ባቢሎንን ያፈረሰው/እንዳይገነባ ያደረገው የጋራ ልሳን እጦት ነው! || በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

ባቢሎንን ያፈረሰው/እንዳይገነባ ያደረገው የጋራ ልሳን እጦት ነው! || በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

አማርኛ በኦፊሻል የስራ ቋንቋነቱ የተነሳ በመላው ሀገሪቱ ቋንቋ በትምህርትነት ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጥ የሚለውን የትምህር ሚንስቴርን አዲሱን ፍኖተ ካርታ በመቃወም የኦሮምያና የትግራይ ክልል ‹‹ልሂቃንና›› የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰጡትን መግለጫና ማስፈራሪያ ተከትሎ፣ የትምህርት ሚንስቴር የሰጠውን ማስተባበያ አዳምጬ በጣም ተገርሜያለሁ፤ የጅል ፖለቲካ ያለ ወሰን ሁሉን ነገር እንደሚመርዝ አይቼበታለሁ፡፡

‹‹አስገዳጅነት የለውም፣ ከፈለጉት ክፍል ይጀምሩ፡፡ ካልሆነም መተው ይችላሁ›› አይነት ማስተባበያው አሸማቃቂና፣ እውቀት አጠር ነው፡፡ በሀገር ደረጃ የሚወጣ ፖሊሲ በየክልሉ ተፈጻሚ መሆን አለበት፡፡ ጥናት ተደርጎ፣ ጊዜና እውቀት ፈሶ የወጣ ፍኖተ ካርታ የፈለገ እንዲያስፈጽመው ያልፈለገ እንዲተወው ነው!? አማርኛ የፌደራል የስራ ቋንቋ ነው ብሎ በህግ ያስቀመጠ መንግስት እንዴት ነው በየክልሉ አማርኛን ስትወድ ተማር፣ ሳትወድ ተወው የሚለው!? አማርኛን ያልተማረ የትግራይና የኦሮሞ ወጣት በፌደራል ደረጃ ስራ አይቀጠሩም!? ትምህርት ሚንስቴር የሚሰራው ከህገመንግስቱና ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሰመረ መርሀ-ሀሳብ (system thinking) ተከትሎ መሆን የለበትም!?

የእኛ ሀገር ልሂቃንና ፖለቲከኞች ይገርማሉ፤ እነሱ አማርኛን አቀላጥፈው እየተናገሩ፣ በእንግሊዘኛ በአለም እየተሽከረሩ፣ መጪውን ትውልድ ድህነት ያሰረው ያነሰው ይመስል በልሳን/በቋንቋ ድህነት ሊሰነክሉት ይሽቀዳደማሉ፡፡ ወንድሜ ጁዋር በኤል.ቲቪ ከቤቲ ጋር የምትራቀቀው፣ በቢ.ቢ.ሲና በሲ.ኤን.ኤን ድምጽህን የምታሰማው አማርኛና እንግሊዘኛ ስለቻልክ አይደል! እነዚህን ቋንቋዎች መናገርህ ችግር የሚሆነው ኦሮምኛህን ቢነጥቅህ፣ እንዳትነገር ቢያደርግህ ነበር፡፡ ታዲያ የተጠቀምክበትን ቋንቋ ወጣቶቹ ተምረው እንዳይጠቀሙበት መቀስቀስ/ማድረግ ምክንያቱ ምንድነው!? . . . ይልቅ የሚበጀው አማርኛን ማጠናከር፣ ሌሎችንም እንደ ኦሮምኛ ያሉ በርካታ የአፍ መፍቻ ተናጋሪ ያላቸውን ቋንቋዎች በፌደራል የስራ ቋንቋነት ጨምሮ በፍቅርና በመተሳሰብ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መጣር ነው፡፡ .. . . .

LEAVE A REPLY