ሰሞኑን የበርካታ ሰላም ወዳድ ኢትዬጵያኖችን ልቦችን ክፉኛ ከጉዱት ክስተቶች መካከል በዋንኛነት የሚጠቀሰው በኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤት ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና እራሳቸውን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ብለው በሚጠሩ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ተቃርኖን ለመሸምገል ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ።
የጠ/ሚ/ሩ ጽ/ቤት የፕሬስ ክፍል ሹም የሆኑት ብሌኒ ስዩም ሰኞ እለት ከአሜሪካ ራዲዬ የአማሪኛው ክፍለ ጊዜ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ ጠ/ሚ/ሩ የወቅቱን የቤተክርስቲያኒቷን እና የምእመናኖቿን ስጋቶች እና ጭንቀቶችን ያበርዱ እንደ ሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ” ከሁለት ጎራ ተከፋፍለው የቆዩት ቅዱስ ሲኖዶስችን አንድ በማድረጉ ጥረት ላይ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ ምንም እንኳን ሰሞኑን በደ/ኮሪያ፣በጃፓን እና በእስራኤል በስራ ጉብኝት ላይ ቢቆይም ሰሞኑን ስለተፈጠረው ችግርን በተመለከተ ያውቁታል(ገለጻ ይደረግላቸዋልም) ፣ ለተፈጠረው ችግር የዶ/ር አብይ ጣልቃ ገብነታቸው ያስፈልጋል ከተባለ ፣ በማንኛውም ሰዓት ፣በማንኛውም ቦታ ፣በማንኛውም ቡድን ጥሪ ከተደረገላቸው ጠ/ሚ/ሩ ዝግጁ ናቸው”በማለት ብሌኒ ስዩም አረጋግጠዋል።
ብሌኒ ስዩም ይህን ይበሉ እንጂ የኢ/ኦ/ተቤ/ክን ሰሞኑን ላወጣቸው ኦፊሲላዊ ተቃውሞ እና ሀገር አቀፍ የድረሱልን ጥሪ የጠ/ሚ/ር ጽህፈት ቤትን በቀጥታ ስለመመልከቱ ፣ ያለመመልከቱ ወይም ልዩ የግብዥ ጥሪ በግላቸው መላክ እንዳለበት ምንም ያሉት ነገር የለም።
ለሰሞነኛው የቤተክርስቲያኒቱ እና ለበርካታ ምእመናኖች ጭንቀት እና ድንጋጤ ዋንኛ ምክንያት የሆነው የኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ የኦሮሚያ ቤተክህነት ጽ/ቤት አስተባባሪዎች ባለፈው እሁድ በአዲስ አባባው የኦሮሚያ የባህል ማእከል ውስጥ ባወጡት ባለ ስድስት ነጥብ መግለጫቸው መካከል ” በአንዲት ቤ/ክን እናምናለን ፣በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣በአንድ ፓትሪያርክ እንመራለን ፣ አላማችን ምድራዊ ፓለቲካን ለመጫን ወይም ቁሳዊ ፍላጎትን ለማሳካት አይደለም ፣ጥያቄያችን የአስተዳደርዊ ጉዳይ ነው ፣ ይህንንም ጥያቄ በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ሆነ ለአቡነ ማቲያስ ጽህፈት ቤት አሳውቀናል፣ ምእመናኖቻችን እየኮበለሉብን ነው፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥያቄዎቻችንን የሚቀበል ከሆነ የሰው ሀይል አመዳደቡን እና አፈጻጸም በተመለከተ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና አደራጅ ኮሚቴው በጋራ የሚወስኑት ይሆናል የሚሉ ነጥቦች ይገኝበታል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲሰጣቸው የአንድ ወር ጊዜ የሰጡት አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ ምላሽ ካላገኙ ግን ለጊዜው በውል ያልተገለጸ እርምጃ እንደሚወስዱ በመግለጫቸው ላይ ተመልክቷል። ከመግለጫው በሁዋላ በተነሱ ጥያቄ ዎች እና መልሶች ላይ የፌደራል መንግስቱ መናገሻ ከተማ የሆነችው የአ/አ ጉዳይም በቀጥታ ይሁን በእጅ አዙር መነሳቱ አልቀረም ።ከአደራጅ ኮሚቴዎቹ መካከል አንዱ “አ/አ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች (ሁለት ጊዜ በመድገም) በአማርኛ ፣በግእዝ፣በትግሪኛ እንደሚቀደስ ሁሉ በክልል ደረጃ ሆነ በአ/አ ውስጥ በኦሮምኛ ቋንቋም እንዲቀደስ እንፈልጋለን፣ እዚህ ላይ ምንም ፍርሀት እና ጭቅጭቅ የለም ” ሲሉ የኮሚቴው አቋምን ገልጸዋል።
ከአደራጅ ኮሚቴዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት ቄሲስ በላይ መኮንን ” ከኢትዬጵይዊነቴ በመጀመሪያ ኦሮሞነቴ እመርጣለሁ /ኦሮሞ ፈርስት” የሚል አመለካከቱን ቀደም ሲል እኤአ 2013 በአልጀዚራ ቴሌቭዥን አማካኝነት መግለጹ በስፋት ከሚታወቀው ፣ የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ ባለቤት እና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆነው አክቲቪስት ጁዋር መሐመድ ጋር ጊዜው እና ቦታው በርግጠኝነት ያልተገለጸበት ነገር ግን በጋራ የተነሱት ማስታወሻ ምስልን ሰሞኑን የተመለከቱ በርካታ ወገኖች “እውን አክቲቪስት ጁዋር መሐመድ ሰሞነኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ወጀብን ይዘውር ይሆን?” የሚሉ ጥያቄዎች እና ጥርጣሬዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ማንሳታቸው አልቀረም።አክቲቪስት ጁዋር ይሁን ቄሲስ በላይ ወይም አስተባባሪው ኮሚቴ በጉዳዩ ዙሪያ እስከ አሁን ድረስ የሰጡት ማስተባበያ ወይም ማረጋገጫ አልታየም።
ባለፈው ሳምንት( ነሐሴ 24 2011ዓም) ለአስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጠው እና በቄሲስ በላይ መኮንን አስተባባሪነት የሚንቀሳቀሰው የኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አደረጃጀት ኮሚቴን እውቅና የነፈገው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን የቅዱስ ሲኖዶስ “እንቅስቃሴው ሆነ መግለጫው ከቤተክርስቲያኒቱ ህግ እና ስርአት ጋር የማይሄድ በመሆኑ አንቀበለውም ፣ መንግስትም ሆነ ምእመናኑ በጽኑ ሊያወግዙት ይገባል” ሲል ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም ።
የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ እና የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሆኑት ብጹ አቡነ ዬሴፍ ሁኔታውን በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ቋሚ ሲኖዶሱ ይህንን መግለጫ ለመስጠት የተገደደው እንቅስቃሴው ቤተክርስቲያናችንን የሚከፋፍል፣ለአገሩቱም ሆነ ለልጆቿ ጠንቅ ስለሆነ እና አካሄዱ ሳይገባቸው የቀሩ ወገኖችም ካሉ ወደ ልቦ ናቸው እንዲመለሱ ታስቦ ነው” ብለዋል።
አቡነ ዬሴፍ የሁኔታውን አሳሳቢነትንም በተመለከተ ሲያብራሩ አግባብነት ላለው የመንግስት አካላት የራሱን ሐላፊነቱን እንዲወጣ በደብዳቤ ይፋ መደረጉን እና ከሰሞነኛው የእነ ቄሲስ በላይ መኮንን እንቅስቃሴ ጀርባም ” የአንድ ሰው ውጥን አይመስልም፣ጠባብ እና አክራሪ አክቲቪስቶች ፣ፓለቲከኞች እና ሌላ ሀይል አለ ብዬ አምናለሁ፣የተያዘው እንቅስቃሴም ቢሆን የእምነት ጉዳይ ሳይሆን የበቀል እርምጃ ይመስላል “በማለት ጥርጣሬያቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም ።
“ኢትዬጵያን ከኦርቶዶክስ ተ/ ቤ/ክን ውጪ ማሰብ ይቻላል?”
ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በሁዋላ በአስተዳደራቸው ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል ለሃያ ስባት አመታት በቅኖና ልዩነት ተለያይተው የነበሩት ሁለቱ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ሲኖዶሶችን ወደ አንድ ሲኖዶስ እንዲመጡ ይደረጉበት ጥረት እና እርቀ ሰላሙንም ባለፈው ሐምሌ 2018 እኤአ በአሜሪካ፣ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ላይ እንዲያከናውኑ የተደረገበት አጋጣሚን ብዙዎች ዛሬ ድረስ በበጎነቱ የወሱታል። ጠ/ሚ/ሩ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ለኢትዬጵያ እንድነት፣ስልጣኔ እና የፍትህ ስርአት መጎልበት ያበረከተችው አስተዋጽኦንም ሲገልጹ” ለኢ/ኦ/ተ/ቤን ልዩ ትኩረት ሳይሰጡ ኢትዬጵያን ማሰብ በጭራሽ አይታሰብም።ቤተክርስቲያኒቱ ቅድስት እና ሀገር ማለት ነች” ማለታቸው ፣ ቤተክርስቲያኒቱ ላበረከትቻቸው ዘርፈ ብዙ ውለታዎች እውቅና መስጠታቸው ፣ ለሁለት አስር አመታት በስደት አለም የነበሩት አራተኛው ቅዱስ ፓትሪያርኳ አቡነ መርቆሪዬስንም አብረዋቸው ወደ አ/አ እንዲመጡ ማድረጋቸው የቤተክርስቲያኒቱን አባቶች ሆነ ምእመናኖቿንእስከ ዛሬ ድረስ በእጅጉ ማስደሰቱ እና በኢትዬጵያ ሰማይ ላይ የሰላም አየር መንፈስ ጀመረልን የሚል ትልቅ ተስፋን እንዲሰንቁ ማድረጉ አይካድም።
ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባለፈው ግንቦት በአመት ሁለቴ የሚያካሄደው ጉባኤውን አ/አ ውስጥ ሲያካሄድ በክብር እንግድነት የተገኙት ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ”ቤተክርስቲያኒቱ ስለ ሰላም፣ስለ ፍቅር፣ በአገር ግንባታ እና በእርቀ ሰላም ጉዳያችም ላይ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የበኩሏን እገዛ እንድታደርግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።እነዚህን እና መሰል ሀይማኖታዊ፣አገራዊ እና ማህበራዊ ራእዬችን እንድታሳካ ሐላፊነቶችን የተቀበለችው ቅድስት ቤ/ክን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ጣልቃ ገብነትን እና ለኢትዬጵያ አንድነትን የሚተጉ ሰላም ወዳዶችን እና የምእመናኖቿን እገዛ ለመሻት ተገዳለች።
እንደ ብዙዎች እምነትም የጥሪ እና ይግብዣ ወረቀት የሚያሻው ለተድላ እና ለሰርግ እንጂ በሀዘን እና በጭንቀት ለወደቀ ወገን ባለመሆኑ ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ በነካ የአስታራቂነት እጃቸው እና ዲፕሎማሲያዊ አግባብነትን በመጠቀም ወቅታዊው የቤተክርስቲያኒቱ እና የልጆቿን ችግሮችን እና ስጋቶችን ለመቅርፍ ፈጥነው ጣልቃ ይግቡ የሚሉ ወገኖች ተበራክተዋል። (በታምሩ ገዳ)