ሰሞኑን ሳላቋርጥ OMN የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚያቀርባቸውን ፕሮግራሞች ስከታተል ነበር።
እውነቱን ለመናገር የኦሮሞ ትግል በየቀኑ የማያልቅ ጥያቄ የሚፈለፍል፣ ጥያቄዎቹ ደግሞ መልሳቸው ራሱ ጥያቄ የሆነ፣ ከዶሮና እንቁላል ማን ቀድሞ ተፈጠረ አይነት አዙሪት ነው።
ይባስ ብሎ ያልተገራና አደገኛ እንድምታ ያለው ንግግር፣ ፍጹም ላብሮነት የማይጠቅም፣ ስሜታዊና ጦር አውርድ ነው።
ጋዜጠኞቹ ደግሞ ቃለመጠይቅ የሚያደርጉትን ሰው ካሜራ ፊት መልሱን እየነገሩት ነው የሚጠይቁት።
ጠያቂ <<ያው እንደሚታወቀው ፊንፊኔ የኦሮሞ ናት . . . እና እርስዎ ፊንፊኔ የማናት ይላሉ ?>>
<<ፊንፊኔ እ. . . የኦሮሞ ናት>> ይላል መላሹ!
<<ቀደምት ከተማዋን ቆርቋሪ የነበሩ ኦሮሞች መሬታቸውን እየተቀሙ ቀስ በቀስ ከከተማዋ ወጥተዋል እርሰዎ ቀደምት የከተማዋ ነዋሪ ኦሮሞዎች የት ሄዱ ይላሉ?>>
<< እ. . . ቀደምት የከተማዋ ነዋሪ ኦሮሞዎች ያው መሬታቸውን እየተቀሙ ቀስ በቀስ ከከተማዋ ወጥተዋል>>
እናተ እንዳላችሁት ይሁን ብሎ መንግስትም ሌላውም ህዝብም ስራውንም ኑሮውንም ትቶ የኦሮሞ ታጋዮች የሚጠይቁትን ጥያቄ ብቻ ቢመልስ ራሱ በቃ ጥያቄው አያልቅም።
በራሳችን መሬት በራሳችን ምርት ራሳችን ተጠቃሚ መሆናችን ይረጋገጥ ? እሺ ! በቋንቋችን እንናገር ? እሽ ተናገሩ ! በቋንቋችን የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ እሺ ይከፈቱ ! አዲስ አበባም ላይ ይከፈቱ? እሺ ይከፈቱ ! ከኦሮሞ አርሶ አደሮች የተወሰዱ መሬቶች ይመለሱ?
እሺ ከነተሰራባቸው ህንጻ ከነተሰራባቸው መንገድ ከነተሰራባቸው ፋብሪካ ውሰዱ ! በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉት ከተሞች የኦሮሚያ ናቸው ? እሺ ናቸው ! አዲስ አበባ ፊንፊኔ ትባል ? እሺ ትባል! አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ናት ? እሺ ናት! ስሟ ፊንፊኔ ይሁን ? እሺ ይሁን! ከከተማዋ ልዩ ጥቅም ይገባናል? እሺ ተጠቀሙ ! እንደውም ፊንፊኔ ሙሉዋን የኛ ናት? እሺ ናት! ከሚሴም የኛ ናት? እሺ ናት! ወረኢሉ ወረ ባቦ ፣ ወረሂማኖ የኛ ናቸው? እሺ ናቸው ! ወሎ ኦሮሞ ነው ? እሺ ውሰዱ!
ከዛስ ? ሚኒሊክ በድሎናል? እሺ በድሏችኋል! የኢትዮጲያ ባንዲራ አይወክለንም ? እሺ የፈለጋችሁትን ባንዲራ ተጠቀሙ! ሚኒሊክ ለሰራብን ግፍ ሐውልት እናቆማለን? እሺ አቁሙ! እሱ የሰራው ግፍ ቢያልፍም በዛ ሜንታሊቲ ዛሬም ኦሮሞ ላይ የሌለ ታሪክ ሊጭኑ የሚሞክሩ ሙህራን ይቅርታ ይጠይቁ ?
እሺ ይጠይቁ ! የሚኒሊክ ሐውልት ይፍረስ ? እሽ ይፍረስ ! የኢትዮጲያ ታሪክ ኦሮሞን የማያከብር የማያካትት ነው መጽሐፎች ተሰብስበው ይወገዱ ሁሉም የሚስማማበት ታሪክ እንደገና ይጻፍ ? እሺ ይጻፍ! በሚኒሊክ ስም የተሰየሙ ማህበራዊ ተቋሞች ስማቸው ይቀየር ? እሺ ይቀየር ! የሃይማኖት መጽሓፍት ሳይቀር ለነፍጠኛው ስርዓት የሚያጎበድዱ ስለሆኑ ይስተካከሉ ? እሺ ይስተካከሉ. . . . .
የት ነው መጨረሻው?
አብሮ ለመኖር ወደፊትም ወደኋላም ላለው ድንበር ማስቀመጥ ግድ ይላልኮ !
እንኳን መልሱ ጥያቄውም ከመብዛቱ አንጻር ማስታወስ ከበደን!
እስቲ ቅልብጭ አድርጎ አምስትም ይሁኑ አስር ሌላውንም ኢትዮጲያዊ ያማከለመልስ ያላቸው መሰረታዊ ጥያቄዎችን የሚያስቀምጥልን የኦሮሞ አክቲቪስት ካለ ይሄው ያስረዳን!
አሁን ባለው ሁኔታ የኦሮሞ ታጋዮች ቅልብጭ ያለ ጥያቄ ምንድነው?
ከተስማማን አብረን ታግለን አገር እንገንባ።
ካልተስማማን አለመስማማታችንን በመከባበርና በትክክል ጥያቄውን በመረዳት እናስቀምጥ ዘንድ ጥያቂያችሁን በስርዓት አስረዱን?