ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አማኞችን የመከፋፈል ዓላማን መሠረት ባደረገ መልኩ የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ የጠራውን መግለጫ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲያስቆም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖስ ጥያቄ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቤተ ክህነት በኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ የተጠራውን መግለጫ እንደማያውቀውና ዕውቅናም እንዳልሰጠው ገልጿል።
የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ርዕሰ ደብር መሀሪ ኃይሉ ዛሬ ቅዱስ ሲኖዶስ በሠጠው መግለጫ ላይ የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ቀሲስ በላይ መኮንን ምንም እንኳ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ትልቅ ሓላፊነት የነበራቸው ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ግን የኦሮሚያ ክልል እንባ ጠባቂ ቢሮ ሓላፊ ሆነው በመሥራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው እየሠሩ ያሉት ነገር ፈጽሞ የማይመለከታቸው መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
የኦሮሚያ ቤተክህነትን የማቋቋም ጥያቄ መምጣት ያለበት ምእመናኑ ተወያይቶበት እንጂ በተወሰኑ ሰዎች ፍላጎት መሆን የለበትም ሲሉም በጉዳዮ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ ክርስቲያን ያላትን አቋም አስታውቀዋል።
የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ በላይ የኦሮሚያ ቤተክህነትን የማቋቋም ጥያቄ ከማንነት እና ከቋንቋ ጋር እንደሚገናኝ እና ኮሚቴው ጥያቄውን ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ መግለጻቸው አይዘነጋም።
አሁን ላይ የኦሮሚያ ሲኖዶስን አቋቁማለሁ የሚሉት ቀሲስ በላይ ቀደም ሲል በአቡነ ጳውሎስ ጊዜም ሆነ በአቡነ ማትያስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ በነበረው የሙስና አሠራር ውስጥ ሰፊ ድርሻ የነበራቸው መሆኑን ያስታወሱ ታማኝ ምንጮቻችን ግለሰቡ የመጡበት መንገድ ጥቅምን መሠረት ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።