የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም

ወንጂ ስኳር ፋብሪካን ለመግዛት ተቃርበናል በሚል የሚካሄደወ የአክስዮን ሽያጭ ማጭበርበር ነው ተባለ

ሠሞኑን በተለያዮ ሚዲያዎች ወንጂ እና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት ተቃርቢያለሁ የሚለው ከፍተኛ ቅስቀሳና የአክሲዮን ሽያጭ በስኳር ኮርፖሬሽንም ሆነ በመንግሥት በኩል ምንም ዓይነት ዕውቅና እንደሌላቸው ተነገረ።

የትኞቹንም ፋብሪካዎች ለመሸጥ ከማንም ጋር አልተደራደርኩም ያለው ስኳር ኮርፖሬሽን ማስታወቂያ አስነጋሪው አካልም በብሮድካስት እና ጉዳዮ በሚመለከታቸው አካላት ይጠየቃል ብሏል።

ከዚህ በፊት ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ በሥነ ምግባር ጉድለት እና በጡረታ የተሰናበቱ ሰዎችን የሰበሰበው ማስታወቂያ አስነጋሪው አካል ወንጂ ስኳር ፋብሪካን ለመግዛት መቃረቡን እየገለጸ የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወኑ ግልጽ የሆነ የማጭበርበር ተግባር ነው ተብሏል።

መተሐራ ስኳር ፋብሪካን ለመግዛት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን እና ወንጂ ስኳር ፋብሪካን በአስራ አንድ ቢሊዮን ብር ለመግዛት እየተደራደሩ መሆናቸውን በጋዜጦች ላይ የገለጹት አካላት ፈጽሞ እውቅና የላቸውም ያለው ኮርፖሬሽኑ ሕብረተሰቡ ትክክለኛነቱ ባልተረጋገጠ መረጃ ላይ ተመስርቶ አላስፈላጊ ውሳኔዎችን እንዳያሳልፍ መክሯል።

ግለሰቦቹ የስኳር ፋብሪካውን ለመግዛት እየተንቀሳቀስን ነው በማለት እያሠራጬ ያሉትን ማስታወቂያ ተከትሎ ኮርፖሬሽኑ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አነጋግሯቸው የነበረ ቢሆንም እንቅስቃሴው ሊቋረጥ ባለመቻሉ ጉዳዮ ወደ ሕግ እንዲመራ አድርጓል።

ምንም ዓይነት የአክሲዮን ሽያጭ ለማድረግ አልሞከርኩም ያለው ተቋም በስኳር ኮርፖሬሽን ስር ከሚገኙ አስራ ሦስት ፋብሪካዎች ተጨማሪ ወጪ የሚያስወጡ ስድስት ፕሮጀክቶችን በቀጣይ ዓመት ለመሸጥ በማሰቡ በዘርፉ ሰፊ ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ ካምፖኒዎችን ጉዳዮን እያስጠና እንደሚገኝ ሕዝብ ይወቅልኝ ብሏል።

ከ252 ሚሊየን ብር በላይ ያስመዘገቡ ኩባንያዎች የማዕድን ማምረት ፈቃድ ወሰዱ

252 ሚሊየን 543 ሺህ 377 ብር ከ50 ሳንቲም ካፒታል ያስመዘገቡ ኩባንያዎች የማዕድን ምርመራ እና ምርት ፈቃድ መውሰዳቸውን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።  ሚኒስቴሩ ኩባንያዎቹ 7 የማዕድን ምርመራ እና 3 የማዕድን የምርት ፈቃዶች መውሰዳቸው ተገልጿል::

ኩባንያዎቹ ለ281 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሲሆን ለውጭ ምንዛሪ ግኝትም ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ነው የተነገረው: :

ክሪፕቶ ማይኒንግና ኬሜካልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን ኮንታ ልዩ ወረዳ በከፍተኛ ደረጃ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ማምረት እንዲሁምበቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ በአነስተኛ ደረጃ የክሮማይት ማዕድን ማምረት ፈቃድ ተሠጥቶታል::

“ሲዳማ አነስተኛ ወርቅ ቁፋሮና የተለያዩ የተፈጥሮ ማዕድናት ንግድ ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር”ደግሞ በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ቦና ዙሪያ ልዩ ወረዳ በደለል ወርቅ ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ መውሰዱ ተገልጿል።     ዦንግሹን ሲሜንት ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በኦሮሚያ ክልል ላይም ስቶን፣ ቻሊንግ ካውንቲ ዢንቶ ማይኒንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደግሞ በጋምቤላ ክልል ወርቅና ላይም ስቶን የምርመራ ፈቃድ ወስዷል።

በተጨማሪም ሳንሸንግ ቢዩልዲንግ ማቴሪያልስ በጋምቤላ ክልል የደለል ወርቅ፣ በኦሮሚያ ክልል ወርቅና ብረት በሶማሌ ክልል ደግሞ የወርቅና ቤዝ ሜታልስ እንዲሁም፥ ኢትዮጵያን ሎንግዢንግ ስቶን ማቴሪያልስ ማይኒንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአማራ ብሔራዊ ክልል ባዛልት ማዕድን የምርመራ ፈቃድ እንደወሰዱ ተገልጿል::

ኩባንያዎቹ የማዕድን አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን መሰረት ሥራቸውን ለማከናወን እና ተመጣጣኝ ዕውቀት፣ ችሎታና ልምድ ላላቸው ዜጎች ቅድሚያ ራ ዕድል ለመስጠትና ለስራው አስፈላጊ የሆነውን ሥልጠና ለመስጠት ግዴታ የገቡ ሲሆን የሠራተኞቹን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ጤንነትና ደህንነት በማይጎዳ መልኩ የምርት ስራውን ለማከናወንም ውል ፈጽመዋል ሲል ሚኒስቴር መ/ቤቱ ገልጿል::

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የበየነ መረብ ነፃነት ጉባዔን ልታዘጋጅ ነው

የአፍሪካ የበይነ መረብ ነፃነት መድረክ በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ  ታወቀ፡፡ መድረኩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር “የበይነ-መረብ ፖሊሲ ትብብር ለምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ” ጋር በመተባባር ነው የሚያዘጋጀው።

ከመስከረም 12 እስከ 15 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ እንዲከበር የተወሰነው ኢትዮጵያ ለኢንተርኔት ነፃነት መከበር በሰጠችው ልዩ ትኩረት መሆኑም እየተነገረ ነው:: የቴሌኮም ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጓ፣ አስርት ዓመታት ተዘግተው የነበሩ የተለያዩ ድረ ገፆች መለቀቃቸው፣ ጸሐፊያንና የበይነ-መረብ አምደኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች በነፃነት እንዲፅፉ መደረጉ መድረኩ በኢትዮጵያ እንዲከበር ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል::

ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ለመመረጧ ሌላኛው ምክንያት ሲሆንበበይነ-መረብ ፎረሙ መካሄድ የአፍሪካ አገራት የሚስተዋልባቸውን የበይነ መረብ ነፃነት ችግሮች ለመለየትና ለመፍታት ያለሙ ምክረ ሃሳቦችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል::

ጉባኤው ለፖሊሲ አውጭዎች፣ የመንግስት ተወካዮች፣ ብዙሃን መገናኛ ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የተመቻቸ መድረክን በመፍጠር የበይነ መረብ ነፃነት ላይ ያለውን የአፍሪካ ችግር ለመቅረፍ ግብዓት ይገኝበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ገልጿል::

የኢትዮጵያ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮዎች ሊቆጠሩ ነው

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ብርቅዬ የዱር እንስሳት በሆኑት ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮዎች ላይ በመጭው መስከረም ወር ወቅታዊ ቆጠራ እንደሚያካሂድ ገለጸ።

የብሄራዊ ፓርኩ ጽህፈት ቤት እንደሚለው ከሆነ በመጭው መስከረም ወር ላይ ሁለተኛ ዙር ወቅታዊ ቆጠራ የሚካሄደው ብርቅዬ የዱር እንስሳቱ ያሉበትን ሁኔታ አውቆ ክትትል ለማድረግ ነው። የቆጠራ ሥራው በፓርኩ ክልልና አዋሳኝ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች የሚካሄድ ሲሆን፥ ይህም በተጨባጭ መረጃ ተመስርቶ ለጎብኝዎች መረጃ ለመስጠት ያስችላል ተብሏል::

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በፓርኩ ላይ ደርሶ በነበረው የእሳት አደጋ በዱር እንስሳቱ ላይ ጉዳት መድረሱንና አለመድረሱን በተጨባጭ ለማረጋገጥ ቆጠራው ትልቅ እገዛ ይኖረዋል::

የዱር እንስሳቱን የውልደትና የሞት መጠን፣ የአመጋጋብ፣ የመኖሪያ አካባቢና ስርጭትን ለማወቅ እንዲሁም የሚደርሱ አደጋዎችን በመለየት ለቀጣይ ግብዓት ለመሰብሰብ ቆጠራ ማካሄዱ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆመው ጽ/ቤቱ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችሉ ከ130 በላይ የቆጠራ ቦታዎች ልየታ መዘጋጀቱን ገልጿል:: ለቆጠራ ሥራው በዘርፉ ልምድ ያላቸው 150 ግለሰቦች መመልመላቸውንና ቆጠራውን በትክክል ማካሄድ እንዲችሉም ስልጠና ተሰጥቷል::

በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ ኢትዮጵያና ኬንያ በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ

 ኢትዮጵያ እና ኬንያ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረማቸው ተገለጸ:: የአገራቱን  ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ነው በዛሬው ዕለት ዕውን ያደረጉት።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ  ፕሬዝዳንት አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ ከኬንያው አቻቻው ጋር ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅትሽብርተኝነትን፣ ሙስናን እና በሙስና ሀብትን የማሸሽ ወንጀልን በጋራ መከላከል እንደሚገባ እና የኬንያ መንግስትም በዚህ ረገድ ያለውን ልምድ እና እውቀት በማጋራት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል::

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የኢትዮጵያ ዜጎችን ለከፋ ጉዳት እየዳረጉ መሆኑንም ያስታወሱትጠቅላይ አቃቤ ህጉ ፤ በሁለቱ አገራት ወሰን በኩል አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ እና ሌሎች አገራት ለመሻገር በሚሞክሩበት ወቅት ለጉዳት የሚዳረጉ ዜጎችን በማስረጃነትገልጸዋል። አንስተዋል::

የኬንያው አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ኑረዲን መሀመድ ሃጂ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት በታሪኳ የተለየች መሆኗን ፣ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች እየተደረገ ያለውን ለውጥም አድንቀው፤ ኢትዮጵያ በሙስና ላይ ያላትን ቁርጠኛ አቋም አገራቸው እንደምትደግፍ እና ለለውጥ ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኬንያው አቻቸው ጋር በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ በጋራ ለመስራት መነጋገራቸው አይዘነጋም።

ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን በተመለከተ የተሠራው አዲስ ፊልም ትችት በዝቶበታል

ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን ከአገራቸው አውጥቶ ወደ እስራኤል ለመውሰድ የተጀረገውን ጥረት በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ እንደተሠራ የሚነገርለት ፊልም ከወዲሁ ከፍተኛ ትችት እየቀረበበት ይገኛል::

በቅርቡ ኔትፍሊክስ ላይ ለእይታ ያበቃው ‘ዘ ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት’ ፊልም መግቢያ የተቀነጨበው እንደሚያሳየው ከሆነ በ1970ዎቹ ሞሳድ ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለመውሰድ የነበረውን አደገኛና መስዋእት የተሞላበት ተልዕኮ ይተርካል::

“ኦፐሬሽን ብራዘርስ  “በተሰኘው በዚህ ሚስጥራዊ ተልዕኮ ሞሳድ ሃሳዊውን ‘አሮስ’ ሪዞርት ከሱዳን መንግሥት በሊዝ ይገዛል። ሪዞርቱን ለስለላ ሥራው እንደ ሽፋን በመጠቀም ቤተ እስራኤላውያንን በመርከብ ነዳጅ አስመስሎ በማውጣት በሲናይ በረሃ በኩል በጀልባ ለማስገባት የተደረገ ግዳጅ መሆኑም ተጠቁሟል::

በእስራኤላዊው ጌዴዮን ራፍ ደራሲና ዳይሬክተርነት የተዘጋጀው ፊልም ላይ የቤተ እስራኤላውያንን እንቅስቃሴ ሲያስተባብር የነበረው ፈረደ አክሎም በአፍሪካአሜሪካዊው ሚካኤል ኬኔዝ ዊልያምስ “ከበደ ቢምሮ”በሚል ገፀ ባህርይ ሲወከል፤ ሌላኛው አፍሪካ አሜሪካዊ ክሪስ እና ቾክ የተባሉ ግለሰቦችም ቤተ እስራኤላውያንን ወክለው ተውነዋል። ኢትዮጵያን ለማስመሰል በናሚቢያ የተቀረፀው ፊልምና በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖች (ቤተ እስራኤላውያኖችን) ለመውሰድ በተደረገው ትግል የኢትዮጵያውያን ቁጥር አስር በማይሞሉ ሰዎች ለማሳየት ተሞክሯል:: በፊልሙ መክፈቻ ላይ ኢትዮጵያ የሚል ጽሁፍ ከመኖሩ ውጪ የጦር አውድማ ተመስላ የቀረበችውም መንደር የት አካባቢ የት እንደሆነች መገመት በጣም ከባድ ነው።

በዚህ አነጋጋሪ ፊልም ላይ አማፂያን ተብለው እርስ በርስ የሚዋጉትም ሆነ፣ ወታደሮቹ እነማን እንደሆኑ ምንም አይነት ፍንጭ የማይሰጥ በመሆኑ ፊልሙን የተመለከቱት ኢትዮጵያውያን ግራ መጋባታቸው በስፋት እየተነገረ ነው::

በተለይም ፊልሙ መጀመሪያ ላይ ደም የጠማቸው አውሬዎች ተደርገው የተሳሉት ወታደሮች ከአለባበሳቸው ጀምሮ ፤ የሚጠቀሙት አማርኛ ኮልታፋ መሆኑ ኢትዮጵያ በወቅቱ የነበሯት ወታደሮች ምን አይነት ናቸው? የሚል ጥያቄንትችቶችንም በማስተናገድ ላይ ይገኛል::

የርስ በርስ ጦርነት እንደነበር ዋነኛው ገፀ ባህርይ በፊልሙ ላይ ከሚተርከው ውጭ ምንም የሚያሳይ ነገር የሌለ ሲሆን ቤተ እስራኤላውያን ከኢትዮጵያ ወታደሮች ለማምለጥ የነበረውን ሞት ቀረሽ ትንቅንቅና በየቦታው ወታደሮች ባዩዋቸው ቁጥር አፈሙዝ መደቀናቸወ በሰዓቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በቤተ እስራኤላውያን ላይ ጦርነት አውጆ ይጠናቀቃል።

 2፡05 ርዝማኔ ባለው ፊልም ላይ የሞሳድ ጀብደኝነትና፣ የሲአይኤ ሚናን በከፍተኛ ሁኔታ በማጉላት ፊልሙ የሚጠናቀቅ ፤በፊልሙ ላይ ቤተ እስራኤላውያን ተብለው የተሳሉት ስደተኞች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የሚናገሩት ቃላቶች የተመጠኑ፤ አካባቢውን ቢያውቁትም የሚመሩት በነጮቹ እንዲሁም እንደሆነና ባህላቸው፣ አለባበሳቸው፣ ፍቅራቸው ምንም አይነት መስተጋብራቸው አይታይም።

ሎዛ አበራ በአውሮፓ የምትጫወት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሆነች

ኢትዮጵያዊቷ ሎዛ አበራ በአውሮፓ የምትጫወት የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጵያዊ እግር ኳስ ተጫዋች መመሆኗታወቀ::ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ሴቶች ሊግ ጎልታ መውጣት የቻለችው ለውዛ  ብቃቷን የምትፈትሽበት አዲስ ዕድል እንዳገኘች ነው እየተነገረ ያለው::

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዱራሜ ተብሎ በሚጠራው ዞን ተወልዳ ያደገችው ሎዛ የእግር ኳስ ሕይወቷን አሁን ላይ መቀመጫውን መቀሌ ያደረገው የደደቢት ሴቶች ቡድንን ከተቀላቀለች በኋላ በርካታ ውጤቶችን ለማስመዝገብቸ  ችላላች::

ባለፈው ዓመት የክረምት ወር ወደ ሌላ አውሮፓ በማቅናት ያደረገችው የሙከራ ዕድል ሳይሳካ ቢቀርም ከሁለት ሳምንት በፊት በማናጀሯ በኩል ለሌላ ሙከራ ወደ ማልታ የተጓዘችው ሎዛ አበራ የተሳካ ጊዜ አሳልፋለች::

ፈተናዋን በብቃት ያለፈችው ሎዛ ለማልታው ቢርኮራኪራ ክለብ ለመጫወትም ፊርማዋን አኑራለች:: የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) ወሳኝ አጥቂ የሆነችው ሎዛ አበራ ስምምነቱን ለምን ያህል ዓመት እንደፈረመች እና ምን ያህል ገንዘብ እንደሚከፈላት ግን እስካሁን ይፋ አልተደረገም::

LEAVE A REPLY