ወጣቱን ክፉኛ ሲደበድቡ በማህበራዊ ሚዲያ የታዩትየአዲስ አበባ ፖሊሶች ታሰሩ
ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች ንጹሑን ዜጋ በአስከፊ ሁኔታ ሲደበድቡ እና ድርጊቱን ሲከላከሉ የነበሩ የዕድሜ ባለጸ ባለጸጋ እናትን ሲያዋክቡ የታዩት፣ ሁለት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታወቀ፡፡
እጅግ አሳፋሪ ተግባር ሲፈፅሙ በሞባይል ስልኮች የተቀረጹት የፖሊስ አባላት ድርጊት በርካታ ነዋሪዎችን ያስቆጣ ነበር፡፡ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በስፋት ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ ከተሞች ተመልምለው በመምጣት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል እንዲሆኑ የተደረጉት የጸጥታ አካላት፤ ለወራት በምሽት በማይረቡ ሰንካላ ምክንያቶች፣ የአዲስ አበባን ወጣቶች ሲደበድቡ እና ሲያሰቃዩ እንደሚታዩ ተደጋጋሚ አስተያየቶች ሲደመጡ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
የኢ/ር ታከለ ኡማ አስተዳደር ከወረዳ እስከ መዘጋጃ ቤትመስተዳድር ያለውን ወሳኝ ቦታ፤ እንዲሁም የተገኘውን ክፍት የሥራ መደብ በኦሮሞ ተወላጆች የማዋቀሩ ሥራ ወደ ከተማዋ ፖሊስ ተቋምም በግልጽ መሸጋገሩ የአደባባይ መስጢር ከሆን ሰነባብቷል፡፡
“ፊንፊኔ ኬኛ” ፖለቲካን በአዲስ አበባ እና መላው ኦሮሚያ ክልል ላይ በግልጽ ከማቀንቀን ባሻገር፣ ቅስቀሳ ከሚያካሂዱ “የኦዴፓ ቄሮዎች” ጋር በተደጋጋሚ ሲወያዩ የሚያሳየው ፎቶ በማስረጃነት የሚቀርብባቸው ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ፤ አዲስ አበባን ከዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች ነጥቀው፣ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ለማድረግ የፖሊስ ተቋሙ በዚህ እሳቤ ተቀርጸው ባደጉ የኦሮሞ ወጣቶች እንዲዋቀር በስውር እየሰሩ መሆናቸው ይነገራል፡፡
አሁን ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስን በብዛት የያዙት የኦሮሚያ ተወላጆች ፈጽሞ ከነዋሪው ጋር መግባባት እንዳቃታቸው ነው ሁኔታዎች የሚጠቁሙት፡፡ በተለይ ከታክሲ አሽከርካሪዎች እና በየአካባቢው ከሚገኙ ወጣቶች ጋር መጣጣም አልቻሉም ነው የሚባለው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የተከሰተው ፖሊሶቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲነገራቸው የቆየው የብሔር ፖለቲካ፣ በዚህ ወቅት በነጃዋር መሐመድ ከሚነዛው የመጠፋፋት ቅስቀሳ ጋር ተቆራኝቶ በውስጣቸው የጥላቻ ስሜትን ሊወልድ በመቻሉ ነው የሚል ግምት አሳድሯል፡፡
በቅርቡ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ከተማ ፖሊስ አባላት፤ አንድን ወጣት በጠራራ ፀሐይ አስተኝተው ያለርህራሄ ሲቀጠቅጡት ታይተዋል፡፡ ማንም ዜጋ እንኳን በፖሊስ ያለአግባብ ሊደበደብ ቀርቶ ያለ ፍርድ ቤት መያዣ ከመንገድ ላይ ተጎትቶ እንደማይወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረው የነበረ ቢሆንም ፖሊሶቹ ግን በማንአለብኝነት ሲደበድቡ ተመልክተናል፡፡
“ስለእግዚአብሄር ብላችሁ አትደብድቡት” ያሉ እናቶችን ሲገፈታትሩ፣ ብሎም ሲያንጓጥጡ የተስተዋሉት ፖሊሶች፤ ድብደባው እንዳይቋረጥና ሰው የተጎዳውን ወጣት እንዳያስጥል ሌላኛው ባልደረባ ጥይት በመተኮስ ዜጎችን ሲያሸብር ታይቷል፡፡
በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጎፋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በድለላ ሥራ ሕይወታቸውን የሚገፉ ግለሰቦች በፈጠሩት አለመግባባት ላይ ጣልቃ ገብተው፤ ፖሊስ ጣቢያ አልሄድ ብሎናል ያሉትን ወጣት የደበደቡት ፖሊሶች ዛሬ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ቢሰማም፤ ከከተማው ፖሊስ ሓላፊዎች ዘንድ የተለመደው ሀሰተኛ መግለጫ ሲሰጥ ተስተውሏል፡፡
አሳፋሪውን ድርጊት የፈጸሙትን ፖሊሶች አስረን ምርመራ እያደረግን ነው ያሉት ከፍተኛ አመራር፤ ግለሰቦቹ የተደበደቡት ከፖሊሶች ላይ መሳሪያ ለመንጠቅ በመሞከራቸው ነው በማለት፣ ያልበሰሉ አባሎቻቸውን ድክመት ለመሸፈን ሞክሯል፡፡ በቀን፣ በመሀል አደባባይ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዛቢዎች ባሉበት፤ መሳሪያ ነጠቃ ተሞክሯል መባሉ የመግለጫውን ታማኝነት አጠያያቂ አድርጎታል፡፡
እነ አረጋዊ በርሄ ለአማራ እና ትግራይ ወጣቶች “የወዳጅነትመድረክ” ሊያዘጋጁ ነው
ትዴት ( የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር) የአማራ እና የትግራይ ክልል ወጣቶች የሚሳተፉበት የወዳጅነት መድረክ ለማዘጋጀት መሰናዶአቸውን ያጠናቀቁ መሆኑ ተገለጸ፡፡
“ቀጣዩ ትውልድ” በሚል መርህ በባህርዳር፣ ቆቦ፣አዲስአበባ፣ አላማጣ እና መቀሌ ከተሞች በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር ይከናወናል የተባለው የወዳጅነት መድረክ፤ በኹለቱ ክልሎች አመራሮች መካከል የሚታየው አተካራ ወደ ህብረተሰቡ እንዳይወርድ፣ በተለይም በወጣቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ ፈጥሮ የከፋ ችግር እንዳይከሰት ይረዳል ተብሏል፡፡
ከአርባ ዓመት በፊት ሕወሓትን በመመስረት የትጥቅ ትግል ለማድረግ፣ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ትምህርታቸውን በማቋረጥ ደደቢት በረሃ የገቡት የወያኔው ቡድን መስራቾች እና የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች፤ በነበሩት ግለሰቦች ነው የወዳጅነት መድረኩ የተወጠነው፡፡
ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እና ኢ/ር ግደይ ዘርአፂዮን በፈታኙ ዘመን የትግራይ ሕዝብን ከጭቆና ለማላቀቅ፣ ሓይልን አማራጭ አድርገው በመውሰድ የጫካውን ቡድን ከትግል አጋሮቻቸው ጋር ቢወልዱትም፤ የእዛን ዘመኑ“ማ.ገ.ብ.ት” የአሁኑ ሕወሓት የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ከሚሆን፣ ጥቂቶች ለጥቅማቸው የሚዘውሩት “የማፊያ ቡድን” እንዲሆን ፅኑ ፍላጎት ባላቸው አቦይ ስብሃት ነጋ እና ወዲ ዜናዊ ሴራ ከድርጅቱ እንዲባረሩ የተደረጉ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ስልጣን በጨበጡ ማግስት የተገፉትን የሕወሓት መስራቾች ጥሪ አቅርበውላቸው በስደት ሕይወት የመሰረቱትን ት.ዴ.ት የተሰኘ ድርጅት ይዘው አገር ቤት ከገቡ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ የእነ ግደይ ዘርአፂዮንን ወደ አገር ቤት መመለስ ለፖለቲካ ጥቅሙ ሊጠቀምበት የፈለገው ሕወሓት፤ ከመሸገበት መቀሌ ሆኖ ክልሉን እንዲጎበኙ እና ሥራውን እንዲመለከቱለት በራሱ ወጪ ትግራይ ድረስ የወሰዳቸው ሁለቱ አመራሮች ከ44 ዓመት በኋላ አዲስ አበባን ከረገጡ አንድ ሳምንት እንኳን ሳይሞላቸው ነበር፡፡
ትግራይን ተዘዋውረው የጎበኙት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እና ኢ/ር ግደይ ዘርአፂዮን እውነታውን ክደው ከሕወሓት ጎን ከመለጠፍ ይልቅ ለውጡን ያመጡትን አካላት በይፋ ማመስገን መጀመራቸው የህወሃት አመራሮች ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ ከምንም በላይ ከዋነኛ ተፎካካሪያቸው አረና ጋር አብረው ለመስራት መስማማታቸው የትዴት አመራሮች እና አባላትን በሰበብ አስባቡ እንዲታሰሩ አድርጓቸዋል፡፡
ከለውጡ ማግስት አንስቶ በዚህን መሰሉ ፈታኝ ሂደት ውስጥ ያለፈው ትዴት በአዴፓ እና በሕወሓት አመራሮች ሽኩቻ የትግራይ እና የአማራ ወጣቶች ወደ ለየለት ግጭት እንዳይገቡ፣ ፖለቲከኞችም የሚታየውን ክፍተት የበለጠ እንዳያሰፉት በማሰብ የወዳጅነት መድረኩን በተለያዩ ከተሞች ላይ በመስከረም 2012 ዓ.ም ለመጀመር አስቧል፡፡ ፓርቲው በራሱ ተነሳሽነት ፕሮግራሙን ያዘጋጀ ቢሆንም ዕቅዱን በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር ከአማራ ክልል መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እንደጠየቀ ከትዴት አባሎች ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
እስካሁን ድረስ በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ሀሳቡን በመልካምነት የተቀበለው የአማራ ክልል መንግስት አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ቃል ገብቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወዳጅነት መድረኩን ለመደገፍ ፍቃደኛ ከሆኑ ግለሰቦች ገንዘብ መሰባሰብ መጀመሩን ምንጮቻችን አረጋግጠውልናል፡፡
ትዴት (የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር) የወዳጅነት መድረኩን ከማዘጋጀት በዘለለ ተጨማሪ ሚና እንደማይኖረው፣ ውይይቱ በሁለቱ ክልል ወጣቶች ብቻ የሚከናወን የወዳጅነት መድረክ እንደሆነም ለማወቅ ችለናል፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሕጻናትመድኃኒት አያገኙም
በኢትዮጵያ ውስጥ በኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው እንደሚገኝ ከሚገመት 54 ሺህ ሕጻናት መካከል 39 በመቶ የሚሆኑት ብቻ የፀረ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድኃኒት እንደሚያገኙ ተሰማ፡፡ መረጃውን ያወጣው የብሔራዊ ኤች አይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ነው፡፡
በሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ያለው ሕክምና በሁሉም ቦታ የተዳረሰ አለመሆኑ፤ እንዲሁም ሕብረተሰቡ ስለ በሽታውያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን የታየው ችግር እንዲከሰት መንስዔ ሆኗል ነው የተባለው፡፡ ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ሕጻናት ከተወለዱ ጀምሮ ባሉት ከ4 እስከ 6 ሳምንታት ውስጥ የኤች .አይ.ቪ ኤድስ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው እና ተገቢውንም ሕክምና ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸው ይታወቃል፡፡
አሳዳጊዎች በዚህ በኩል የሚጠቁ ሕጻናትን ወደ ህክምና ለማምጣት ፍቃደኛ አለመሆናቸው፣ ከወረዳ እስከ ፌደራል የሚመጣው የመረጃ ፍሰትም ያልተሟላ እና የተደራጀ አለመሆኑ የተጠቃሚዎቹን ቁጥር ለማሳደግ ዕንቅፋት ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል ከተባሉ ሕጻናት ውስጥ አብዛኛው መድኃኒት አለማግኘታቸው አሳሳቢ ደረጃ በመድረሱ በቀጣዩ አዲስ ዓመት ሕጻናት የሚመረመሩበት እንዲሁም ሕክምናውን የሚያገኙበት አዲስ አሠራር ለመዘርጋት በጤና ጥበቃ ሚኒስትር በኩል ተወጥኗል።
ንግድ ባንክ፣ ዳሽንና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ 300 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰረቁ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ (በተለይ በምዕራብ ወለጋ) ሲካሄድ የቆየው የባንክ ዘረፋ ጋብ አለ በሚባልበት ወቅት፤ በአዲስ አበባ ሦስት ባንኮች ዘረፋ መካሄዱ ተሰማ፡፡
ለየት ባለ መንገድ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የተለያዩ ባንኮች ላይ የተፈጸመው ስርቆት ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ በንግድ ባንክ፣በዳሽን ባንክ እና በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ላይ ነው ስርቆቱ የተፈጸመው፡፡
እሁድ ማለዳ ለንባብ የበቃውና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚዘጋጀው “ካፒታል” ጋዜጣ እንዳስነበበው ከሆነ ከእነዚህ ሶስት ባንኮች 300.000.000 (ሦስት መቶ ሚሊዮን ብር) በሕገ ወጥ መንገድ ተሰርቋል፡፡
ከታላቁ ንግድ ባንክ፣ ዳሽን ባንክ እና ከኦሮሚያ ኢንተርናሺናል ባንክ አካውንት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የተሰረቀው በተጭበረበረ ቼክ ነው ተብሏል፡፡
ከጉዳዩ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ፖሊስ እስካሁን 23 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያካሄደ ሲሆን፤ የድርጊቱ አቀናባሪ ግን ከአገር እንደወጣ ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጃፓን ገብተዋል
ኢትዮጵያ ከተለያዮ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ወደ ተለያዮ አገራት በመጓዝ ላይ ያሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጃፓን ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጃፓን ሲገቡ የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የለውጡ ቡድን ፊታውራሪ የዘመነችው ጃፓን ጎራ ያሉት በአነጋጋሪዋ ደቡብ ኮሪያ የነበራቸውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማጠናቀቅ እና በጃፓን-አፍሪካ የልማት ፎረም (የቲካድ ) ላይ ለመሳተፍ ነው ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ከጉባዔው በተጨማሪ ከጃፓን ከፍተኛ የስራ ሓላፊዎች ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል::ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጃፓን-አፍሪካ የልማት ፎረም (የቲካድ ) ላይ እንዲሳተፉ እና ከጉባዔው ቀደም ብሎም በጃፓን ጉብኝት እንዲያደርጉ በጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጥሪ ቀርቦላቸው እንደነበር አይዘነገም::
የደቡብ ክልል ም/ቤት መደበኛ ጉባዔውን ከስምንት ወር በኋላ ሊያካሂድ ነው
ለስምንት ወራት መሰብብ ያልቻለው እና በዋና መቀመጫው ሀዋሳ በኢጄቶ የተባረረው የደቡብ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር አራተኛ አመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ከነሐሴ 24 ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገለጸ::
የክልሉ ምክር ቤት እንደገለጸው ከሆነ ምክር ቤቱ በከሁለት ቀናት በኋላ በሚጀምረው ስብሰባ የ2011 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2012 በጀት ዓመት የስራ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ያጸድቃል:: በተጨማሪም ምክር ቤቱ የክልሉን የጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ዋና ኦዲት መስሪያ ቤትን ሪፖርትና እቅድን በማድመጥ ውሳኔ ያሳልፋል::
የምክር ቤቱ አባላት ከመደበኛ ጉባኤው አስቀድመው በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በኮማንድ ፖስት ስር በምትገኘው ሀዋሳ ከተማ ላይ እየመከሩ ይገኛሉ::
የሀገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታና ክልላዊ ጉዳዮች ምን ደረጃ ላይ ናቸው የሚለውንና በክልሉ እየተነሱ ያሉት የአደረጃጀት ጥያቄዎች የሚመለከት ሁለት አንኳር ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እየተነጋገሩ ያሉት የምክር ቤት አባላት ልዮነቶቻቸውን አስቀድመው ለመፍታት ጥልቅ ውይይት ጀምረዋል::
በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ማዕከል ምክትል ዋና አስተባባሪ አቶ መለሰ አለሙ መድረኩን እየመሩ ሲሆን የምክር ቤቱ አባላት በሀገራዊና ክልላዊ ነበራዊ ሁኔታ ላይ ግንዛቤያቸውን በማሳደግ የማስፈጸም አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ለማስቻል በውይይቱ ላይ ጥረት እየተደረገነው። በክልል ደረጃ በተነሳዉ የአደረጃጀት ጥያቄ ላይ በምሁራን የተጠናው ጥናት ለምክር ቤቱ አባላት ቀርቦ ምክክር ይረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።