ቢቢሲ || የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኝ ፍርድ ቤት ውጪ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ የተያዘው ጋዜጠኛ ምስጋናው ጌታቸውን በአስቸኳይ እንዲለቁ ለጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ድርጅት ሲፒጄ ባወጣው መግለጫ ጠየቀ።
ኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ) እንዳለው የሳምንታዊዋ ‘ኢትዮጲስ’ ጋዜጣ ዘጋቢ የሆነው ምስጋናው ከአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውጪ ሄኖክ አክሊሉ የተባሉ ጠበቃን ሲያናግር የተያዘ ሲሆን፤ አሁን በጸረ ሽብር ሕጉ እንደተወነጀለ ምስጋናው የሚሰራበት ጋዜጣ አርታኢ እስክንድር ነጋ ተናግረዋል።
ሔኖክ ለሲፒጄ እንደተናገረው ሁለት ጋዜጠኞችን ጨምሮ በፀረ ሽብር ህጉ ተወንጅለው ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ሲሆን ምስጋናው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መረጃ ለማግኘት እያናገረው እንደነበር ገልጿል።
አስክንድርና ሄኖክ እንደሚሉት ጋዜጠኛው መነጽሩ ላይ በተገጠመ ካሜራ ከጠበቃው ጋር የሚያደርገውን ቃለ ምልልስ እየቀረጸ እንደነበረ አስረድተዋል። እስክንድር ጨምሮም አዳም ውጅራ የተባለ የባልደራስ ምክር ቤት አባል በተመሳሳይ መያዙንና ምስጋናው በሚታይ ሁኔታ ቪዲዮ ቢቀርጽ ጥቃት ይደርስብኛል የሚል ስጋት ስለነበረው ነው ይህንን መንገድ የተጠቀመው።
የፌደራል ፖሊስ ለሲፒጄ እንደተናገረው ምስጋናው በቁጥጥር ስር የዋለው በሕገ ወጥ መንግድ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ፊልም ሲቀርጽ መሆኑን ቢገልጽም የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ግን ምስጋናውና አዳም የተያዙት በአማራ ክልል ከተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘ መሆኑን ገልጿል።
የምስጋናውን መያዝ በተመለከተ የሲፒጄ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራት ተወካይ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ እንዳሉት “ቀደም ሲል ለነበሩ ጭቆናዎች መገልገያ የነበረው የጸረ ሽብር ሕጉ ጥቅም ላይ መዋል ኢትዮጵያ ወዳለፈው ተቃውሞንና ትችትን ወደማፈን እየተመለሰች መሆኑን ያመለክታል” በማለት ባለስልጣናት የታሰረውን ጋዜጠኛ እንዲለቁ፣ የጸር ሽብር ሕጉን ጋዜጠኞች ላይ ከመጠቀም እንዲቆጠቡና መረጃ የማግኘትና የመናገር ነጻነትን የሚጠብቁ የሕግ ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ አቶ ዝናቡ ቱኑ ለሲፒጄ እንደገለጹት “በምስጋናውና በአዳም ላይ በአማራ ክልል ከተሞከረው መፈንቅለ መንግሥትና ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ግድያ ጋር በተያያዘ ተሳትፎ እንዳላቸው አሳማኝ ጥርጣሬ አለ” ብለዋል።
አቶ ዝናቡ አክለውም የግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር መዋል “ካላቸውና ከሚያራምዱት ወይም ከሚያሳትሙት ዘገባ ጋርም ቢሆን ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም” ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ጄይላን አብዲ በበኩላቸው ምስጋናው የተያዘው በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ፈቃድ ሳያገኝ መነጽሩን በመጠቀም ቪዲዮ ሲቀርጽ በአካባቢው በነበሩ ፖሊሶች በጥጣሬ መያዙን ይናገራሉ።
ሲፒጄ እንደሚለው ምስጋናው በግንቦት ወር ላይ አራት ኪሎ አካባቢ የሚፈርሱ ቤቶችን በሚዘግብበት ወቅት ለአጭር ጊዜ ተይዞ በዋስ ተለቆ ነበር።