ከኢ/ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

ከኢ/ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የሥልጣኔና የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ ትምህርትና ሥልጣኔን ያስጀመረች፣ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲና የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ገና ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዓትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኮትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት የጣለች፣ በውጭ ወራሪ ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ወቅት የእምነቱ ተከታይ ምእመናኖቿና አገልጋይ ካህናቶቿ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእምነታችን መገለጫ የሆነውን የቃልኪዳኑን ታቦት ይዘው በየጦር ግንባሩ በመሰለፍና በመሰዋት እንኳንስ ሕዝቦቿ ምድሪቱም ለወራሪ ጠላት እንዳትገዛ በማውገዝ የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበረችና ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሌሎች አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ቅኝ ገዥዎች ያልደፈሯት አገር ተብላ በታሪክ ድርሳናት እንድትመዘገብ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች የሀገር ባለውለታ እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን እንኳንስ እኛ ልጆቿ ይቅርና የታሪክ ምሁራን ዘወትር በየአደባባዩ የሚመሰክሩት በብዕር ሳይሆን ለነጻነት በተከፈለ በአበው አባቶቻችን ደም የተጻፈ አኲሪ ታሪካችን ነው፡፡

እናት ቤተ ክርስቲያን ከላይ በአጭሩ የተጠቀሱትን ዘመናት የማይሽሩት ታሪካዊ ውለታዎችን ለሀገር ያበረከተች ቤተ ክርስቲያን ብትሆንም አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የጥፋት ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚፈጽሙት ከፍተኛ የሆነ አስተዳደራዊ በደልና የተቀናጀ ጥቃት እያደረሰብን ያለውን መከራና ችግር ቤተ ክርስቲያናችን ባላት ሀገራዊ ኃላፊነት ችግሩን በትዕግስት አሳለፈችው እንጂ እየተፈጸመባት ካለው ግፍና በደል አንጻር ይከሰት የነበረው ችግርና ሀገራዊ ቀውስ በቀለሉ የሚታለፍ ባልሆነም ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እየደረሰብን ያለውን በደልና መከራ ከዛሬ ነገ ይሻላል በማለት ታግሰን ብንችለውም እያደር እየባሰና የችግሩም አድማስ እየሰፋ ሊሄድ ችሏል፡፡ ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው በደል ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም ቅሉበተለይ በአሁኑ ወቅት መልኩን እየቀያየረ እና ለዘመናት የቆየ አንድነቷን በማፈራረስ ከቤተ ክርስቲያኒቱም አልፎ ሀገራዊ ቀውስና አለመረጋጋት የሚያስከትል የጥፋት አጀንዳን ባነገቡ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የጀመሩት እንቅስቃሴ ወደከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ እና የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በስፋት ከተወያየ የሚከተለውንየአቋም መግለጫ አውጥቷል፡-

1. አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ እና ለጥፋት ለተደራጁ ቡድኖች ፖለቲካዊ ሽፋን በመስጠት በልዩ ልዩ ክልሎች የተፈጸሙት የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የአገልጋይ ካህናት እና ምእመናን መገደል፣ ዘመን የማይተካቸው የሀገር መገለጫ የሆኑትን ጥንታውያን እና ታሪካውያን ቅርሶችን በማቃጠል ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿን ታሪክ እና ቅርስ አልባ በማድረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን በደሎች እና ግፎች ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል፤

2. ቤተ ክርስቲያኒቱ ባህል፣ ቀለም፣ ቋንቋ እና ብሔር ሳትለይ በአንድነት እና በአቃፊነት ለሀገር ውለታ ያበረከተች መሆኗ ተዘንግቶ በእምነት ሽፋን የቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች የሆኑ ምእመናን ካደጉበትና ሀብት እና ንብረት ካፈሩበት ቀያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉ፣ በእምነታቸው ብቻ ተገደው በመደፈር እና ልዩ ልዩ የሥነ ልቦና ጥቃት እንዲደርስባቸው በማድረግ እንዲሁም በድብደባ እና በዛቻ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ እየተደረገ ያለውን ሕገ ወጥ አድራጎትን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል

3. ለባለውለታዋ እናት ቤተ ክርስቲያን በማይመጥን እና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሕጋዊ ይዞታዋን እና የአምልኮት ቦታዎቿን በመንጠቅ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን እንደ ሽፋን በመጠቀም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በደል እና ግፍ የሚፈጽሙ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኃላፊዎችን ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ አድራጎታቸው እንዲታቀቡ በጥብቅ ያሳስባል

4. እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ በሀገራዊ የሀላፊነት ስሜት ታግሶ እና ችሎ ሞቱ፣ እሥራቱ፣ ዛቻው፣ ስደቱ እና እንግልቱ ሳይበግረው ሀገር በአንድነት እና በፍቅር እንዲሁም በመተሳሰብ እንድትቀጥል ታሪክ የማይረሳው መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን አገልጋይ ካህናት እና መላውን ምእመናንን እንዲሁም ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በአጠቃላይ መላው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ላሳያችሁት ትዕግስት የተመላበት ሀገራዊ ሀላፊነት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያመሰገነ እንደአሁን ቀደሙ ሁሉ ትዕግስት የተመለበትን ሀገራዊ ኃላፊነታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለውን እና ወደፊትም ሊደርስ የታቀደውን ግፍ እና ጥፋት በአንድነት እና በኅብረት ከእኛ ከመንፈስ ቅዱስ አባቶቻችሁ ጋር በመሰለፍ በጽናት ቤተ ክርስቲያናችሁን እንድትጠብቁ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን ያስተላልፋል፤

5. በቤተ ክርስቲያናች እምነት እና ቀኖና መሠረት በእምነታቸው ምክንያት በሰይፍ የታረዱ፣ በጥይት የተገደሉት፣ በእሳት የተቃጠሉ፣ ሕይወታቸውን ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው የሰጡ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በሰማእትነት ክብር እና ማዕረግ ዘወትር እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በሰማእትነት ሕይወታቸውንየሰጡ አገልጋዮች እና ምእመናን ቤተሰቦች ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዳይናጋ በተቻለ አቅም ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረግ ሁላችንም ከጎናቸው በመሆን የድርሻችንን እንወጣ ዘንድ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽኑ መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፤

6. እናት ቤተ ክርስቲያችን በእንግዳ ተቀባይነቷ እና በአቃፊነቷ ዛሬ ለቁጥር አዳጋች የሆኑት ቤተ እምነቶች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ ሰላማዊ፣ የማምለክ መብታቸው እንዲረጋገጥ የበኩሏን ድርሻ የተወጣች መሆኗን ሁሉም ቤተ እምነቶች በየአደባባዩ የሚመሰክሩት እውነታ እንደመሆኑ መጠን በእናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ ሁሉም ቤተ እምነቶች በአንድነት እና በተባበረ ድምጽ በጽናት እንዲያወግዙ እና ለእምነት ተከታዮቻቸውም የቤተ ክርስያናችን ጥፋት እና በደል እንዲወገድ የበኩለቸውን ሚና እንዲወጡ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን እንዲያስተላልፉልን በቅድስተ ቤተ ክርስቲያናችን ስም የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለልን፣

7. የፍትሕ አካላት ለምሥረታችሁ እና ለእድገታችሁ ውለታ የከፈለችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የቀደመ ውለታዋን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሕግ ተጥሶ እና ፍትሕ ተጓድሎ በቤተ ክርስቲያነቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና በደል በጽናት ከማውገዝ በተጨማሪ አጥፊዎችን ለፍትሕ በማቅረብ እና ተመጣጣኝ እና ለሌሎችም አስተማሪ የሆነ ውሳኔ በመስጠት እና በማሰጠት የራስዋየሆነ ተቋማዊ ሕልውና እና መዋቅር ያላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ መብት እና ልእልና መከበር የበኩላችሁን ድርሻ ትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ጥሪ ያስተላልፋል

8. በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የተከበረውን እና የተረጋገጠውን የእምነት ተቋማት ነፃነት እና ሉዓላዊ ክብር በሚጋፋ ሁኔታ እየተፈጸሙ ያሉት የመብት ጥሰቶች እና የጥፋት በደሎችን የማረም እና ከመፈጸማቸውም በፊት የመከላከል ኃላፊነት ያለባችሁ በየደረጃው የምትገኙ የመንግሥት አካላት በሕገ መንግሥቱ የተጣለባችሁን ሕግን የማስከበር አደራና ኃላፊነት፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መብት የማስጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስያኒቱን ልዕልና እና ክብር እንድታስጠብቁ በቅድስት ቤተ ክርስያናችን ስም ቅዱስ ሲኖዶስ አደራውን ጥሎባችኋል በማለት በጽኑ ያሳስባል፤

9. አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ ሰላም እና ፍቅርን በመስበክ እና በተግባር በመፈጸም ለሀገር እና ለመላው ዓለም አርኣያ የሆነችውን እናት ቤተ ክርስቲያን ያለ ስሟ ስም፣ ያለግብረዋ ግብር በመስጠት በተለይም የተከበረውን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ባለውለታ የሆነውን የኦሮሞን ሕዝብ ቤተ ክርስቲያናችን እንዳገለልችው እና አቅዳ እንደበደለቸው ለማስመሰል እና ለማስቆጠር አቅደው ቤተ ክርስያኒቱን እና ሀገርን ለመከፋፈል ድብቅ አጀንዳ ይዘው በተነሡ ግለሰቦች እና ቡድኖች አለአግባብ እየተሠራጨ ያለው አፍራሽ እና ከፋፋይ ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም እና ድምጽ ካለመሆኑ በተጨማሪ ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ እንደሚያስረዳን ሕገ ወጦቹ ግለሰቦቹ እና ቡድኖች የተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ የሚያገለግለው እና የሚባርከው መንፈሳዊ አባት እንደሌለው ቢገልጹም እንኳንስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ለሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ነፃነት ከተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ የተገኙት እና ነፍሳቸውን ሳይሳሱ በሰማዕትነት ዋጋ የከፈሉትን የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ታሪክ የማይረሳውን ውለታ የዘነጋ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት በመዓርገ ጵጵስና ሹማ በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት ለሐዋርያ አገልግሎት አሠማርታ መላውን የክልሉን ሕዝበ ክርስቲያን በማገልገል ከቤተ ክርስቲያኒቱ አልፎ ለክልሉ ሰላም እና አንድነት ዋጋ በመክፈል ላይ የሚገኙትን ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኙትን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት እና በእነሱ የሚመሩ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ያሉ በርካታ ጽ/ቤቶች ከዐሥራ አምስት የሚበልጡ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩ የቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቶች እና መዋቅሮችን ፈጽሞ የካደ አድርጎት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ እያወገዘ በዚህ አድርጎት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉትን ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከዚህ አድርጎታቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፤

10. የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የኦሮሞ ሕዝብ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ እንደ ትናንቱ ሁሉ ባህልን፣ ቀለምን፣ ቋንቋ እና ብሔርን መሠረት ሳታደርግ በተቻላት አቅም መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ተደራሽ ለማድረግ የጸሎት፣ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እና ሃይማኖታዊ የትምህርት መጻሕፍትን በኦሮምኛ ቋንቋ በመተርጎም እና በማዘጋጀት፣ ከአምስት በላይ የካህናት ማሠልጠኛ ተቋማትን፣ አንድ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅን በጀት መድባ በማቋቋም መላውን የኦሮሞ ብሔር ሕዝበ ክርስቲያን ስታገለገል የቆየችውን እና ያላቸውን ወደ ፊትም ዘመኑን በዋጀ መልኩ አጠናክራ የምታገለግለውን እናት ቤተ ክርስያናችሁ መሆኗን አውቃችሁ አንድነታችሁን እና ፍቅረ ቤተ ክርስቲያናችሁን ለመከፋፈል የተነሡትን የጥፋት ኃይሎች በጽናት በመቃወምና አንድነት እና ፍቅራችሁን አጠናክራችሁ ቤተ ክርስያናችሁን እና ሃይማኖታችሁን ከጥፋት ኃይሎች ትጠብቁ እና ትንከባከቡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ያሳስባል፣

11. አዲስ የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚል መዋቅር በራሳቸው ሥልጣን መሥርተው በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት ግለሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ በሰጣቸው እድል ቀርበው የተወያዩ ሲሆን በውይይቱም ወቅት ጥያቄውን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአሁን ቀደም በኮሚቴ ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ ሰጥቶበት እያለ ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰጠው በማስመሰል ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናና ፈቃድ ውጭ አዲስ መዋቅር ፈጥረው መግለጫ መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን አምነው ይቅርታ ለመጠየቅ ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተን እንመለስ ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 የተቀጠሩ ቢሆንም በዕለቱ የኮሚቴው ዋና ተጠሪ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ያልተገኙ ሲሆን 2 የኮሚቴው አባላት ብቻ ከተሰጣቸው ሰዓት አሳልፈው ከመምጣታቸውን በላይ 2ቱ ግለሰቦች በጽሑፍ ባቀረቡት ምላሽ በሕገወጥ አቋማቸው የፀኑ መሆናቸውን የገለጹ በመሆኑ የግለሰቦቹ እንቅስቃሴም ሆነ የኦሮሞ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተብሎ የተጠቀሰው አደረጃጀት ሕጋዊ እውቅና የሌለው መሆኑን ሁላችሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን አውቃችሁ የግለሰቦቹን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመቃወምና በቀደመው አንድነታችሁ ጸንታችሁ ቤተ ክርስቲያናችሁንና ሃይማኖታችሁን ትጠብቁ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

12. ከዚህ በላይ በተገለጸው መሠረት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውክልናም ሆነ ከሕገ የመነጨ ሥልጣን ሳይኖራቸውና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሕግ የመነጨ መብት በመጋፋት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሎጎ /አርማ/፣ ማህተምና መጠሪያ ስያሜ መጠቀማቸው ሕገወጥ አድራጎት በመሆኑ የሚመለከታችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግለሰቦቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሎጎ /አርማ/ እና ማህተም እንዲሁም መጠሪያ ስያሜ መጠቀም የማይችሉ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምት በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ታስከብሩ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት እያሳሰበ፤ የጽ/ቤታችን የሕግ አገልግሎት መምሪያም በሕገወጦች ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ያስከብር ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ አዟል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በዝርዝር በተገለጹት የአቋም መግለጫዎችና በሌሎችም ዓበይት ጉዳዮች ላይ በመወያየትና ተገቢውን ውሳኔ በመስጠት ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

LEAVE A REPLY