለቤት መስሪያነት የተሰጠው ቦታ የሚገኘው ከውጫሌ ከተማ ሦስት ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን ልዩ ስሙም አበጋር ሜዳ ተብሎ የሚታወቅ ነው።

በሐምሌ ወር ከአካባቢው ለተነሱ አርሶ አደሮች የመሬት ካሳ እንደተከፈለ የተናገሩት ዋና ኢንስፔክተር መኮንን፤ ግጭቱ የተከሰተው የከተማው ማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎች ቦታውን በመለካት ላይ ሳሉ ወጣቶች ተሰባስበው በመምጣታቸው ግርግር እና የቃላት ልውውጡ ወደ ፀብ በማምራቱ እንደሆነ ገልፀዋል::

የወረዳው የፀጥታ አካላት በቦታው ተገኝተው ለማረጋጋት ሞክርው የነበረ ቢሆንም “ወጣቱ ሆ! ብሎ በመውጣት የፀጥታ ኃይሉ ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ” ሲሉም ስለ ግጭቱን ዋነኛ መነሻ ምክንያት ተናግረዋል። ፖሊስ ሁኔታውን ለማረጋጋት የተኩስ ድምፅ ቢያሰማም “የወጣቶቹ ጥያቄ ቦታውን ልቀቁልን የሚል ስለነበር፤ ሰላም ከተፈጠረ ብለን ቦታውን ለቀን ወጥተናል” በማለት ጉዳዩን በትዕግስት ለማለፍ ሙከራ መደረጉን ጠቁመዋል።

የመጀመሪያውን ክስተት ተከትሎ በማግስቱ ‘መሬቱ ለእኛ ነው የሚገባን’ የሚሉ ወጣቶች ተሰባስበው ሰልፍ እንዳካሄዱና የታሰሩ ወጣቶችንም ለማስፈታት ወደ ፖሊስ ጣቢያ አምርተዋል። ጣቢያ ከደረሱ በኋላ ግን ወጣቶቹ ቁጥራቸውን ጨምረው በግምት 300 የሚሆኑ ወጣቶች በመሰባሰብ በአምባሰል ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ እስረኞችን ለማስፈታት አላስፈላጊ ሙከራ አድርገዋል።

ተደራጅተው በመጡት ሰዎች ጥይት በመተኮሱ እና  ጣቢያውም በድንጋይ በመደብደቡ ፤ ፖሊስም ይህንን ለመከላከል ጥረት ማድረጉን ያመላከቱት የወረዳው ፖሊስ ሓላፊ በክስተቱ ሕይወታቸው ያለፈና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ከማን በተተኮሰ ጥይት እንደተጎዱ አላውቅም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በተኩሱ ሕይወታቸውን ያጡትም ሆነ ጉዳት ያጋጠማቸው የግጭቱ አካል ያልነበሩና በነዋሪዎቹ አጠራር ‘ተባራሪዎች’ ያሏቸው ንፁሃን ሰዎች መሆናቸው ታውቋል።

LEAVE A REPLY