የደም ባንክ በየብሔራችን እናቋቁም እንዳይሉን… || ሙሸ ሰሙ

የደም ባንክ በየብሔራችን እናቋቁም እንዳይሉን… || ሙሸ ሰሙ

ኢህአዴጋውያን ከአጃቢዎቻቸው ጋር ሆነው ገና ከጅምሩ ሲምሉበትና ሲገዘቱበት የነበረውን ኢትዮጵያዊነትን የመበቀል እቅዳቸውን ለማሳካት ከብዙ በጥቂቱና በተለይ ደግሞ ወሳኝ የሚሏቸውን ሶስቱ የኢትዮጵያዊነት የማዕዘን አምዶች አማርኛ ቋንቋ፣ ኦርቶዶክስ ተዋህዶና በአማራነት የሚመስሉትን የአንድነት (የኢትዮጵያዊነት) ጽናትን ማዳከም ማዕከል አድርገው ጥቃታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ገሀድ እየወጣ ነው።

ኢህአዴጎች ለዘመናት የዘለቀውን በበጎም ሆነ በደካማ ጎኑ የሚነሳ የጋራ ታሪክችንን፣ ባህላችንና እምነታችንን ደልዘውና ሰርዘው እነሱ እንደልባቸው የሚናኙበትና የሚወናኙበት ኢትዮጵያዊነት ካልተፈጠረ በስተቀር ከጥፋት እርምጃቸው እንደማይርቁና ምርኮኛ ካደረጋቸው ባህሪም እንደማይመለሱ ግልጽ ሆኗል። የሚለወጥ ነገር ካለም ማሊያቸውና አጫዋቾቻቸው ብቻ መሆኑን ለመረዳት ሰሞኑን የኢትዮጵያዊነት አንዱ አምድ በሆነው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በገሃድ የተከፈተው የመከፋፈል ዘመቻ በቂ ማመሳከርያ ሊሆነን ይገባል።

የጥላቻ ሰራዊት የሰፈረባቸው ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለና በጥላቻ የሰከረ ቡድን ገደብ ሲጥስ ሰማይን ልርገጥ ማለቱ የሚጠበቅ ነው። ትናንት በባንክ የተጀመረው በብሔር ካባ ተሸፍኖ መነገድ፣ ዛሬ ላይ አድጎና ተመንድጎ ከፍተኛ እመርታ በማሳየት አምልኳችሁን በብሔር ማዕቀፍ ካላደራጃችሁ እንጨራረሳለን እየተባለ ነው። መቼስ ለአፍ የመቅለሉን ያህል መጨራረስ የሚለው ዛቻ ተግባር ላይ እንደማይገድ ባየን ኖሮ መልካም ነበር።

ያም ሆነ ይህ ግን እጅግ የሚያስደምመው ጉዳይና ነገ ላይ ብቅ ሊል የሚችለው ቀሪ አጀንዳ በዘር ጥላቻ ተጠርንፈው ቀልባቸውን የሳቱ ግለሰቦችና ቡድኖች ደማችን ለብሔራችን በሚል ፋሽስታዊ ጥላቻ ተቀንብበው የደም ባንክ በየብሔራችን እናቋቁም እንዳይሉን ብቻ ነው።

ዘንድሮ እንደተለመደው በየአጥቢያው ላይ የእገሌ ቤተ መቅደስ እያሉ የራስን የአምልኮ ስርዓት እየዘረጉ ማምለክ መብት ከመሆኑም በላይ እርስ በእርስ መመላለኩ ማንንም እንደማያስቆጣ እየታየ ነው። በተቃራኒው ደግሞ በግልጽ መታወቅ ያለበትና ሁሉም ሊረዳው የሚገባው ጉዳይ የተዋህዶ አምልኮን ከጥላቻ በመነጨ ነባር ሴራ እንዲሁም እቅድ በተዘረጋለት ውስጠ ወይራ ድርጅታዊ ስልት ለመከፋፈልና ለማዳከም መሞከር በእሳት መጫወት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

ማንም ለብሔሩ ቀናኢ የሚሆነውን ያህል፣ ሌላውም ለአምልኮው በእጥፍ ቀናኢ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ማስተዋል ጠቃሚ ነው። ዛሬ በተዋህዶ ላይ የተቀነባበረው ሴራና ፈተናም ነገ ወደ ሙስሊሙና ወደ ሌላው አምልኮ ሊሸጋገር እንደሚችል ከወዲሁ ማሰብና እንደዚህ አይነቱን ሴራ ከወዲሁ በጋራ መታገል ብልህነት ነው።

መብት እስከ አፍንጫ ድረስ ነው ሲባል አፍንጫን እስካልነካ ድረስ ብቻ መሆኑን መገንዘብም ደግ ነው። በሚቀለድበት ሁሉ መቀለድ ይቻላል፣ በሀገርና በሃይማኖት ላይ ግን ለመቀለድ መሞከር ቢገታ ደግሞ ለሁላችንም መጻኣ እድል መልካም ነው።

እስከዛሬ ድረስ የስካር አዙሪትና የጊዚያዊ እብደት አባዜ ውሎ አድሮ በሂደት ይሰክናል በሚል እንጂ ካበዱት ጋር ማበድም ሆነ ከሰከሩት ጋር እኩል መንጀባረር የሚገድ እንዳልሆነ እንገንዘብ።

LEAVE A REPLY