የደቡቡ ሲአን ፓርቲ ለሁለት ተሰነጠቀ
በዚህ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) አመራሮች መካከል በተከሰተው አለመግባባት ፓርቲውን ለሁለት እንደሰነጠቀው እየተነገረ ነው፡፡
የሲአን ሕጋዊ አመራር እኔ ነኝ ያለው በዶ/ር ሚሊዮን ቱማቶ የሚመራው ቡድን፤ በቅርቡ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴን ስብሰባን አካሂዶ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በዱካሌ ለሚሶ የሚመራው ቡድን ደግሞ “የማዕከላዊ ኮሚቴውን ስብሰባ ያካሄዱት አመራሮች በከባድ ሥነ ምግባር ጉድለት ያሰናብተናቸው ግለሰቦች ናቸው” ሲል ወቅሷል፡፡
በፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሐላፊና ዋና ጸሐፊ ለገሰ ላንቃሞ፤ በሚሊዮን ቱማቶ የተመራው ስብሰባ ሕገ ወጥ እንደሆነ ጠቁመው፤ “ፓርቲው 104 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እያሉት 35 ሰዎች ብቻ ተሰባስበው ያደረጉት ጉባኤ የተሟላ ነው ማለት አይቻልም” ብለዋል፡፡
የእነ ሚሊዮን ቡድን በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በተደረገ ምርጫ ተሸንፈው የወጡ መሆናቸውን ያስታወሱት የድርጅት ጉዳይ ሐላፊው፤ በንቅናቄው አንድ ሠው በምርጫ መወዳደር የሚችለው ለሦስት ጊዜ ብቻ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ለአራተኛ ጊዜ መወዳደር የሚፈልጉ ግለሰቦችም ቅሬታ እያቀረቡ እንደሚገኙ ይፋ አድርገዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ፈፅሞ ሊግባቡ ባለመቻላቸው አቤቱታቸውን ለምርጫ ቦርድ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ በወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚተዳደረው ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ ከሁለቱም ቡድኖች የአቤቱታ ማመልከቻ እንደደረሰው አስታውቆ መተዳደሪያ ደንባቸውን መርምሬውሳኔውን አሳውቃለሁ ብሏል፡፡
ጃዋር መሀመድና ሚሚ ስብሓቱ ስልት ቀይረው በ”አዋሽ ኤፍ.ኤም ራድዮ” መጡ
የተለያዩ ውዝግቦችን በማንሳት በሚታወቀው ጃዋር መሐመድ የሚመራው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ.ኤም.ኤን) ከቀድሞው ዛሚ ኤፍ.ኤም 90.7 ራዲዮ (ከአሁኑ አዋሽ ኤፍ ኤም) ጋር ለጊዜው የአየር ሰዓት በመግዛት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ ድርሻ ለመግዛት አብሮ ለመስራት ከስምምነት ላይ ደረሰ፡፡
የሚሚ ስብሓቱ ዛሚ ራዲዮ ጣቢያ፤ ከስያሜ ለውጥ ባሻገር የአስተዳር ለውጥም ተደርጎበታል፡፡ መስከረም ወር ላይ ኦ.ኤም.ኤን በገዛው የአየር ሰዓት ስርጭት እንደሚጀምርምተረጋግጧል፡፡ ኦ .ኤም.ኤን ከአንድ ዓመት በፊት የራድዮ ጣቢያ ለመክፈት ለብሮድካስት ባለሥልጣን ያቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ባለማግኘቱ ከዛሚ ኤፍ.ኤም ጋር ለመሥራት እንደወሰነም ሰምተናል፡፡
አስቀድሞ ለታሰበው የራድዮ ጣቢያ ሙሉ ዕቃ ከውጭ አገር የገባ በመሆኑ፣ እነዚህ ዕቃዎች በአዳማ ከተማ አዲስ ራዲዮ ጣቢያ በማቋቋም ስርጭቱን በኦሮምኛ ቋንቋ ለማድረስ ጃዋር መሐመድ ማቀዱን የጠቆሙ ምንጮቻችን፤ “አዋሽ”የተሰኘው የቀድሞው ዛሚ ራዲዮ ግን ሙሉ ለሙሉ በአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራሞችን እንደሚያስተላልፍ፣ ምናልባት ለአንድ ሰዓት የኦሮምኛ ቋንቋ ፕሮግራም ሊኖረው እንደሚችል ነግረውናል፡፡
ባለፈው ግንቦት 26/2010 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት፤ የናሁ ቴሌቪዥን እናት ድርጅት በሆነው በጎልደን ኮፊ ሮስተሪ አመልካችነት፣ በዛሚ ኤፍ.ኤም ሬድዮ ላይ በቀረበው ክስ መነሻ፤ በድርጅቱ ስም የተመዘገቡ ሁለት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ድርጅቱ እንዳይሸጥና እንዳይለወጥ ዕግድ መውጣቱ አይዘነጋም፡፡
ተስፋ የተጣለበት ለውጥ በአፍጢሙ እንደተደፋ፣ ስንታየሁ ቸኮል ከእስር ቤት ገለጸ
ላለፉት 20 ዓመታት በሰላማዊ መንገድ አምባገነኑን ሥርዓት በመታገል የሚታወቀው እና ቀደም ሲል ለአስር ጊዜያት ያህል ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እስከ ሸዋሮቢት እና ዝዋይ ያሉ ማጎሪያዎች ውስጥ ለእስር የተደረገው ስንታየሁ ቸኮል፤“ኢትዮጵያ በክፉ ቀን የሚደርስላት አታጣም” ሲል ከዕስር ቤት ለኢትዮጵያውያን መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
አዲስ አበባ በተለምዶ ቄራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዶ ያደገው ስንታየሁ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚሠራው የባልደራስ ባለአደራ ም/ቤት መሥራችና የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእስክንድር ነጋ የሚመራው ባላደራው ሰኔ 16 ቀን በባህርዳር ከተማ ሊያካሂድ የነበረውን ሕዝባዊ ውይይት ለማዘጋጀትና አንዳንድ ሁኔታዎችም ለማመቻት ቀደም ብሎ የሄደው ወጣቱ የነፃነት ታጋይ ስንታየሁ ቸኮል፤ ሰኔ 15 ቀን በባህርዳር በተፈፀመው ግድያ ላይ እጅህ አለበት ተብሎ አዲስ አበባ ላይ ተይዞ ከታሠረ ሁለት ወራት አልፈውታል፡፡
ዛሬ ላይ በሽብርተኝነት ተከስሶ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስር ቤት ውስጥ የሚገኘው ስንታየሁ፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ከከተማዋ የፖሊስ ሹማምንት እስከ ከንቲባው ድረስ ጥርስ እንዳስነከሰበት የቅርብ የትግል አጋሮቹ ይናገራሉ፡፡ የቲም ለማ ቡድን የሕወሓት የበላይነትን ገርስሶ ስልጣኑን ሲቆጣጠር፤ አጥፊው ቡድን በተለያዩ መንገዶች የሚፈፅማቸውን የሠላም ማደፍረስ ተግባሮች በማውገዝ፣ የሰኔ 16ቱን ሠልፍ ካዘጋጁት ስድስት አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው፡፡
የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍን ለማዘጋጀት ሀሳቡን ከማመንጨት እስከ ማዘጋጀት ትልቅ ሥራ ያከናወነው ስንታየሁ ቸኮል፤ የሄደበት መንገድ ያልተዋጠላቸው ሰዎች ዛሬ ላይ ለእስር እንደዳረጉት ለባልደረባችን ገልጾለታል፡፡ “ጠ/ሚ/ሩ የገቡትን ቃል አጥፈው፣ ይቅርታ የጠየቁበትን የሕወሓት መንገድ ለመድገም የሄዱበት መንገድ አገራችንን በእጅጉ የከፋ አደጋ ላይ ጥሏታል፡፡ ቲም ለማ ለስልጣን መወጣጫ የተጠቀመበት “የኢትዮጵያውነት ሱስ ነው” መፈክር በዘረኝነት የተጨማለቀ ከሆነ፣ የአገሪቱን አንድነት ከስጋት ላይ ይወድቃል”ያለው አሁን በእስር ላይ የሚገኘው ስንታየሁ ቸኮል፤ “የኦዴፓ አካሄድ ከኦነግም በላይ የኦሮሞ ህዝብ አፍቃሪ ሆኖ ለመታየት፣ራሱንም አገሪቱንም ይዞ በፍጥነት ወደ ገደል እየተምዘገዘገ እንደሆነ ያሳያልም” ብሏል፡፡
ተስፋ የተጣለበት ለውጥ በአፍጢሙ ሲደፋ እያየን ነው በማለት የሚናገረው ስንታየሁ፤ እንደወትሮው ሁሉ ይህቺ አገር በክፉ ቀን የሚደርስላትን አታጣም ሲል ዕምነትና ተስፋውን ገልፆልናል፡፡ ወጣቱ ፖለቲከኛ አሁን በታሰረበት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዕስር ቤት ውስጥ የባለ አደራው አመራርናአባላት፣ የአሥራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች፣ የአብን አመራርና አባላት፣ የአማራ ክልል ሚሊሺያና ልዩ ሀይል አሠልጣኞች እና የሠብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ 108 ሰዎች በዕሥር ላይ እንደሚገኙም ነግሮናል፡፡
የሕሊና ዕስረኞቹ በሙሉ በምርመራ ወቅት የሚጠየቁት ከሰኔ 15 መፈንቅለ መንግሥት ጋር የተያያዘ ሳይሆን “ለምን አብን ሆናችሁ?” እንዴት ባአደራውን ትደግፋላችሁ?” ኦዴፓን ለምን ጠላችሁ? የሚሉ ተራ አሉባልታዎች በተደጋጋሚ እየቀረቡላቸው የማስፈራራት ተግባርን ለመፈፀም እንደሚሞከር ጭምር ከህሊና ዕስረኛው ስንታየሁ ቸኮል መረዳት ችለናል፡፡
በወለጋ ቅዳሴም ሆነ ስብከት በኦሮምኛ ቋንቋ ሲካሄድ መኖሩን ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መሰከሩ
በኦሮምያ ክልል በወለጋ ያለችውን ቅድስት ቤተክርስቲያንን የመሩት እና ሰሞነኛው የኦሮሚያ ቤተክህነትን እናቋቁማለን የሚለው ጥያቄ በቀጥታ የሚመለከታቸው ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ እርሳቸው በሚመሩት የኦሮሚያ አገረ ስበከት ዝማሬ፣ ቅዳሴና ስብከቱ ሁሉንም ባማከለ መልኩ በኦሮምኛ፣ በአማርኛ እና በግዕዝ ቋንቋ ሲሰጥ መቆየቱን ገለጹ።
አሁን እየተነሳ ያለው የቋንቋ ጥያቄን መሰረት ያደረገው የኦሮሚያን ሲኖዶስ የማቋቋም ጉዳይ ፈጽሞ እንዳልገባቸው የገለጹት አቡነ ናትናኤል፤ ”እኔ እራሴ በክልሉ አገልግሎቱ በስፋት እንዲሰጥ ካለኝ ፍላጎት እና ጉጉት የተነሳ በመንበረ ጵጵስናዬ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮምኛ ቀድሼ፣ አቁርቤ፣ ሰብኬ ጀምሬ ያስጀመርኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በቢሮ ሥራም ደብዳቤዎች በኦሮምኛ ሲመጡ የምናስተናግደውም ሆነ የምንመራው በኦሮምኛ ነው፡፡ እኔም በኦሮምኛ የመጣን ደብዳቤ ስመራ በኦሮምኛ ነው።
ይህ አጀንዳ አስፈላጊ ነው ተብሎ ቢታመንበት እንኳን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን አጥንቶ እና መርምሮ ለቤተክርስቲያኗ የሚጠቅመውን ውሳኔ ሊያሳልፍ ይገባል፡፡ ጥያቄ አቅራቢዎቹም የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በትዕግስት መጠበቅ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ መከበር ያላቸውን ክርስቲያናዊ ግዴታ መወጣት ሲገባቸው ይህ ባልሆነበት ሁኔታ እንደው ብድግ ብሎ ቤተክርስቲያኗን የሚከፋፍል ሃሳብ ማራመድ እና ማጮህ ለምን እንደተፈለገ ሊገባኝ አልቻለም፡፡” ሲሉ በሆነው ሁሉ ማዘናቸውን አስታውቀዋል፡፡
እንዴት አድርገን መንፈሳዊ አገልግሎቱን በኦሮምኛ ቋንቋ እናስፋፋው? እንዴትስ አድርገን ተደራሽ እንሁን? ብሎ የተሻለ ሃሳብ ይዞ ቀርቦ በውይይት የተሻለ ሥራ መስራት ይቻላል ያሉት እኚህ የሐይማኖት አባት፤ “ቅዱሳን አበው ያስረከቡንን አሃቲ ቤተክርስቲያን በብሄር የምንከፋፍል ከሆን የአባቶች አፅም ይፋረደናል። ይወጋናልም። ስለሆነም እኔ ለልጆቼ ሁሉ የምመክረው ተረጋግተው ጉዳዩን እንዲያጤኑት እና ለቤተክርስቲያናቸው እንዲታዘዙ ነው “ በማለት ምክር ለግሰዋል፡፡
በየትኛውም ቋንቋ ሰብከን ነፍሳትን ወደ መንግስተ እግዚአብሔር ማስገባት እንጂ አንዱን ከፍ፣ አንዱን ዝቅ አድርገን በሰዎች መካከል ጥላቻን እና መከፋፈልን መፍጠር አይገባም ያሉት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል
“እኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአንድ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የማምን እና የምመራ መሆኔን ላሳውቅ እወዳለሁ፡፡ አስፈላጊ በሆነው እና ጠቃሚ በሆነው ማንኛውም ነገር የቤተክርስቲያንን አንድነት በጠበቀ መልኩ ልናደርገው እንችላለን ከዛ ባለፈ ግን እራስን እንደ ሌላ ተቋም በማየት እና ከቃለ ዓዋዲው ውጪ መንቀሳቀስ ከበድ ያለ መንፈሳዊ ቅጣት ያስከትላል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚመጣ ካለም እስከ ህይወቴ ፍጻሜ ስለቤተክርስቲያኔ አንድነት እየመሰከርኩ እና እያስተማርኩ እሰዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ከአባቶቼ የተቀበልኩት አደራ እና ሓለፊነት ስለሆነ” በማለት ሕዘበ ክርስቲያኑ ለአንዲት ቤተክርስቲያን ሕልውና መታገል እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ታከለ ኡማ በኮፐንሀገን ዓለም አቀፉ የከንቲባዎች ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ
ም/ ከንቲባ ታከለ ኡማ በዴንማርክ ኮፐንሀገን በሚደረገው የሲ-40 ዓለም አቀፉ የከንቲባዎች ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ መጋበዛቸው ተነገረ፡፡ ለከንቲባው ግብዣው የቀረበላቸው በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ካሪን ፖልሰን ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ነው ተብሏል፡፡
የሲ-40 ዓለም አቀፉ ከንቲባዎች ጉባኤ ዋነኛ ትኩረቱን የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ጥበቃ ላይ በማድረግ ከጥቅምት 17 እስከ 20 2012 ዓ.ም በኮፐንሀገን ይካሄዳል። በጉባኤው ላይ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በአዲስ አበባ እየተሰሩ ባሉ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ሥራዎች ዙሪያ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመዲናዋ የወንዝ ዳርቻዎች የሚለሙበት ግዙፉ ሸገርን የማልማት ፕሮጀክት ዙሪያ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ የሚል ግምትም ከወዲሁ ተሰንዝሯል፡፡ ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በክርስቲያንስበርግ ቤተመንግስት ከዴንማርክ የንጉሳውያን ቤተሰቦች ጋር ቆይታ ይኖራቸዋል፡፡
ሕዝብ የተማረረበትን የዋጋ ንረት ለመፍታት እየሠራ መሆኑን መንግሥት ገለጸ
በፍጆታ ዕቃዎች እና በአገልግሎት ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመፍታት መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር ተናግረዋል።
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በፍጆታ እቃዎች እና በአገልግሎት ላይ በሚስተዋለው የዋጋ ንረት ዙሪያ ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር እየተወያየ ነው በማለትም ሐላፊዋ ሕዝብ የተሰላቸበትን እና ላለፉት 27 ዓመታት ሲሰማው የኖረውን ደካማ ሰበብ እንደመፍትሄ አቅርበዋል።
የዋጋ ንረት በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን የጠቆሙት ወ/ሮ ፈትለወርቅ (ሞንጆሪኖ)፤ በገበያ ላይ የሚስተዋለው ዕጥረት የተከሰተው ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ለዋጋ ንረቱ ምክንያት በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ በግብይት ሰንሰለቱ ላይ የተሰማሩ ደላሎችም የምርቶች ዋጋ አላግባብ እንዲያሻቅብ በማድረግ ችግሩን እንዳባባሱት አስታውቀዋል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለውን የዋጋ ንረት ለመፍታትም የዘርፉ ባለድርሻዎች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ከመገለጹ ባሻገር መንግሥት በአስቸኳይ የኑሮ ውድነቱን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ተብሏል፡፡ በውይይቱ ላይ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ አስመጪዎች፣ አከፋፋዮች እና የፌደራል፣ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል የዘርፉ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይልን አስቆማለሁ ሲል ኦዴፓ ቃል ገባ
በቀጣዩ ዓመት (2012) በኦሮሚ ክልል ውስጥ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ አካል እንዳይኖር አደርጋለሁ ሲል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት (ኦዴፓ) አስታወቀ። ከመንግሥት ውጪ በሕገ-ወጥ መንገድ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀስ አካል እንዳይኖር ይደረጋልም ተብሏል፡፡
የክልሉ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ አድማሱ ዳምጠው ክልሉን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ እና የክልሉ መንግሥት በመጪው አዲስ የሥራ ዘመን ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩባቸው ቁልፍ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጠኞችን ሰብስበው ዛሬ መግለጫ በሰጡበት ጊዜ መንግስታቸው ዕቅዱን እውን ለማድረግ እንደሚሰራ በርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
ቁጥራቸው እና የታጠቁት መሳሪያ በውል የማይታወቅ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ኃይሎች በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። ኦነግ ታጣቂ ኃይሎቹን እንደማያውቃቸው ያሳወቀ ሲሆን፤ ታጣቂዎቹም ከፓርቲው ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው ኃይል የጦር መሪ የሆነው ኩምሳ ዲሪባ ወይም መሮ፤ በምዕራቡ ክፍል የሚገኘው ኃይል የትጥቅ ትግል ማድረጉን እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ ሲገልጽ፤ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው ኦነግ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ የጦር ኃይል አይኖረውም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ይሁን እንጂ አቶ አድማሱ በመጪው ዓመት ሰላምን እና ጸጥታን ማስከበር ዋነኛው የመንግሥት ትኩረት መሆኑን የመሰከሩት፡፡ “ሕግ የሚተላለፍ አካልን ለሕግ እናቀርባለን። ኦሮሚያ ሕግን ተላልፎ መኖር የማይቻልበት ክልል መሆኑን በመጪው ዓመት እናስመሰክራለን።” ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በክልሉ ውስጥ ለዕስር እየተዳረጉ መሆኑን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከዚህ በፊት ሲከናወኑ የቆዩት ሕግን የማስከበር ሥራዎች እንደሆኑ ጠቁመው፤ በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ክልሉን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ ፍላጎት አለው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እና ያለ ጸጥታ ችግር እንዲካሄድ ተገቢው ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል፡፡