ሕወሓት የአረና ፓርቲ ንብረት ናቸው ያላቸውን ፍየሎች አሠረ

ሕወሓት የአረና ፓርቲ ንብረት ናቸው ያላቸውን ፍየሎች አሠረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከፌደራል መንግሥቱ ማፈንገጡን በድርጊቶቹ በተደጋጋሚ ያሳየው ሕወሓት ንብረትነታቸው የአረና ትግራይ ፓርቲ አባል ናቸው የተባሉ አስራ ስድስት ፍየሎችን አስሯል:: የአረና ፓርቲ ሊቀመንብር አቶ አብርሃ ደስታ በላፈው ረቡዕ የፓርቲው አባል ንብረት የሆኑ 16 ፍየሎች በትግራይ ክልል ቆላ ተምቤን ወረዳ ንኡስ ወረዳ ወርቅ አንባ ቀይሕ ተኽሊ ቀበሌ ውስጥ መታሰራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋ።

የፍየሎቹ ባለቤት የሆኑት አቶ ዜናዊ አስመላሽ 16 ፍየሎቻቸው ታስረውባቸው እንደነበረ እና ተታስረው ከነበሩት ፍየሎች ሶስቱ አምልጠው ወደ ቤት መመለሳቸውን ገልጸዋል:: አቶ ዜናዊ አስመላሽ የአረና ፓርቲ አባልና የተንቤን አካባቢ አስተባባሪ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ለእስር ከመዳረጋቸው ባሻገር በተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎችን ይደርስባቸውም ነበር::

አቶ ዜናዊ ፍየሎቻቸው የታሰሩባቸው የአረና ፓርቲ አባል በመሆናቸው መሆኑን ይናገራሉ። ፍየሎቹ ዕሮብ እለት ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአንድ ሰው ተነድተው በአከባቢው በሚገኝ ሚሊሻ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ ከሰው መስማታቸውን አስታውቀዋል::

ግለሰቡ ‘ፍየሎቼ ተወስደውብኛል’ በማለት ለፖሊስ አቤቱታ ቢያቀርቡም ‘ከአረና አባልነትህ መውጣት አለብህ ካልሆነ ፍየሎቹ አይሰጡህም’ የሚል ምላሽ ከፖሊስ እንደተሰጣቸው አቶ አብርሃ ደስታ ገልጸዋል ።

አቶ ዜናዊ በበኩላቸው ፍየሎቹ እንዲመለሱላቸው ለፖሊስ አቤቱታ ሲያቀርቡ ‘በፌስቡክ ሄደህ እንዳስወራኀው መፍትሄውን እዛው ፈልግ’ እንደተባሉ እና አሁን ላይ ግራ ተጋብተው ያለ መፍትሄ ተቀምጠው እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደምም የአንድ የአረና ፓርቲ አባል ንብረት የሆኑ ሁለት ላሞች በጥይት መገደላቸውን ያስታወሱት አብርሃ ደስታ ክብሮም የተባለ የፓርቲው አባል፤ ንብረቱ የሆኑ የቤት እንስሳቶች ተወስደው ታስረውበት እንደነበረ እና  ሕወሓት በድርጅታቸው አባሎች ላይ የሚፈጽመውን በደል አያይዘው ገልጸዋል::

ለድርጊቱ የህወሃት አመራሮችን ተጠያቂ የሚያደርጉት አቶ አብረሃ፤ “ውሳኔው ከሕወሓት እንደሚመጣ እናውቃለን” ይላሉ። አቶ አብረሃ በአከባቢው አመራሮች ላይ ክስ እንደሚመሰርቱ ጨምረው ረዳት ኢንስፔክተር ፍሰሃ አብረሃ የቆላ ተንቤን ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ በቢቢሲ በኩል ለቀረበላቸው ጥያቄ”በአካል ካልመጣችሁ መነጋገር አንችልም” በማለት መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

LEAVE A REPLY