“ምነው ተለየህን መስከረም ሳይጠባ
እንቁጣጣሽ ብለን ሳናጌጥ በአበባ”
እጀ ጉርድ ካኪ ሸሚዝ ለብሷል። የሸሚዙን የላይኛውን ቆልፎች ከፍቷታል። ገራጫ ሱሪ አድርጓል። ቡኔ ቆዳ ጫማ ተጫምቷል። በብሔራዊ ቲያአትር ቤት መናፈሻ ውስጥ የፀጋዬ ገ/መድህን ግራር ከበው ተቀምጠዋል። ነጭ ፀጉሩና ነጭ ፂሙ ግርማ አላብሶታል። ከሰዎቹ ሁሉ ጎልቶ የሚታየው እሱ ነው። አብረውት ከተቀመጡት ሰዎች መካከል የቀጠርኩት ሰው ስለነበር ወደ ወንበራቸው አመራሁ። ሠላምታ ተለዋወጠን። ባለ ነጭ ፀጉሩ ሰው ጨዋታውን አቋርጦ በፈገግታና በአክብሮት ሠላምታ ሰጠኝ። እኔም አፀፋውን መለስኩ። የቀጠርኩትን ሰው “እስክትጨርሰ ልጠብቅ” ብዬ በዓይኔ ያልተያዘ ወንበር ሳማትር ባለነጭ ፀጉሩ ሰው በውሸት ቁጣ “ወዴት ለመሄድ ነው በል ተቀምጥ” አለኝ። ሳመናታ ሰውዬው በፈገግታ “ሚስጥር የለንም ሁሉም የጋራ ነው” በማለት ወንበሩን አሳይኝ ተቀመጥኩኝ። በዚህ መንገድ ነበር ለመጀመሪያ ግዜ ከተዘራ ጋር የተዋወኩት። ይህ ከሆነ እነሆ ዛሬ አምስት አመት አለፈው።
የሁሉ “እኩያ”
በተዋወቅን በአመቱ ከአራት አመት በፊት መሆኑ ነው በናዝሪት ከተማ “እስክትመጪ ልበድ” የሚልውን ፊልሜን ስሰራ ዋና ገፀ-ባህሪው ተዘራ ነበር። የፊልሙ የቀረፃ ቡድን አባለት ከአዲስ አበባ የሄድን ስለነበረ እንደ አባት ተቆጣጥሮ፣ ስናጠፋ መክሮ፣ ሲደክመን አበርትቶ ስራችን እንዲሳካ ትልቁን ሀላፊነት ለራሱ በመስጠት ሀላፊነቱን የተወጣ ነበር።
ደንገት የቀረፃ ቦታ ላይ የዘፈን እንጉርጉሮ ከሰማህ በንጉርገሮ ሰው ነቃ ካለ በቃ እዛ ቦታ ላይ ተዘራ አለ ማለት ነው። ደርግ በቋቋማቸው የከፍተኛ ኪነት ውስጥ ያሳለፈው ተዘራ በአካበቢው ጌታር ካየ አፍፍ አድርጎ መጫዎት ልማዱ ነው። እኛም ወደን መስማት ልማዳችን አደርገነዋለን። ጆሊነትን የራሱ ያደረገው ተዜ ጨዋታ አዎቂነቱን ጨምሮበት ወጣትነቱን ሲያወራህ በሚያስቀው ስቀህ በሚያሳዝነው አዝነህ ብቻ አታቆምም አረ በነተዜ ግዜ በኖርኩኝ የሚል መንፈሳዊ ቀናት ሲናውዝህ ነው እራስህን የምታገኘው።
ተዜን በድጋሚ ከአንድ አመት በኃላ በጷግሜ 7 ፊልም ላይ ሳገኘው ለሠኮንድም ከባህሪው ሣይናወጥ፣ ከፈግግታ ሣይቀንስ ከነበረበት ማማ ሳይወርድ ነበር ያገኘሁት። ልታይ ልታይ ሳይል ደብዝዞ ግን ደምቆ የሚታየው ተዘራ ለማ ነበር።
ከሦት ወር በፊት
ሚያዚያ 2011ዓም ከሁለት አመት በኃላ በስራ ከተዜ ጋር በድጋሚ ተገናኘን። ለወራት በዘለቀው “የእነ..እገሌ” የፊልም ስራ ላይ ተዜ አንደኛው ተዋንያይኔ በመሆኑ የማሩ ግዜያቶችን አብረን ልናሳልፍ ችለናል። አንድ ቀን በቀረፃ መካከል ምግብ ተበልቶ አረፍ እንደለን ተዜ መዳህኒት ሲውጥ አየሁት። ተዜን በአራት አመታት ውስጥ ለሦስት የፊልም ስራ ሳገኘው ነው። መዳህኒት ሲውጥ አይቼው አላውቅም ነበር። በዚህ ላይ ዛሬ ሲውጥ ያየዋቸው የመዳህኒቶቹ አይነትና ብዝት ግራ አጋብተውኝ ላፍታ ዝም ብዬ ተመለከትኩት። ውጦ ሲጨርስ “ምነው ተዜ ምን አገኘህ?” አልኩት “ለልቤ ነው” አለኝ ደነገጥኩ “ልብህን ያምካል ወይ?” አልኩት ቀልል አድርጎ “እንደዛ መሆኑ ነው” ብሎኝ ከሌሎች ክሩ ጋር እየሳቀ መጫወቱን ቀጠለ። ቀረፃውን ጀምርን እስክንጨርስ ግዜ ድረስ ተዜ የመዳከም ሆነ ፊቱ ላይ የሚታይ የህመም ምልክት አልነበር። እሱም የሚጠበቅበትን ስራ በአግባቡ እየተወጣ እየሳቀ እየተጫወተ ነበር ስራችን የጨረስነው።
የመጨረሻ መጨረሻ
ከሳምንታት በፊት ተገናኝተን ቡና እየጠጣነ ነው። ተዜ ስለ ቤተሰብ ስለ ስራ ጠየቀኝ መለስኩኝ። ቆየት ብዬ “ተዜ ጤናስ እንዴት ነው?” አልኩት ቡናውን ፉት እያለ ወደላይ ለምስጋና ቀና ብሎ “እሱ ካለ ምን እሆናለሁ!” አለኝ። በመስማማት እራሴን ነቀነኩኝ። ሌሎች ነገሮች ተጨዋውትን ስናበቃ አንቢ እንደሚለኝ እያወኩ ቡና የጠጣንበትን ሒሳብ ልክፍል ስል ፈገግታው ሳይጠፋ “ማን አዘዝህ” በማለት እንደተለመደው ከፈለ። ያዛን ቀን ከተዜ ጋር ልንለያይ ስንል ዝናብ መዝነብ ጀመረ ሰማዩን አየነው ዳመና አልቋጠረም በመገረም “እንዴ” አልኩ ተዜ አይኑን ከሰማዩ ላይ ሳይነቅል “እሱ እንደፈቀደ የፈለገውን በፈለገው ግዜ ነው የሚያደርገው” አለ። በሀሳቡ ከመስማማት ውጪ የምለው አልነበረኝም። ደና ሁን ተባብለን ተለያየ። ሰንለያይ ግን ዳግም እንደምንገናኝ ነበር የማውቀው ….
ትላት ምሽት ነሐሴ 30/2011 ዓም
ከምሽቱ 4:50 ላይ ስልኬ ላይ መልክት መግባቱን የሚያሳውቅ ድምፅ ሰማሁ አንደቀልድ ስልኬን ሳየው የአንዱን ወዳጄን ስም ተመለከትኩኝ። መልክቱን ከፈትኩት ባየሁት ነገር ድርቅ ብዬ ቀረሁ!! ድጋሚ መልክቱን አንበብኩት “አዝናለሁ ሚኪ ተዋንያን ተዘራ ለማ አርፏል” ይላል። መቼ በንደዚህ አይነት ነገር እየቀለደ አይደለም አልኩ። መልክት የላከለኝ ልጅ ጋር እየደወልኩኝ በአንድ ልቤ እንደው እየቀልድኩ ነው ባለኝ የሚል የሞኝ ሃሳብ አስብኩኝ። እኔ ይህን ሳስብ ወዳጄ ስልኩን አንስቶ የፃፈልኝን መልሶ ደገመልኝ። ከዛ በኃላ እኔም ሌሎች ጋር ደወልኩ ሌሎችም ደወሉልኝ የተዜ ማረፍ እውነት መሆኑን አረጋገጥኩኝ። የምለውም የማስበውም አጣሁ …
ዛሬ ያረፈው ተዘራ ለማ ማለት ሰው ስልህ … !!
መንግሰት በሄደ በመጣ ቁጥር የማያንሾካሽኩ መክሊታቸውን ለስጋቸው ፈቃድ የማይቸረችሩ የጥበበብ ሰው ቁጥር ቢባል ተዘራ ለማን አንድ ብለህ ተቆጠረዋለህ። ደግሞ አንድ ቤት ውስጥ ቆመህ ቀረፃ ከመጀመርህ በፊት የቤቱን እቃ ለማስተካከል ስታስብ ድንግት በል ያዝ! ቀስ … ወደዚህ ገፋ … በቃ! ኑ ደግሞ ይሄን እናንሳ የሚል የተዋንያን ድምፅ ከሰማክ ያ ሰው አመለ ሸጋው ተዘራ ለማ ስለመሆኑ እንዳትጠራጠር። የሆነ የቀረፃ ቦታ ስትፈልግ ቀድሞ ቦታው ከተገኝ ፕሮዳክሽኑ ላይ ተዘራ ለማለ መኖሩን አወክ ማለት ነው። የሆነ ተዋንያን ለጠየቁት ሁሉ ልምዱን ሲያካፍል አንጠፍጥፎ ነው የሚናገረው ከተባለክ ያ ሰው ስለ ተዘራ ለማ እያወራልክ እንደሆነ ትረዳለህ። የትንሹም የትልቁም እኩያ የሆነ ተዜ አስር ፊልምም የሰራ ለአስር ደቂቃም ለፊልም ስራ የመጣ ሰው ለሁለቱም እኩል ክብር የሚሰጥ ሰው ነው። ለከፈላቸው ሰው የሚጮህ ጥበበኛ ነን ባዮች በበዙበት ዘመን ለተከፈላባቸው ጉዳይ ብቻ ዘብ ከሚቋሙት የኪነት ሰዎች መካከል ተዘራ ለማን ፊተኛው ወንበር ላይ ታገኘዋለህ። እንግዲህ ዛሬ ያረፈው ተዘራ ለማ ማለት ከትወናው በተጨማሪ ሰው ስልህ ይሄን ማለቴ ነው።
ተዘራን ስሰናበት!!
እስካሁን በዝግጅት ዘርፍ የሰራዎቸው ሦስት ፊልሞች ላይ ተዜ ምርጫዬ ስለነበር አብሬው ሰርቻለሁ። ከተዜ ጋር ግንኙነታችን የተዋንያን እና የአዘጋጅ ብቻ አልነበረም። ከዛ ያልፋል ይሻገራል። መካሪየ፣ የስራ ባልደረባዬና ጓደኛዬ ከሳምንታት በፊት ሳገኝህ ያለ ደመና ድንገት ዝናብ መዝነቡ ሲያሰገረምኝ “እሱ እንደፈቀደ የፈለገውን በፈለገው ግዜ ነው የሚያደርገው” ያልከው ዛሬ ምን እንደሆነ ገብቶኛል። ለካስ ስለራስህም ነበር የነገርከኝ። ተዜ ድንገት ነው አያጣነህ። የሱን ትእዛዝ ማን መቃውም ይችላል!? ማንም አይችልም። ተዜ ትዝታህ ከኛ ጋር ይኖራል። አንተ በስራዎችህ ህያው ነህ።
አምላክ ማረፊያህን ከደጋጎቹ ጎን በቀኙ ያድርግልን። ነፍስህን ይማረው። አሜን።
ጷጉሜ 1/13/2011 ዓም
አዲስ አበባ