የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም

ለሐጅ የተጓዙ 180 ኢትዮጵያውያን ምዕመናን በጂዳ ለእስር ተዳረጉ

በየዓመቱ ለሚከናወነው የሐጅ ሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ወደ መካ የሄዱ ምዕመናን ጨምሮ ለተጓዦች የምስጋና አቀባበል ዝግጅት ያደረጉ 180 ኢትዮጵያውን በሳዑዲ ዓረቢያ ጂዳ ለእስር መዳረጋቸው ተሰማ፡፡

ይማኖታዊ ጉዞዎች ላይ በጋራ ተሰባስቦ ማመስገን የተለመደ ከመሆኑ አኳያ ባሳለፍነው ሣምንት መጨረሻ በሥፍራው ላይ የተሰባሰቡ እና ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸውን ሰዎች ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡

በጉዳዩ ላይ በፍጥነት ጣልቃ የገባው ጂዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንሲላ ጽሕፈት ቤት የመኖሪ ፍቃድ ያላቸው 70 ኢትዮጵያውያን በተያዙበት ዕለት እንዲፈቱ አድርጓል፡፡ ጽ/ቤቱ በቀጣይ ቀናትም አስር ያህል የሐጅ ተጓዦችን ከእስር አስለቅሷል፡፡

በአሁኑ ሰዓት አንድ መቶ ያህል ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ሥር ናቸው፡፡ ታሳሪዎቹ ኢትዮጵያውን ፈቃድ የሌላቸውበመሆኑ ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በ2011 ዓ.ም የሐጅ ጉዞ ሐምሌ 5 ቀን የጀመረ ሲሆንእስካሁን ድረስ 15 ሺህ ያህል ምዕመናን ወደ ሥፍራዋ ተጉዘዋል፡፡ የሳዑዲ አረቢያ የሐጅ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ሐጅ ተጓዦች የሰጠው ኮታ 43.337 መሆኑ አይዘነጋም፡፡

በፓርላማ የፀደቀው ዓለም አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥርን የኢትዮጵያ መንግሥት ጣሰ  

መንግሥት በሀሳቡ ላይ ተስማምቶ የፈረመውን እና በሂደት በፓርላማ ያፀደቀውን የዓለም የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬሽንና ኮንቬሽኑን ለማስፈፀም በፓርላማው የወጣውን የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ የሚጥስ ተግባበመፈፀም ላይ ነው ተባለ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ታማኝ ግብር ከፋዮችን ዕውቅና ለመስጠት በቅርቡ አካሂዶት በነበረው ዝግጅት ላይ በአገሪቱ ብቸኛ የሆነውን የትምባሆ ኢንዱስትሪ በታማኝ ግብር ከፋይነት መሸለሙ ኮንቬሽኑን የሚጥስ ተግባር እንደሆነ በማስረጃነት ይጠቀሳል፡፡

ኢትዮጵያ የተቀበለችውን ዓለም አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬሽን በጣሰ መልኩ ለትምባሆ ኢንዱስትሪው የፕላቲኒየም ደረጃ እውቅና መሸለሙ መንግሥት ሕግ ተፃራሪ ነው የሚል ትችትን አድርሶበታል፡፡

የምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 የትኛውም የመንግሥት አካል የትምባሆ ኢንዱስትሪን ከሚያበረታታ ማንኛውም ዓይነት ድርጊት መቆጠብ ይኖርበታል ሲል ይደነግጋል፡፡

በሕግ ካልተፈቀደና ለቁጥጥር ዓላማ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር፣ የመንግሥት ተቋማትም ሆኑ ላፊዎች ከትምባሆ አምራች ኢንዱስትሪ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው እንደማይገባም በግልጽ አስቀምጧል፡፡

ከምንም በላይ የመንግሥት ተቋማትም ሆኑ ላፊዎች የትምባሆ ምርትን እና ድርጅት በበጎ መንገድ ሊያስተዋወቅ ከሚችል ማንኛውም ተግባር መቆጠብ አለባቸው ሲልም ያስጠነቅቃል፡፡

ይሁንና እነዚህን ሁሉ ስምምነቶች የፈፀመው የኢትዮጵያ መንግሥት “ጃፓን ቶኮባ ኢንተርናሽናል” ለተሰኘው ዓለም አቀፍ የትምባሆ አምራች የተሸጠውን ብሔራዊ የትምባሆ ኢንተርፕራይዝን በታማኝ ግብር ከፋይነቱ ሸልሞታል፡፡ ኮንቬሽኑንም ሆነ በፓርላማ የፀደቀውን ማስፈፀሚ አዋጅም በዚህ ድርጊቱ ሙሉ ለሙሉ መጣን በተግባር አሳይቷል፡፡

 ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የጀርመኑ “ሔስያን፣ የሰላም ሽልማት” አሸናፊ ሆኑ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  የአውሮፓውያኑ የ2019 የሔስያን የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው  ተነገረ፡፡ለኢትዮጵያዊው መሪ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ የሚገኘው  የፍራንክፈርት የሰላም ጥናት ማዕከል  ነው ሽልማቱን የሚሰጠው፡፡

ዶ/ር ዐቢይ አህመድ  በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ታሪካዊ ያለውን የሰላም ስምምነት በመፈጸማቸው የሔስያን  የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ተቋሙ ትናንት ይፋ አድርጓል፡፡ የፍራንክፈርት የሰላም ጥናት ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈጸሙትን የዕርቅ ተግባር “ታሪካዊ” ሲል ገልጾታል፡፡

በመጪው መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ፣ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሽልማቱን የሚቀበሉ ሲሆን፤ የክብር ሽልማቱ 25 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ስጦታን ይጨምራል ተብሏል፡፡

የፍራንክፈርት የሰላም ጥናት ማዕከል ሓላፊ እና የባለአደራ ቦርድ አባል የሆኑት ኒኮል ዳይትልሆፍ “ ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአፍሪካ ተስፋ ከሚጣልባቸው መሪዎች አንዱ ናቸው፤ ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት  በሔስያን የሰላም ሽልማት  ማክበር እና ማበረታታት እንፈልጋለን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡  በቀድሞው የሔሰን ግዛት  ጠቅላይ ሚኒስትር የተመሰረተው የሔስያን የሰላም ሽልማት 26 ዓመት ሞልቶታል፡፡        

የአዋሽ ኮምቦልቻ የባቡር መስመር ቢጠናቀቅም የኤሌትሪክ ኃይል አላገኘም

በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አማካይነት የተሰራው የአዋሽ  – ኮምቦልቻ የባቡር መስመር ግንባታ ቢጠናቀቅም የኤሌትሪክ ሃይል ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ኤሌትሪክ ከቀረበለት ግን ሥራ መጀመር ዝግጁ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡

አገልግሎት መስጠቱ መጓተት ዋነኛ መንስኤ ነው በሚል ቅሬታ የቀረበበት የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ይል በበኩሉ፣ ለኤሌትሪክ መስመር ዝርጋታ ክፍያ እንዳልተፈፀመለት እና አገልግሎቱን ለማቅረብም 18 ወራትን እንደሚፈጅበት ተናግሯል፡፡

የአዋሽ ኮምቦልቻ ሐራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ሥራ አስኪጅ አቶ አብዱልከሪም መሐመድ የባቡር መሥመር ግንባታው 99 በመቶ መጠናቀቁን ቢገልፁም፤ በእሳቸው እሳቤ አንድ ፐርሰንት ነው የተባለው የኤሌትሪክ ዝርጋታ ይህን ያህል ጊዜ ሳይከናወን የተጓተተበትን ምክንት ግን አልገለፁም፡፡ በአሠራር ረገድ አብዛኛው የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ከሌሎች አካላት ጋር የመቀናጀት ተግባር ስለማይታይባቸው እንዲህ ዓይነት ስህተቶች በተደጋጋሚ መከሰታቸው የተለመደ ሆኗል፡፡

ግንባታው የተጠናቀቀው የአዋሽ ኮምቦልቻ የባቡር መስመር ኤሌትሪክ እስኪገጠምለት ድረስ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ያለ ሥራ የሚቀመጥ ከሆነ ለሚደርሰው ኪሳራ ተጠያቂው ማነው? የሚለውን ጉዳዩ የሚመለከው መንግሥታዊ አካል ከወዲሁ ሊያስብበት ይገባል፡፡

9 ኪሎ ግራም ወርቅ በበሶማሌ ክልል በኩል ከአገር ለማውጣት ሲሞከር ተያዘ

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ዘጠኝ ኪሎ ግራም የሚመዝን ወርቅ በገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ ሲል መያዙ ታወቀ፡፡ ወርቁን ለማውጣት የተሞከረው በሶማሌ ክልል በኩል መሆኑን ከደረሰን ዜና መረዳት ተችሏል፡፡

9 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን ወርቅ አንድ ግለሰብ ከአገር ለማውጣት ሲሞክር ረጅም ክትትል ያደረገው ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በቦምባሳ ከተማ ላይ ነው በቁጥጥር ሥር ያዋለው፡፡

ወርቁን በሕገ ወጥ መንገድ  ከአገር ይዞ ሊወጣ ሲል ከተያዘው ወርቅ በተጨማሪ ሌሎች የተለያዩ የውጭ አገር ገንዘቦችም ይዞ ነበር፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ፤ ወንጀለኛው አርባ አንድ ሺህ ዶላር እና ሀምሳ አምስት ሺህ የሳዑዲ ሪያል በተቀያሪ ጫማዎቹ ውስጥ ደብቆ ነበር ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፊት ከወርቅ ንግድ ከፍተኛ የሆነ ገቢ ስታገኝ ቆይታለች፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ከወርቅ የውጪ ንግድ ከአራት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ ቢሆንም፤ ባለፈው ዓመት ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ግን ወደ 30 ሚሊዮን ዶላር ማሽቆልቁሉን የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡    

LEAVE A REPLY